በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስታ የሚያስገኝ መንገድ

ዓላማ ያለው ሕይወት

ዓላማ ያለው ሕይወት

የሰው ልጆች በብዙ መንገዶች ከሌሎች ፍጥረታት የተለዩ ናቸው፤ መጻፍ፣ ሥዕል መሣልና መፍጠር የሚችሉ ከመሆኑም ሌላ ሕይወትን በተመለከተ አስፈላጊ ጥያቄዎችን ያነሳሉ። ከእነዚህ መካከል ‘አጽናፈ ዓለም የኖረው ለምንድን ነው? የሰው ልጆች ወደ ሕልውና የመጡት እንዴት ነው? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣል?’ የሚሉት ጥያቄዎች ይገኙበታል።

አንዳንድ ሰዎች እነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንደማይገኝላቸው በማሰብ ጥያቄዎቹን ከማንሳት ወደኋላ ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ሕይወት የተገኘው የማሰብ ችሎታ ባለው አካል ሳይሆን በዝግመተ ለውጥ ስለሆነ እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳት ምንም ጥቅም እንደሌለው ይሰማቸዋል። የታሪክና የሥነ ሕይወት ፕሮፌሰር የሆኑት ዊሊያም ፕሮቪን “አምላክ የሚባል ነገር ስለሌለ ሕይወት ዓላማ የለውም” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “የሥነ ምግባር ሕጎችን ለማውጣት የሚያስችል ፍጹም የሆነ መሠረት የለም፤ በተጨማሪም ሕይወት ይህ ነው የሚባል ዓላማ የለውም” ብለዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ያለው አደገኛ አመለካከት ተቀባይነት እንደሌለው ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች አጽናፈ ዓለም ዝንፍ በማይሉ አስደናቂ የሒሳብ ሕጎች እንደሚመራ ተገንዝበዋል። በተጨማሪም በተፈጥሮ ውስጥ አስገራሚ ንድፎች እንደሚታዩና ሰዎች እነዚህን ንድፎች በመኮረጅ አንዳንድ ነገሮችን ለመሥራት እንደሚሞክሩ አስተውለዋል። ደግሞም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከሚያዩት ነገር በመነሳት እነዚህ ውስብስብና ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡ ንድፎች በዘፈቀደ በሚንቀሳቀስ ኃይል ሊገኙ እንደማይችሉ ከዚህ ይልቅ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንደፈጠራቸው ደምድመዋል።

አንዳንድ የዝግመተ ለውጥ አማኞች እነዚህን ማስረጃዎች በማየታቸው አመለካከታቸውን መለስ ብለው ለማጤን ተነሳስተዋል። ቀጥሎ የቀረቡትን ሁለት ምሳሌዎች ተመልከት።

የነርቭ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሆነው ዶክተር አሌክሴ ማርኖቭ። ዶክተር አሌክሴ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የተማርኩባቸው ትምህርት ቤቶች አምላክ የለሽነትንና ዝግመተ ለውጥን ያስተምሩ ነበር። በአምላክ መኖር የሚያምን ሁሉ መሃይም እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።” ከ1990 በኋላ ግን አሌክሴ አመለካከቱ መለወጥ ጀመረ።

እንዲህ ብሏል፦ “አንጎላችንን ጨምሮ ከማንኛውም ነገር ጋር በተያያዘ አሳማኝ የሆነ ማብራሪያ ለማግኘት ጥረት አደርግ ነበር። አስደናቂ የሆነው ይህ የሰውነታችን ክፍል በአጽናፈ ዓለም ውስጥ እስካሁን ከምናውቃቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ ውስብስቡ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሆኖም ይህን የመሰለ አንጎል የኖረን ለተወሰነ ጊዜ ያህል እውቀት ከቀሰምንና ችሎታ ካዳበርን በኋላ እንድንሞት ነው? ይህ ለእኔ ትርጉም የማይሰጥና አሳማኝ ያልሆነ ነገር ነበር። ስለዚህ ‘ወደ ሕልውና የመጣነው ለምንድን ነው? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ። ጉዳዩን በቁም ነገር ካሰብኩበት በኋላ ‘ፈጣሪ መኖር አለበት’ የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ።”

አሌክሴ የሕይወትን ትርጉም ለማግኘት ባደረገው ጥረት መጽሐፍ ቅዱስን መማር ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ፣ ሐኪም የሆነችውና ልክ እንደ እሱ በአምላክ መኖር የማታምን የነበረችው ባለቤቱም መጽሐፍ ቅዱስን መማር ጀመረች፤ እርግጥ መጀመሪያ ላይ ዓላማዋ ባለቤቷ እንደተሳሳተ ማሳመን ነበር! በአሁኑ ጊዜ ግን ሁለቱም የአምላክን መኖር ፈጽሞ አይጠራጠሩም፤ እንዲሁም አምላክ ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተረድተዋል።

ሳይንቲስት የሆነችው ዶክተር ሁዋቢ ኢን። ሁዋቢ ኢን ፊዚክስ ያጠናች ሲሆን ለብዙ ዓመታት ስለ ፀሐይ ምርምር አድርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “ሳይንቲስቶች ተፈጥሯዊ ክስተቶችን ሲያጠኑ ሁሉም ነገር አስደናቂ በሆነ መንገድ እንደተደራጀ ይገነዘባሉ፤ ይህ ደግሞ ዝንፍ የማይሉ ሕጎች መኖራቸው ያስገኘው ውጤት ነው። ‘እነዚህ ሕጎች ሊኖሩ የቻሉት እንዴት ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። ‘ምግብ ለማብሰል የምንጠቀምበት ትንሽ እሳት እንኳ ቁጥጥር ሊደረግለት ይገባል፤ ታዲያ የፀሐይን ኃይል የሚቆጣጠሩትን ሕጎች ያወጣው ማን ነው?’ ከጊዜ በኋላ እንደተገነዘብኩት ለዚህ ጥያቄ በጣም አሳማኝ የሆነው መልስ ‘በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ’ የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ነው።”—ዘፍጥረት 1:1

እርግጥ ነው፣ ሳይንስ ‘የአንጎል ሴሎች የሚሠሩት እንዴት ነው? ፀሐይ ሙቀትና ብርሃን የምታመነጨው እንዴት ነው?’ እንደሚሉት ላሉ በርካታ ጥያቄዎች ማብራሪያ እንደሚሰጥ አይካድም። ይሁን እንጂ አሌክሴም ሆነ ሁዋቢ ከጊዜ በኋላ እንደተገነዘቡት “እንዴት” ከሚለው ይበልጥ አስፈላጊ ለሆነው ጥያቄ ማለትም “ለምን” ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አጽናፈ ዓለም የኖረው ለምንድን ነው? በሕግ የሚመራው ለምንድን ነው? የሰው ልጆች ወደ ሕልውና የመጡት ለምንድን ነው?’ እንደሚሉት ላሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን አስመልክቶ ሲናገር ‘አምላክ መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ አልፈጠራትም’ ይላል። (ኢሳይያስ 45:18) አዎን፣ አምላክ ምድርን የፈጠራት በዓላማ ነው፤ ደግሞም በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ይህ ዓላማ ከወደፊቱ ተስፋችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።