በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

የክርስቶስ ወታደር ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ

የክርስቶስ ወታደር ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ

ወታደሮቹ የጥይት እሩምታ አዘነቡብን። እኔም ከተደበቅኩበት ቦታ ሆኜ ነጭ መሐረብ ከፍ አድርጌ አሳየሁ። ይተኩሱ የነበሩት ወታደሮች ከተደበቅኩበት እንድወጣ አዘዙኝ። ይገድሉኝ ይሆናል የሚል ስጋት ስለነበረኝ ፈራ ተባ እያልኩ ወደ እነሱ ተጠጋሁ። ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የገባሁት እንዴት ነው?

የተወለድኩት ካሪትዛ በተባለች በግሪክ የምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ በ1926 ነው። ታታሪ የሆኑት ወላጆቼ በአጠቃላይ ስምንት ልጆች የነበሯቸው ሲሆን እኔ ሰባተኛው ነኝ።

ወላጆቼ እኔን ከመውለዳቸው ከአንድ ዓመት በፊት ጆን ፓፓሪዘስ ከተባለ ቀናተኛና ተጫዋች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ጋር ተገናኝተው ነበር። ወላጆቼ፣ ጆን ያቀረበው አሳማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ስለማረካቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በመንደራችን ውስጥ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። እናቴ በይሖዋ አምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ነበራት፤ ማንበብና መጻፍ ባትችልም ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ለሌሎች ትመሠክር ነበር። የሚያሳዝነው ነገር አባቴ በሌሎች አለፍጽምና ላይ በማተኮሩ ከጊዜ በኋላ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘቱን አቆመ።

እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና እህቶቼ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት የነበረን ቢሆንም ልጆችን የሚማርኩ ነገሮች ትኩረታችንን ሰርቀውት ነበር። በዚህ መሃል በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አውሮፓን ሲያናውጣት በመንደራችን ውስጥ የተፈጠረው ነገር አስደነገጠን። ጎረቤታችንና የቅርብ ዘመዳችን የሆነው ኒኮላስ ሳራስ በግሪክ ጦር ሠራዊት ውስጥ እንዲያገለግል ተመለመለ፤ በወቅቱ ኒኮላስ ከተጠመቀ ብዙም አልቆየም ነበር። የ20 ዓመት ወጣት የነበረው ኒኮላስ ለወታደራዊ ባለሥልጣናቱ “የክርስቶስ ወታደር ስለሆንኩ መዋጋት አልችልም” ሲል በድፍረት አቋሙን ገለጸላቸው። በዚህ ምክንያት ተከስሶ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን የአሥር ዓመት እስራት ተፈረደበት። ይህን ስንሰማ በጣም ደነገጥን!

ደስ የሚለው ነገር በ1941 መጀመሪያ ላይ የኅብረ ብሔሩ ጦር ግሪክን ለአጭር ጊዜ ሲቆጣጠር ኒኮላስ ከእስር ተፈታ። ኒኮላስ ወደ ካሪትዛ ሲመለስ ታላቅ ወንድሜ ኢልያስ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያሉትን ጥያቄዎች ሁሉ አዥጎደጎደበት። እኔም ውይይቱን በጉጉት አዳመጥኩ። ከዚያ በኋላ እኔ፣ ኢልያስና ታናሽ እህታችን ኤፍሞርፍያ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲሁም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በቋሚነት መሰብሰብ ጀመርን። በቀጣዩ ዓመት ሦስታችንም ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ተጠመቅን። ከጊዜ በኋላ አራት ወንድሞቼና እህቶቼም ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።

በ1942 በካሪትዛ ጉባኤ ውስጥ ከ15 እስከ 25 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ያሉ ዘጠኝ ወጣት ወንድሞችና እህቶች ይገኙ ነበር። ሁላችንም ከባድ ፈተና እንደሚጠብቀን ተረድተን ነበር። በመሆኑም ራሳችንን ለማጠናከር ስንል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አንድ ላይ ተሰባስበን መጽሐፍ ቅዱስን እናጠና፣ መንፈሳዊ መዝሙሮችን እንዘምር እንዲሁም እንጸልይ ነበር። ይህም እምነታችን ጠንካራ እንዲሆን ረድቶናል።

ዲሚትሪየስና ጓደኞቹ በካሪትዛ

የእርስ በርስ ጦርነት

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ የግሪክ ኮሚኒስቶች በግሪክ መንግሥት ላይ በማመፃቸው ከባድ የሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ። ኮምኒስት የሆኑት ሽምቅ ተዋጊዎች በገጠራማ አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ እንዲሁም በየመንደሩ ያሉት ነዋሪዎች ከእነሱ ጎን እንዲሰለፉ ያስገድዱ ነበር። እኛ የምንኖርበትን መንደር በወረሩበት ወቅት ሦስት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮችን ይኸውም አንቶኒዮ ሱካሪስን፣ ኢልያስንና እኔን ወሰዱን። ክርስቲያኖች በመሆናችን ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ እንደሆንን በመናገር እንዲለቁን ብንማጸናቸውም ከመንደራችን 12 ሰዓት ርቆ ወደሚገኘው ኦሊምፐስ ተራራ እንድንጓዝ አስገደዱን።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አንድ የኮሚኒስት አዛዥ፣ የሽምቅ ውጊያ ቡድኑን እንድንቀላቀል አዘዘን። እውነተኛ ክርስቲያኖች በሌሎች ሰዎች ላይ የጦር መሣሪያ እንደማያነሱ ስንነግረው አዛዡ ተበሳጭቶ ጄኔራሉ ፊት አቀረበን። ለአዛዡ የነገርነውን ለጄኔራሉ ደገምንለት፤ እሱም “እንደዚያ ከሆነ በቅሎ ይዛችሁ ሂዱና በጦር ሜዳ ላይ የተጎዱ ወታደሮችን ወደ ሆስፒታል ውሰዱ” አለን።

እኛ ግን “የመንግሥት ወታደሮች ቢይዙንስ? በውጊያው ላይ እየተሳተፍን እንዳለ አድርገው አይመለከቱንም?” ብለን መለስንለት። እሱም “እንግዲያው በጦር ግንባር ላሉት ዳቦ አመላልሱ” አለን። እኛም መልሰን “በቅሎ ይዘን ስንሄድ አንድ አዛዥ ቢያየንና በጦር ግንባር ላሉት መሣሪያ እንድናደርስ ቢያዘንስ?” አልነው። ጄኔራሉ ብዙ ካወጣና ካወረደ በኋላ “መቼም በግ መጠበቅ ትችላላችሁ! በተራራው ላይ ሆናችሁ በጎቹን ጠብቁ” አለን።

በመሆኑም የእርስ በርስ ጦርነቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅት እኛ ሦስታችን በግ እንጠብቅ ነበር፤ ይህን ማድረጉ ሕሊናችንን አልረበሸንም። ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ኢልያስ የቤታችን የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን መበለት የሆነችውን እናታችንን ለመንከባከብ ወደ ቤት እንዲመለስ ተፈቀደለት። አንቶኒዮም ቢሆን ስለታመመ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ተፈቀደለት። እኔን ግን አልለቀቁኝም።

በዚህ መሃል የግሪክ ሠራዊት በኮሚኒስቶቹ ላይ እያየለ መጣ። እኔን የያዘኝ የዓማፂያኑ ቡድንም በተራሮቹ በኩል አድርጎ ጎረቤት አገር ወደሆነችው አልባኒያ ሸሸ። ወደ ድንበር አቅራቢያ ስንደርስ በድንገት የግሪክ ወታደሮች ከበቡን። ዓማፂያኑ ስለተሸበሩ ሸሽተው አመለጡ። እኔም አንድ የወደቀ ዛፍ ሥር ተደበቅኩ፤ በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት ሁኔታ ያጋጠመኝ በዚህ ወቅት ነበር።

ለግሪክ ወታደሮች፣ ኮሚኒስቶቹ ምርኮኛ አድርገው ይዘውኝ እንደነበር ስነግራቸው በቬርያ (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቤርያ ተብላ የተጠራችው ጥንታዊ ከተማ) አቅራቢያ ወዳለ አንድ ወታደራዊ ካምፕ ለምርመራ ወሰዱኝ። በዚያም ለወታደሮቹ ምሽግ እንድቆፍር ታዘዝኩ። ፈቃደኛ ባለመሆኔ አዛዡ፣ እስረኞች ለቅጣት ወደሚላኩባት ወደ ማክሮኒሶስ (ማክሮኒሲ) ደሴት ላከኝ፤ ይህች ደሴት በአስከፊነቷ የታወቀች ናት።

አስፈሪዋ ደሴት

ማክሮኒሶስ ከአቴንስ 50 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የአቲካ ባሕር ዳርቻ ላይ ያለች ወና የሆነች ዓለታማ ደሴት ናት፤ አካባቢው ውኃ የሌለበት በረሃ ነው። ደሴቲቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ 13 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖራት ሰፊ በሆነችበት ቦታ ላይ እንኳ የጎን ስፋቷ 2.5 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ይሁንና ከ1947 እስከ 1958 ባሉት ዓመታት ከ100,000 የሚበልጡ እስረኞችን አስተናግዳለች፤ ከእነዚህ እስረኞች መካከል ኮሚኒስቶችና በኮሚኒስትነት የተጠረጠሩ ሰዎች፣ ዓማፂ የነበሩ ግለሰቦች እንዲሁም በርካታ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል።

በ1949 መጀመሪያ አካባቢ እዚያ ስደርስ እስረኞቹ በተለያዩ ካምፖች ውስጥ ታስረው ነበር። ጥብቅ ቁጥጥር በማይደረግበት ካምፕ ውስጥ ከሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ጋር ታሰርኩ። አሥር ሰዎችን ለመያዝ በተዘጋጀ አንድ የሸራ ድንኳን ውስጥ 40 እስረኞች መሬት ላይ እንተኛ ነበር። የምንጠጣው ውኃ መጥፎ ጠረን ያለው ሲሆን ብዙውን ጊዜ የምንበላው ምስርና ደበርጃን ነበር። ያለማቋረጥ የሚነፍሰው ነፋስና አቧራው የሚያስመርር ነበር። ይሁን እንጂ ድንጋዮችን ከቦታ ወደ ቦታ ያለማቋረጥ እንድናመላልስ አለማድረጋቸውም ተመስገን ነው፤ ይህ እስረኞችን ለማሠቃየት የሚጠቀሙበት ጭካኔ የተሞላበት ቅጣት ሲሆን እንዲህ እንዲያደርጉ የታዘዙ በርካታ እስረኞች አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በማክሮኒሶስ ደሴት በግዞት ከነበሩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር

አንድ ቀን በባሕሩ ዳርቻ እየተዘዋወርኩ ሳለ በሌሎች ካምፖች ከታሰሩ በርከት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። በመገናኘታችን ምን ያህል እንደተደሰትን መግለጽ ያስቸግራል! እንዳንያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንገናኝ ነበር። ለሌሎች እስረኞችም በጥበብ እንመሠክር የነበረ ሲሆን ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካፈላችን እንዲሁም ከልባችን መጸለያችን መንፈሳዊነታችንን ጠብቀን እንድንቀጥል ረድቶናል።

ከባድ መከራ

ባለሥልጣናቱ አመለካከቴን እንድለውጥ ለማድረግ ለአሥር ወራት በዚህ ሁኔታ ካቆዩኝ በኋላ ወታደራዊ ልብስ ሊያለብሱኝ ሞከሩ። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኔ ወደ ካምፑ አዛዥ አቀረቡኝ። ለአዛዡ “እኔ የምፈልገው የክርስቶስ ወታደር ብቻ መሆን ነው” የሚል ሐሳብ ወረቀት ላይ ጽፌ ሰጠሁት። አዛዡ ካስፈራራኝ በኋላ ከእሱ ቀጥሎ ላለው ባለሥልጣን አሳልፎ ሰጠኝ፤ ይህ ሰው የግሪክ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳሳት ሲሆን የቄስ ልብስ ለብሶ ነበር። ላነሳልኝ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ በድፍረት ስመልስለት “ከፊቴ ውሰዱልኝ። ይሄ ጽንፈኛ ነው!” ሲል በቁጣ ተናገረ።

በማግስቱም ወታደሮቹ፣ የጦር ሠራዊቱን ልብስ እንድለብስ እንደገና አዘዙኝ። ለመልበስ ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ ሲያዩ በቡጢ እና በዱላ ደበደቡኝ። ከዚያም ወደ ካምፑ ክሊኒክ ወስደው አጥንቶቼ እንዳልተሰበሩ ካረጋገጡ በኋላ ወደ ድንኳኔ መለሱኝ። ለሁለት ወራት ያህል በየቀኑ እንዲህ ያደርጉ ነበር።

እምነቴን ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆኔ የተበሳጩት ወታደሮች በመጨረሻ ሌላ ዘዴ ቀየሱ። እጆቼን ወደ ኋላ ካሰሩ በኋላ ያላንዳች ርኅራኄ ውስጥ እግሬን በገመድ ገረፉኝ። ከባድ ሥቃይ ላይ በነበርኩበት በዚያ ወቅት ኢየሱስ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት ትዝ አሉኝ፦ “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁ . . . ደስተኞች ናችሁ። በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።” (ማቴ. 5:11, 12) ሥቃዩ ማቆሚያ ያለው አይመስልም ነበር፤ በመጨረሻም ራሴን ሳትኩ።

ስነቃ ቀዝቃዛ በሆነ ክፍል ውስጥ ነበርኩ፤ ዳቦም ሆነ ውኃ እንዲሁም ብርድ ልብስ አልሰጡኝም። እንደዚያም ሆኖ የመረጋጋት ስሜት ተሰማኝ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በተገባልን መሠረት ‘የአምላክ ሰላም ልቤንና ሐሳቤን ጠብቆልኛል።’ (ፊልጵ. 4:7 ግርጌ) በቀጣዩ ቀን አንድ ደግ ወታደር ዳቦ፣ ውኃ እንዲሁም ካፖርት ሰጠኝ። ሌላ ወታደር ደግሞ የራሱን ምግብ ሰጥቶኛል። በዚህና በሌሎች ብዙ መንገዶች የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ ተመልክቻለሁ።

ባለሥልጣናቱ የማይታረም ዓመፀኛ እንደሆንኩ አድርገው ስለተመለከቱኝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት እንድቀርብ ወደ አቴንስ ወሰዱኝ። ፍርድ ቤቱም ከማክሮኒሶስ በስተ ምሥራቅ 50 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በያሮስ (ግያሮስ) ደሴት ለሦስት ዓመታት እንድታሰር በየነብኝ።

“እናምናችኋለን”

የያሮስ እስር ቤት ከቀይ ጡቦች የተሠራ ትልቅ ሕንፃ ሲሆን በውስጡም ከ5,000 የሚበልጡ የፖለቲካ እስረኞችን ይዞ ነበር። በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት የታሰሩ ሰባት የይሖዋ ምሥክሮችም በዚያ ነበሩ። መሰብሰብ በጥብቅ የተከለከለ ቢሆንም ሰባታችንም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚስጥር እንገናኝ ነበር። የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎች እንኳ በድብቅ ይገቡልን የነበረ ሲሆን ስንሰበሰብ የምንጠቀምበት ቅጂ እንዲኖረን ጽሑፉን በእጃችን እንገለብጥ ነበር።

አንድ ቀን በድብቅ እያጠናን ሳለ ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች አንዱ አገኘን፤ በመሆኑም ጽሑፎቻችንን ወሰደብን። ከዚያም ወደ እስር ቤቱ ምክትል አስተዳዳሪ ተጠራን፤ በዚህ ጊዜ የእስር ቤት ቆይታችን እንደሚራዘም ጠብቀን ነበር። ሆኖም የእስር ቤቱ ምክትል አስተዳዳሪ እንዲህ አለን፦ “እናንተ ማን እንደሆናችሁ እናውቃለን እንዲሁም ያላችሁን አቋም እናከብራለን፤ እናምናችኋለን። ወደ ሥራችሁ ተመለሱ።” እንዲያውም ምክትል አስተዳዳሪው ለአንዳንዶቻችን ቀለል ያለ ሥራ ሰጠን። በዚህ ጊዜ ይሖዋን ከልባችን አመሰገንን። በእስር ላይ ሆነንም እንኳ ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን ለይሖዋ ውዳሴ አምጥቷል።

ከአቋማችን ፍንክች አለማለታችን ሌሎች ጥሩ ውጤቶችም እንዲገኙ አስችሏል። የሒሳብ ፕሮፌሰር የነበረ አንድ እስረኛ መልካም ምግባራችንን ካስተዋለ በኋላ ስለ እምነታችን ጠየቀን። በ1951 መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ከእስር ስንለቀቅ እሱም ተፈታ። ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው የተጠመቀ ሲሆን የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኗል።

አሁንም ወታደር ነኝ

ከባለቤቴ ከጃኔት ጋር

ከእስር ከተለቀቅኩ በኋላ በካሪትዛ ወዳሉት ቤተሰቦቼ ተመለስኩ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከሌሎች በርካታ የአካባቢያችን ሰዎች ጋር ሆነን ወደ ሜልበርን፣ አውስትራሊያ ሄድን። በዚያም ጃኔት ከተባለች ጥሩ ክርስቲያን ጋር የተዋወቅኩ ሲሆን ትዳር መሠረትን፤ አንድ ወንድና ሦስት ሴቶች ልጆቻችን የክርስትናን ጎዳና እንዲከተሉ መርዳት ችለናል።

አሁን ከ90 ዓመት በላይ ቢሆነኝም የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ አገለግላለሁ። ቀደም ሲል በደረሰብኝ ጉዳት የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በተለይ ደግሞ በስብከቱ ሥራ ተካፍዬ ስመለስ የተወሰኑ የሰውነቴን ክፍሎችና እግሬን ያመኛል። ይሁንና አሁንም ቢሆን ‘የክርስቶስ ወታደር’ ሆኜ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ።—2 ጢሞ. 2:3