በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?

የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?

የአምላክ ዓላማ ሰዎች እንዲሞቱ አልነበረም። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ፍጹም አካልና ፍጹም አእምሮ ነበራቸው፤ እስካሁንም ድረስ በሕይወት መኖር ይችሉ ነበር። ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ ከነበረ አንድ ዛፍ ጋር በተያያዘ ለአዳም የሰጠው ትእዛዝ ይህን በግልጽ ያሳያል።

አምላክ አዳምን “ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) አዳም ዞሮ ዞሮ አርጅቶ መሞቱ የማይቀር ቢሆን ኖሮ ይህ ትእዛዝ ምንም ትርጉም አይሰጥም ነበር። አዳም ከዛፉ ካልበላ እንደማይሞት ያውቅ ነበር።

የአምላክ ዓላማ ሰዎች እንዲሞቱ አልነበረም

የአትክልት ስፍራው፣ ፍሬ በሚያፈሩ ዛፎች የተሞላ በመሆኑ አዳምና ሔዋን በሕይወት ለመኖር ከዚህ ዛፍ መብላት አያስፈልጋቸውም ነበር። (ዘፍጥረት 2:9) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከዚህ ዛፍ ባለመብላት ሕይወት ለሰጣቸው አምላክ ታዛዥ መሆናቸውን ማሳየት ይችሉ ነበር። ከዛፉ አለመብላታቸው አምላክ እነሱን የመምራት መብት እንዳለው እንደሚያምኑ ያሳይ ነበር።

አዳምና ሔዋን የሞቱት ለምንድን ነው?

አዳምና ሔዋን የሞቱት ለምን እንደሆነ ለማወቅ በሰይጣንና በሔዋን መካከል የተደረገውን ውይይት መመርመር ይኖርብናል፤ ይህ ውይይት የሁላችንንም ሕይወት ይነካል። ሰይጣን ዲያብሎስ አንድን እባብ በመጠቀም አደገኛ ውሸት ተናገረ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እባብም ይሖዋ አምላክ ከሠራቸው የዱር እንስሳት ሁሉ እጅግ ጠንቃቃ ነበር። በመሆኑም ሴቲቱን ‘በእርግጥ አምላክ “በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ” ብሏችኋል?’ ሲል ጠየቃት።”—ዘፍጥረት 3:1

ሔዋንም በምላሹ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን። ይሁንና በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኘውን ዛፍ ፍሬ በተመለከተ አምላክ ‘ከእሱ አትብሉ፤ ፈጽሞም አትንኩት፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል” አለችው። ከዚያም እባቡ እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም። አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።” በዚህ መንገድ ሰይጣን ይሖዋ ውሸታም እንደሆነና አዳምንና ሔዋንን መልካም ነገር እንደነፈጋቸው ተናገረ።—ዘፍጥረት 3:2-5

ሔዋን ሰይጣንን አመነችው። ዛፉን ትኩር ብላ ስታየው ለዓይን የሚማርክና የሚያጓጓ ነበር! ስለዚህ ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች። መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ የሆነውን ሲገልጽ “ባሏም አብሯት ሲሆን ለእሱም ሰጠችው፤ እሱም በላ” ይላል።—ዘፍጥረት 3:6

አምላክ አዳምን “ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” ብሎት ነበር።​—ዘፍጥረት 2:17

አምላክ የሚወዳቸው ልጆቹ ሆን ብለው ትእዛዙን እንደጣሱ ሲያይ ምን ያህል አዝኖ ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! ታዲያ ምን አደረገ? ይሖዋ አዳምን እንዲህ አለው፦ “ከመሬት ስለተገኘህ ወደ መሬት [ትመለሳለህ]። አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ።” (ዘፍጥረት 3:17-19) “ስለዚህ አዳም በአጠቃላይ 930 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።” (ዘፍጥረት 5:5) አዳም ወደ ሰማይ ወይም ወደ ሌላ መንፈሳዊ ዓለም አልሄደም። አዳም ከምድር አፈር ከመፈጠሩ በፊት ሕልውና አልነበረውም። ስለዚህ ሲሞት፣ እንደተፈጠረበት አፈር ሕይወት አልባ ሆነ። ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጭ ሆነ። ይህ ምንኛ የሚያሳዝን ነው!

ፍጹም ያልሆንነው ለምንድን ነው?

አዳምና ሔዋን ሆን ብለው የአምላክን ትእዛዝ በመጣሳቸው ምክንያት ፍጽምናቸውንም ሆነ ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጡ። ኃጢአት መሥራታቸው በአካላቸው ላይ ለውጥ አመጣ፤ ፍጽምና የሌላቸውና ኃጢአተኞች ሆኑ። ሆኖም የሠሩት ኃጢአት የጎዳው እነሱን ብቻ አይደለም። ኃጢአትን ለዘሮቻቸው አስተላልፈዋል። ሮም 5:12 እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኃጢአትና ስለ ሞት ሲገልጽ ‘ሕዝቦችን ሁሉ የሸፈነው ከፈን እንዲሁም ብሔራትን ሁሉ ተብትቦ የያዘው መሸፈኛ’ የሚል ምሳሌ ይጠቀማል። (ኢሳይያስ 25:7) ይህ ከፈን ማምለጫ እንደሌለው መርዛማ አየር ሰዎችን ከቧቸዋል። በእርግጥም ‘ሁሉም በአዳም ይሞታሉ።’ (1 ቆሮንቶስ 15:22) አሁን የሚነሳው ጥያቄ ሐዋርያው ጳውሎስ ካነሳው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ጳውሎስ “እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?” ብሎ ነበር። በእርግጥ ሊታደገን የሚችል አካል አለ?—ሮም 7:24