በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ወጣቶች

የጀብደኝነት ድርጊት መፈጸም ምን ጉዳት አለው?

የጀብደኝነት ድርጊት መፈጸም ምን ጉዳት አለው?

ተፈታታኙ ነገር

“በዋሻ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየከነፈ ወደሚያልፍ ባቡር በጣም ተጠግቼ እቆም ነበር። ሰውነቴ አድሬናሊን የተባለውን ሆርሞን ሲረጭ የተሰማኝ ስሜት ችግሮቼን ያስረሳኛል።”—ሊየን *

“ከረጅም ቋጥኝ ቁልቁል ተወርውሬ ውኃ ውስጥ ስገባ፣ ለጥቂት ሴኮንዶች ያህል ከሁሉ ነገር እንደተገላገልኩ ሆኖ ይሰማኛል። ይህን ማድረግ በአብዛኛው ቢያስደስተኝም አንዳንድ ጊዜ ግን በጣም ያስፈራኛል።”—ላሪሳ

እንደ ሊየንና ላሪሳ ሁሉ በርካታ ወጣቶች አደገኛ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ አቅማቸውን የሚፈትን ድርጊት መፈጸም ያስደስታቸዋል፤ አንዳንድ ጊዜ ይህን የሚያደርጉት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነው። አንተስ እንዲህ ለማድረግ ትፈተናለህ? ከሆነ ይህን ርዕስ ማንበብህ ሊጠቅምህ ይችላል።

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

የጀብደኝነት ድርጊት በመፈጸም ደስታ ለማግኘት መሞከር ሱስ ሊሆንብህ ይችላል። እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ለአጭር ጊዜ ያህል ከፍተኛ የደስታ ስሜት ቢፈጥሩብህም፣ ብዙም ሳይቆይ ከዚያ የበለጠ የደስታ ስሜት የሚፈጥር ነገር ለመፈጸም እንድትጓጓ ያደርጉሃል። እንደ ሊየን ዓይነት የጀብደኝነት ድርጊት ይፈጽም የነበረው ማርኮ እንዲህ ብሏል፦ “መውጫ የሌለው እሽክርክሪት ውስጥ እንደ መግባት ነው። ለቅጽበት ያህል ደስ ቢለኝም እንደዚያ ዓይነት ሌላ ድርጊት የመፈጸም ፍላጎት ይቀሰቀስብኛል።”

ባለ ጎማ ጫማ በማድረግ፣ በከፍተኛ ፍጥነት የሚበርሩ መኪኖችን ይዞ የመጓዝ ልማድ ያለው ጀስቲን እንዲህ ይላል፦ “የሚሰማኝ የደስታ ስሜት፣ ድርጊቱን ደግሜ ደጋግሜ እንድፈጽመው ያነሳሳኝ ነበር። ዓላማዬ የሰዎችን አድናቆት ማትረፍ ነበር፤ መጨረሻዬ ግን ሆስፒታል ሆነ።”

የእኩዮች ተጽዕኖ፣ በጤናማ አእምሮህ የማታደርገውን ነገር እንድትፈጽም ሊያነሳሳህ ይችላል። ማርቪን የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ጓደኞቼ፣ ምንም ዓይነት መሣሪያ ሳልጠቀም ረጅም ሕንፃ ላይ እንድወጣ ገፋፉኝ። ‘አይዞህ፣ ሞክረው’ አሉኝ። በጣም ፈራሁ። ሕንፃው ላይ መውጣት ስጀምር በፍርሃት እየተንቀጠቀጥኩ ነበር።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ላሪሳም “ሌሎች ያደረጉትን ሁሉ አደርግ ነበር። ቆም ብዬ አላስብም ነበር” ብላለች።

አንዳንዶች፣ አደገኛ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን የሚያወድሱና ድርጊቱ እምብዛም አደገኛ እንዳልሆነ የሚያስመስሉ ነገሮችን ኢንተርኔት ላይ በማውጣትም በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እንዲያውም በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚወጡ አንዳንድ የጀብደኝነት ድርጊቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ተመልካች ማግኘታቸው፣ ድርጊቱን የሚፈጽሙት ሰዎች እውቅናና ትኩረት እንዲሰጣቸው አድርጓል።

ለምሳሌ በአንዳንድ የታወቁ ቪዲዮዎች ላይ ሰዎች ፓኩዎ በመባል በሚታወቀው እንቅስቃሴ ሲካፈሉ ይታያሉ፤ ሰዎቹ ምንም ዓይነት መከላከያ ሳያደርጉ እንደ አጥር፣ ቤትና ደረጃ ያሉትን ነገሮች ያለምንም ችግር በሩጫ፣ በመንጠላጠል አሊያም በዝላይ በፍጥነት ሲሻገሩ ይታያል። እነዚህን ቪዲዮዎች ስትመለከት (1) ድርጊቱ ያን ያህል አደገኛ እንዳልሆነ እንዲሁም (2) ሁሉም ሰው የሚያደርገው ነገር እንደሆነ በማሰብ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለህ። በዚህም የተነሳ፣ ሕይወትህን አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎችን ለመሞከር ትፈተን ይሆናል።

አቅምህን ለመፈተን የሚያስችሉ የተሻሉና ለአደጋ የማያጋልጡ መንገዶች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ያም ሆኖ “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዝ እንዳለብንም ይናገራል። (ቲቶ 2:12) እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ምን ማድረግ ትችላለህ?

አደጋውን ገምግም። መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ ሰው ተግባሩን በእውቀት ያከናውናል፤ ሞኝ ሰው ግን የገዛ ራሱን ሞኝነት ይገልጣል” ይላል። (ምሳሌ 13:16) በአንድ ድርጊት ለመካፈል ከማሰብህ በፊት፣ ስለሚያስከትላቸው አደጋዎች ለማወቅ ሞክር። ‘በዚህ እንቅስቃሴ ብካፈል ራሴን ለከባድ አደጋ ወይም ለሞት አጋልጣለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 14:15

ለሕይወት አክብሮት የሚያሳዩ ጓደኞች ያዝ። እውነተኛ ወዳጆች ራስህን አደጋ ላይ እንድትጥል ወይም የማትፈልገውን ነገር እንድታደርግ ለመገፋፋት አይሞክሩም። ላሪሳ እንዲህ ብላለች፦ “ኃላፊነት የሚሰማቸው ጥሩ ጓደኞች ያዝኩ፤ እነሱም የምካፈልባቸውን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ የተሻለ ምርጫ እንዳደርግ ረዱኝ። ጓደኞቼን ስለውጥ ሕይወቴም ተለወጠ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 13:20

‘በዚህ እንቅስቃሴ ብካፈል ራሴን ለከባድ አደጋ ወይም ለሞት አጋልጣለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ

ሕይወትህን አደጋ ላይ ሳትጥል የሚያስደስቱህን ነገሮች ማድረግ ትችላለህ። አዶለሰንት ሪስክ ቢሄቭየርስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው እድገት ማድረግ “የምትከተላቸውን መመሪያዎች ማውጣትንና ለራስህ ገደብ ማበጀትን” ይጨምራል። አቅምህን መፈተን ከፈለግህ፣ አደጋ በማያስከትል ሁኔታ ውስጥ ሆነህ አስፈላጊውን የአደጋ መከላከያ መሣሪያ በመጠቀም ይህን ማድረግ ትችላለህ።

ለራስህ አክብሮት ይኑርህ። ሰዎች ለአንተ አክብሮት እንዲኖራቸው የሚያደርገው፣ በገሃዱ ዓለም የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች የምትወጣበት መንገድ እንጂ የጀብደኝነት ድርጊቶች መፈጸምህ አይደለም። ላሪሳ እንዲህ ብላለች፦ “ከወሰድኳቸው ሕይወቴን የሚያበላሹ እርምጃዎች መካከል፣ ከቋጥኝ ላይ ቁልቁል መወርወር የመጀመሪያው ብቻ ነበር። የሌሎችን ተጽዕኖ መቋቋምን ተምሬ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ይሆን ነበር።”

ዋናው ነጥብ፦ የጀብደኝነት ድርጊቶችን በመፈጸም ሳያስፈልግ ራስህን አደጋ ላይ ከመጣል ይልቅ በመዝናኛ ረገድ ማስተዋል የተንጸባረቀበት ምርጫ አድርግ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 15:24

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።