በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የዛጎል ቅርጽ

የዛጎል ቅርጽ

ሞለስክ በመባል ከሚታወቁት የባሕር ፍጥረታት አብዛኞቹ ሰውነታቸውን የሚሸፍኑበት ዛጎል አላቸው፤ ይህ ዛጎል በባሕሩ ወለል አካባቢ ያለውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። መሐንዲሶች፣ ዛጎሎች እነዚህን ፍጥረታት ምን ያህል ከአደጋ እንደሚከላከሉላቸው ሲመለከቱ፣ ተሳፋሪዎችን ወይም ነዋሪዎችን ከማንኛውም አደጋ ሊጋርዱ የሚችሉ ተሽከርካሪዎችንና ሕንፃዎችን ለመሥራት በማሰብ የዛጎሎችን ቅርጽና አሠራር ማጥናት ጀምረዋል።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ መሐንዲሶች ባይቫልቭ (ለሁለት የሚከፈሉ) እና ስፓይራል (ጥምዝምዝ ቅርጽ ያላቸው) በሚባሉት ሁለት የዛጎል ዓይነቶች ላይ ጥናት አካሄዱ።

ባይቫልቭ የሚባሉት የዛጎል ዓይነቶች በውጭ በኩል ሸንተረሮች አሏቸው፤ እነዚህ ሸንተረሮች በዛጎሉ ላይ የሚያርፈው ጫና ወደ መገጣጠሚያውና ወደ ጠርዙ እንዲሄድ ያደርጋሉ። ስፓይራል የሚባሉት የዛጎል ዓይነቶች ደግሞ ጎበጥ ያለ ቅርጽ አላቸው፤ ይህም በዛጎሉ ላይ የሚያርፈው ጫና፣ ወደ ዛጎሉ ጫፍና ጫፍ እንዲሄድ ያደርጋል። ሁለቱም የዛጎል ዓይነቶች ያላቸው ቅርጽ፣ የሚደርስባቸው ጫና ጠንካራ ወደሆነው ክፍል እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችል ነው፤ ይህም አደጋ በሚመጣበት ጊዜ በዛጎሉ ውስጥ ባለው ፍጥረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በጣም ይቀንሰዋል።

በተጨማሪም ተመራማሪዎች እውነተኛ ዛጎሎችን፣ የዛጎልን ቅርጽና አሠራር በመኮረጅ በ3ዲ ፕሪንተሮች ልሙጥ አድርገው ከሠሯቸው ነገሮች ጋር አነጻጽረዋል። ውጤቱ ምን ሆነ? የተፈጥሮ ዛጎሎች በውጭ በኩል ያላቸው ቅርጽና አሠራር፣ ልሙጥ ተደርገው ከተሠሩት ሰው ሠራሽ ዛጎል መሰል ነገሮች በእጥፍ ገደማ የሚበልጥ ጫና የመቋቋም አቅም እንዲኖራቸው አድርጓል።

ሳይንቲፊክ አሜሪካን የዚህ ጥናት ግኝት ስለሚኖረው ጠቀሜታ ሲናገር “የዛጎል ቅርጽ ያለው መኪና መንዳት ላይ ከደረስን፣ በጣም የሚያምርና ሰውነታችን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከለላ የሚሆን መኪና ይኖረናል” ብሏል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የዛጎል ቅርጽ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?