በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዘሌዋውያን 19:16 ላይ የሚገኘው “በባልንጀራህ ሕይወት ላይ አትነሳ” የሚለው ትእዛዝ ምን ትርጉም አለው? እኛስ ከዚህ ጥቅስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ይሖዋ እስራኤላውያንን ቅዱስ ሕዝብ እንዲሆኑ አሳስቧቸው ነበር። ይህን ማድረግ እንዲችሉም የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷቸዋል፦ “በሕዝብህ መካከል እየዞርክ ስም አታጥፋ። በባልንጀራህ ሕይወት ላይ አትነሳ። እኔ ይሖዋ ነኝ።”—ዘሌ. 19:2, 16

“አትነሳ” የሚለው ቃል እዚህ ቦታ ላይ የሚገኘውን የዕብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። ይሁንና ይህ አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? የዘሌዋውያን መጽሐፍን የሚያብራራ አንድ የአይሁዳውያን የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ይህን የጥቅሱን ክፍል ማብራራት ያስቸግራል፤ ምክንያቱም የዕብራይስጡ ፈሊጣዊ አነጋገር ያለውን ትክክለኛ ትርጉም ማወቅ አስቸጋሪ ነው፤ ይህ አገላለጽ ቃል በቃል ቢፈታ ‘[በባልንጀራህ ሕይወት] ላይ፣ አጠገብ፣ አቅራቢያ አትቁም’ ማለት ነው።”

አንዳንድ ምሁራን ይህ ሐሳብ ከቁጥር 15 ጋር ተዛማጅነት እንዳለው ያስባሉ፤ ጥቅሱ “ፍርድ አታዛቡ። ለድሃው አታዳላ ወይም ባለጸጋውን ከሌሎች አስበልጠህ አትመልከት። ለባልንጀራህ ፍትሐዊ ፍርድ ፍረድ” ይላል። (ዘሌ. 19:15) እነዚህ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ፣ በቁጥር 16 ላይ የሚገኘው ‘በባልንጀራህ ላይ አትነሳ’ የሚለው ሐሳብ የአምላክ ሕዝቦች ከፍርድ ጉዳዮች፣ ከንግድ እንቅስቃሴዎች ወይም ከቤተሰባቸው ጋር በተያያዘ ፍትሕን ማጓደል እንደሌለባቸው የሚገልጽ ነው ማለት ነው፤ በተጨማሪም አንድ እስራኤላዊ ጥቅም ለማግኘት ሲል ሐቀኝነት የጎደለው ነገር ከማድረግ መቆጠብ እንዳለበት የሚጠቁም ነው። እነዚህን ነገሮች ማድረግ እንደሌለብን ጥያቄ የለውም። ይሁንና በቁጥር 16 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ይበልጥ አሳማኝ የሆነ ሌላ ማብራሪያ ሊኖረው ይችላል።

በቁጥር 16 መጀመሪያ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እስቲ እንመልከት። አምላክ፣ እየዞሩ ስም እንዳያጠፉ ሕዝቡን አዟቸው ነበር። ስም ማጥፋት ከሐሜት የከፋ እንደሆነ እናስታውስ፤ እርግጥ ነው፣ ሐሜትም ቢሆን ጉዳት አለው። (ምሳሌ 10:19፤ መክ. 10:12-14፤ 1 ጢሞ. 5:11-15፤ ያዕ. 3:6) ስም አጥፊ የሚባለው ግን የሌላውን ሰው መልካም ስም ለማበላሸት ሲል ሆን ብሎ ውሸት የሚናገር ሰው ነው። ስም አጥፊ የሆነ ሰው የሌላን ሰው ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል እያወቀም እንኳ የሐሰት ምሥክርነት ይሰጥ ይሆናል። ስም አጥፊ የሆኑ ሰዎች በናቡቴ ላይ በሐሰት እንደመሠከሩበት እናስታውሳለን፤ በዚህም የተነሳ ናቡቴ ያለጥፋቱ በድንጋይ ተወግሮ ተገድሏል። (1 ነገ. 21:8-13) በእርግጥም በዘሌዋውያን 19:16 ላይ እንደተገለጸው፣ ስም አጥፊ የሆነ ሰው በባልንጀራው ሕይወት ላይ ተነስቷል ሊባል ይችላል።

ከዚህም ሌላ አንድ ሰው የሌላውን ሰው ስም ማጥፋቱ ግለሰቡን እንደሚጠላው የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። አንደኛ ዮሐንስ 3:15 እንዲህ ይላል፦ “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሁሉ ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።” አምላክ በቁጥር 16 ላይ የሚገኘውን መመሪያ ከሰጠ በኋላ በቀጣዩ ቁጥር ላይ “ወንድምህን በልብህ አትጥላው” በማለት መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው።—ዘሌ. 19:17

ከዚህ አንጻር፣ በዘሌዋውያን 19:16 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ለክርስቲያኖች ጠንከር ያለ ምክር የያዘ ነው። ስለ ሌላ ሰው መጥፎ ነገር ከማሰብ ወይም ስሙን ከማጥፋት መቆጠብ አለብን። አንድ ሰው ደስ ስለማይለን ወይም በምቀኝነት ተነሳስተን ስሙን በማጥፋት በእሱ ላይ ‘ከተነሳን’ ይህ ግለሰቡን እንደምንጠላው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ክርስቲያኖች ማንንም ላለመጥላት በጣም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።—ማቴ. 12:36, 37