በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ​—ክፍል 5

ግሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ​—ክፍል 5

ይህ ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተገለጹትን ሰባት የዓለም ኃያላን መንግሥታት በተመለከተ “በንቁ!” ላይ ከሚወጡት ሰባት ተከታታይ ርዕሶች መካከል አምስተኛው ነው። ዓላማውም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበትና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ እንዲሁም ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት እንደያዘ ማሳየት ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ፣ ጭካኔ የተሞላበት የሰው ልጆች አገዛዝ ያስከተለው መከራና ሥቃይ እንደሚያከትም ይገልጻል።

በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እስክንድር የተባለ አንድ የመቄዶንያ ወጣት ግሪክ * በዓለም መድረክ ጎልታ እንድትታይ አደረገ። እንዲያውም ግሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ አምስተኛዋ የዓለም ኃያል መንግሥት እንድትሆን ማድረግ የቻለ ሲሆን እሱ ራሱም ከጊዜ በኋላ ታላቁ እስክንድር ተብሎ ተጠርቷል። ከግሪክ በፊት የነበሩት ኃያላን መንግሥታት ግብፅ፣ አሦር፣ ባቢሎንና ሜዶ ፋርስ ናቸው።

እስክንድር ከሞተ በኋላ ግዛቱ የተፈረካከሰ ሲሆን ኃይሉም እየተዳከመ ሄደ። ይሁን እንጂ ግሪክ ከባሕል፣ ከቋንቋ፣ ከሃይማኖትና ከፍልስፍና አንጻር ያሳደረችው ተጽዕኖ ፖለቲካዊው ግዛት ከወደቀ ከረጅም ጊዜ በኋላም አልጠፋም።

እምነት የሚጣልበት ታሪክ

ግሪክ የዓለም ኃያል መንግሥት በነበረችበት ዘመን ያገለገሉ የአምላክ ነቢያት እንደነበሩ የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ አናገኝም፤ በዚያ ወቅት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም የለም። ያም ቢሆን ግሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተመዘገቡ ትንቢቶች ላይ ተጠቅሳለች። በተጨማሪም በተለምዶ አዲስ ኪዳን የሚባሉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ግሪክ ስለነበራት ተጽዕኖ በተደጋጋሚ ጊዜ ጠቅሰዋል። ለምሳሌ በእስራኤል አገር ዲካፖሊስ የሚባሉ አሥር የግሪካውያን ከተሞች ነበሩ፤ ይህ የግሪክኛ ቃል “አሥሩ ከተሞች” የሚል ትርጉም አለው። (ማቴዎስ 4:25፤ ማርቆስ 5:20፤ 7:31) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አካባቢ በርካታ ጊዜ የሚጠቅሰው ሲሆን ዓለማዊ ታሪክ እንዲሁም የቲያትሮች፣ የአምፊቲያትሮች፣ የቤተ መቅደሶችና የመታጠቢያ ቦታዎች ፍርስራሾች እነዚህ ከተሞች በእርግጥ እንደነበሩ ያረጋግጣሉ።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በተለይ ሐኪሙ ሉቃስ በጻፈው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ግሪካውያን ባሕልና ሃይማኖት ብዙ ጊዜ ይጠቅሳል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፦

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በ50 ዓ.ም. አካባቢ አቴናን ሲጎበኝ ስላጋጠመው ሁኔታ ሲገልጽ ከተማዋ “በጣዖት የተሞላች” እንደነበረች ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 17:16) አቴና እና በዙሪያዋ የነበሩ ቦታዎች በሃይማኖታዊ ምስሎችና እንደ ቅዱስ ተደርገው በሚታዩ ስፍራዎች የተሞሉ እንደነበሩ ታሪካዊ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

የሐዋርያት ሥራ 17:21 “የአቴና ሰዎችና ወደዚያ የመጡ የውጭ አገር ሰዎች ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት ብቻ ነበር” ይላል። የቱሲዲዲስና የዲማስተኒዝ ጽሑፎች አቴናውያን ለውይይትና ለክርክር ከፍተኛ ቦታ ይሰጡ እንደነበር ይናገራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ “ከኤፊቆሮስና ከኢስጦይክ ፈላስፎች መካከል አንዳንዶቹ [ጳውሎስን] ይከራከሩት” እንደነበረና የሚናገረውን ይበልጥ ለመስማት ወደ አርዮስፋጎስ እንደወሰዱት ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 17:18, 19) የአቴና ከተማ ኤፊቆሮሳውያንን እና ኢስጦይኮችን ጨምሮ በብዙ ፈላስፎችዋ የታወቀች ነበረች።

ጳውሎስ “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል ጽሑፍ ስለተቀረጸበት በአቴና የሚገኝ አንድ መሠዊያ ጠቅሷል። (የሐዋርያት ሥራ 17:23) ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሑፍ የተቀረጸባቸውን መሠዊያዎች የሠራቸው የቀርጤሱ ኤፒሜንዲዝ ሳይሆን አይቀርም።

ለማይታወቅ አምላክ የተሠራ መሠዊያ

ጳውሎስ ለአቴናውያን ባቀረበው ንግግር ላይ “እኛም የእሱ ልጆች ነን” የሚለውን አባባል የጠቀሰ ሲሆን ይህንንም የተናገረው አንድ ባለቅኔ ሳይሆን በአቴናውያን “መካከል ያሉ አንዳንድ ባለቅኔዎች” እንደሆኑ ገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 17:28) ግሪካውያኑ ባለቅኔዎች ኧራተስ እና ክሊያንቲዝ ሳይሆኑ አይቀሩም።

አንድ ምሑር “ጳውሎስ በአቴና ስላደረገው ጉብኝት የሚገልጸው ዘገባ የዓይን ምሥክር በሆነ ሰው የተጻፈ ይመስላል” ብለው መደምደማቸው በእርግጥም የተገባ ነው። ጳውሎስ በትንሿ እስያ በምትገኘው በኤፌሶን ስላጋጠመው ሁኔታ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባም በተመለከተ ተመሳሳይ ነገር መናገር ይቻላል። በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. በዚህች ከተማ ለግሪካውያን አረማዊ ሃይማኖት በተለይም ለአርጤምስ አምልኮ ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር።

አርጤምስ የተባለችው የኤፌሶን አምላክ ምስል

በጥንት ጊዜ ከተሠሩ የዓለማችን ሰባት አስደናቂ ነገሮች መካከል አንዱ የሆነው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። ለምሳሌ ጳውሎስ በኤፌሶን ያከናወነው አገልግሎት፣ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በመሥራት የደራ ንግድ ያካሂድ የነበረውን ድሜጥሮስ የተባለ ብር አንጥረኛ አስቆጥቶት እንደነበረ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቧል። በቁጣ የገነፈለው ድሜጥሮስ “ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው . . . በእጅ የተሠሩ አማልክት ሁሉ አማልክት አይደሉም እያለ ብዙ ሰዎችን አሳምኖ አመለካከታቸውን [አስለውጧል]” በማለት ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 19:23-28) ከዚያም ድሜጥሮስ ሕዝቡ በቁጣ እንዲሞላ ስላደረገ ብዙ ሰዎች “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር።

በዛሬው ጊዜ የኤፌሶንን ፍርስራሾችም ሆነ የአርጤምስ ቤተ መቅደስ የነበረበትን ቦታ መጎብኘት ትችላለህ። ከዚህም በላይ በኤፌሶን የተገኙ የተቀረጹ ጥንታዊ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ለዚህች አምላክ ጣዖታት ይሠሩ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በኤፌሶን የብር አንጥረኞች ማኅበር ነበር።

እምነት የሚጣልበት ትንቢት

ታላቁ እስክንድር በሕይወት ከኖረበት ዘመን 200 ዓመት ያህል ቀደም ብሎ የይሖዋ አምላክ ነቢይ የነበረው ዳንኤል በዓለም ላይ ስለሚኖሩት ኃያላን መንግሥታት እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “በዐይኖቹ መካከል ትልቅ ቀንድ ያለው አውራ ፍየል፣ መሬት ሳይነካ ምድርን ሁሉ እያቋረጠ በድንገት ከምዕራብ መጣ፤ . . . ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ ተንደርድሮ መጣበት፤ በታላቅ ቍጣም መታው፤ እየወጋውና ሁለቱን ቀንዶቹን እየሰበረ፣ በጭካኔ አውራውን በግ ሲጐዳ አየሁ፤ አውራ በጉም ለመቋቋም ጕልበት አልነበረውም። ፍየሉ በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ . . . ፍየሉም ታላቅ ሆነ፤ ነገር ግን በኀይሉ በበረታ ጊዜ፣ ትልቁ ቀንዱ ተሰበረ፤ በቦታውም ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት የሚያመለክቱ አራት ታላላቅ ቀንዶች በቀሉ።”—ዳንኤል 8:5-8

ይህ ትንቢት የሚያመለክተው ማንን ነው? ዳንኤል ራሱ እንዲህ በማለት መልሱን ሰጥቶናል፦ “ያየኸው ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል። ጠጕራሙ ፍየል የግሪክ ንጉሥ ሲሆን፣ በዐይኖቹም መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያው ንጉሥ ነው።”​—ዳንኤል 8:20-22

እስቲ አስበው! ባቢሎን የዓለም ኃያል መንግሥት በነበረችበት ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ የሚነሱት ኃያላን መንግሥታት ሜዶ ፋርስና ግሪክ እንደሆኑ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ከላይ እንደተጠቀሰው የግሪክ ንጉሥ “በኀይሉ በበረታ ጊዜ፣ ትልቁ ቀንዱ” ማለትም እስክንድር ‘እንደሚሰበር’ እና በሌሎች አራት ግለሰቦች እንደሚተካ እንዲሁም ከእነዚህ መካከል አንዳቸውም የእሱ ዘር እንደማይሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር ተናግሯል።​—ዳንኤል 11:4

ይህ ትንቢት አንዱም ሳይቀር ተፈጽሟል። እስክንድር በ336 ዓ.ዓ. ንጉሥ ሆነ፤ ከዚያም በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ኃያሉን የፋርስ ንጉሥ ሳልሳዊ ዳርዮስን ድል አደረገ። እስክንድር በ323 ዓ.ዓ. በ32 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በቀጣዮቹ ዓመታት ግዛቱን ማስፋፋቱን ተያይዞት ነበር። ከእስክንድር በኋላ የእሱን ያህል ግዛቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የቻለ ገዥ አልተነሳም፤ በእሱ ምትክ ሥልጣን የያዙትም ዘሮቹ አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ ላይሲመከስ፣ ካሳንደር፣ ሰሉከስና ቶሌሚ የተባሉት አራቱ ዋና ዋና ጄኔራሎቹ “ራሳቸውን ነገሥታት በማድረግ” ግዛቱን እንደተከፋፈሉት ዘ ሄለንስቲክ ኤጅ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል።

እስክንድር ግዛቱን በሚያስፋፋበት ወቅት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችንም ፈጽሟል። ለምሳሌ ያህል፣ በሰባተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖሩት ሕዝቅኤልና ዘካርያስ የተባሉ ነቢያት የጢሮስ ከተማ እንደምትጠፋ አስቀድመው ተናግረዋል። (ሕዝቅኤል 26:3-5, 12፤ 27:32-36፤ ዘካርያስ 9:3, 4) ሕዝቅኤል የከተማዋ ድንጋይና የግንቦች ፍርስራሽ “ወደ ባሕር [እንደሚጣል]” ጭምር ጽፎ ነበር። ታዲያ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል?

የእስክንድር ሠራዊት በ332 ዓ.ዓ. ጢሮስን በወረረበት ወቅት ምን እንዳደረገ እንመልከት። ወታደሮቹ በየብስ ላይ ትገኝ የነበረችውን የጢሮስ ከተማ ፍርስራሽ ባሕሩ ውስጥ በመደልደል በደሴት ላይ ወደምትገኘው የከተማዋ ክፍል የሚወስድ መተላለፊያ ሠሩ። ይህ የጦርነት ስልት ውጤታማ በመሆኑ ጢሮስን ድል አደረጓት። ይህን አካባቢ በ19ኛው መቶ ዘመን የጎበኘ አንድ ሰው “በጢሮስ ላይ የተነገሩት ትንቢቶች አንድም ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ተፈጽመዋል” በማለት ተናግሯል። *

እምነት ልትጥልበት የምትችል ተስፋ

እስክንድር ያካሄደው ዘመቻ፣ ዓለም ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ እንዲሆን አላደረገም። አንድ ምሑር ስለ ጥንቷ ግሪክ የግዛት ዘመን ከመረመሩ በኋላ “በተራው ሕዝብ ሕይወት ላይ ያን ያህል ለውጥ አልታየም” በማለት ተናግረዋል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በተደጋጋሚ ጊዜ የታየ ከመሆኑም ሌላ “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ነው።​—መክብብ 8:9

ይሁንና አምላክ፣ የሰው ልጅ ከሚያስበው ከማንኛውም መስተዳድር የላቀ መንግሥት ስላቋቋመ መጥፎ አገዛዝ ለዘላለም አይቀጥልም። የአምላክ መንግሥት ተብሎ የሚጠራው ይህ መስተዳድር ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ የሚያስወግድ ሲሆን ተገዥዎቹ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት እንዲያገኙ ያደርጋል።​—ኢሳይያስ 25:6፤ 65:21, 22፤ ዳንኤል 2:35, 44፤ ራእይ 11:15

የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። የሥልጣን ጥመኛ ከሆኑትና ለሰዎች ከማያስቡት ሰብዓዊ ገዥዎች በተቃራኒ ኢየሱስ ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር አለው። ኢየሱስን በተመለከተ አንድ መዝሙራዊ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል፦ “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል።”​—መዝሙር 72:12-14

በእንዲህ ዓይነት ንጉሥ አገዛዝ ሥር መኖር ትፈልጋለህ? ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ስድስተኛ ስለሆነው የዓለም ኃያል መንግሥት ይኸውም ስለ ሮም መመርመር ያስፈልግሃል። ደግሞም አስቀድሞ የተነገረለት አዳኝ የተወለደውና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የማይፋቅ አሻራ ትቶ ያለፈው በሮም አገዛዝ ወቅት ነበር። በዚህ መጽሔት ቀጣይ እትም ላይ የሚወጣውን የእነዚህን ተከታታይ ርዕሶች ስድስተኛ ክፍል እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ግሪክ የሚገልጹት ሐሳቦች ከመጀመሪያው መቶ ዘመን በፊት የነበረችውን የጥንቷን ግሪክ የሚያመለክቱ ናቸው፤ በዘመናችን ካሉት ብሔራዊ ድንበሮች ጋር የሚያያዙ አይደሉም።

^ አን.23 ሕዝቅኤል አስቀድሞ እንደተናገረው ጢሮስን መጀመሪያ ድል ያደረጋት የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ነበር። (ሕዝቅኤል 26:7) ከዚያ በኋላ ከተማዋ እንደገና ተገነባች። እስክንድር ድል ያደረገው እንደገና የተሠራችውን ይህችን ከተማ ሲሆን በዚህም ነቢያቱ የተናገሩት ትንቢት አንድም ሳይቀር እንዲፈጸም አድርጓል።