በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰላማዊ መሆን ትችላለህ

ሰላማዊ መሆን ትችላለህ

ሰላማዊ መሆን ትችላለህ

በተፈጥሯችን መጥፎ ነገር የማድረግ ዝንባሌ ቢኖረንም በአብዛኛው አንድ ሰው የዓመፀኝነት ባሕርይ የሚያንጸባርቀው ከሌሎች በመማር ነው። ሰላማዊ መሆንን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ ሰላማዊ መሆን የምንችልበትን መንገድ ማን ሊያስተምረን ይችላል? እውነተኛውን ሰላም ለማስተማር ከማንም በላይ ብቃት ያለው በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለው ፈጣሪያችን እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ቀጥሎ የተጠቀሱትን አምስት ነጥቦችና በእነዚህ ሥር የቀረቡትን ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኙ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውን እንደ ዕንቁ ያሉ ምክሮች ተመልከት።

1 “በክፉ ሰው አትቅና።” (ምሳሌ 3:31) አንድ ሰው እውነተኛ ጥንካሬ አለው የሚባለው እንደ ራስ መግዛትና ገርነት ያሉ ባሕርያትን ሲያዳብር ነው። ምሳሌ 16:32 “ታጋሽ ሰው ከጦረኛ . . . ይበልጣል” ይላል። አንድ ጠንካራ ግድብ ውኃን አግዶ እንደሚይዝ ሁሉ ታጋሽ ሰውም የሚያስቆጡ ነገሮች ሲያጋጥሙት ስሜቱን መቆጣጠር ይችላል። እንዲያውም በዚህ ጊዜ ሁኔታውን የሚይዘው በገርነት ስለሆነ “ቍጣን ያበርዳል።” (ምሳሌ 15:1) በቀላሉ የሚቆጣ ሰው ግን ትንሽ ነገር ይበቃዋል።​—ምሳሌ 25:28

2 አብረሃቸው የምትውላቸውን ሰዎች በጥበብ ምረጥ። ምሳሌ 16:29 “ክፉ ሰው ባልንጀራውን ያባብለዋል” ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል።” (ምሳሌ 13:20) አዎን፣ ራሳቸውን ከሚገዙና የገርነት መንፈስ ካላቸው ሰላማዊ ሰዎች ጋር የምንውል ከሆነ እነሱን ለመምሰል መጣራችን አይቀርም።

3 ለሌሎች እውነተኛ ፍቅር አዳብር። ስለ ፍቅር ከተጻፉት መግለጫዎች ሁሉ የሚልቀው በ⁠1 ቆሮንቶስ 13:4-7 ላይ የሚገኘው ነው። ጥቅሱ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። . . . አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም። . . . ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ . . . ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።” የአምላክ ዓይነት ፍቅር ካለን ጠላታችንን ጭምር እንደምንወድ ኢየሱስ ተናግሯል።​—ማቴዎስ 5:44, 45

4 አምላክ መፍትሔ እንደሚሰጥህ እምነት ይኑርህ። “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። . . . ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ’ ተብሎ [ተጽፏል]።” (ሮም 12:17-19) በአምላክና እሱ በሰጠን ተስፋዎች ላይ እምነት የምንጥል ከሆነ እምነት የለሽ የሆኑ ሰዎች ፈጽሞ ሊረዱት የማይችል ውስጣዊ ሰላም እናገኛለን።​—መዝሙር 7:14-16፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7

5 የአምላክ መንግሥት የሚያመጣውን እውነተኛ ሰላም ተስፋ አድርግ። የአምላክ መንግሥት በሰማይ የተቋቋመ መስተዳድር ሲሆን በቅርቡ ክፋትን ሁሉ ጠራርጎ በማጥፋት መላዋን ምድር ይቆጣጠራል። (መዝሙር 37:8-11፤ ዳንኤል 2:44) በዚህ መንግሥት ሥር “ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል።”​—መዝሙር 72:7

እንደዚህ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች፣ ዓመፀኛ ባሕርይ የነበራቸውን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሰላም ወዳዶች እንዲሆኑ ረድተዋል። የሳልቫዶር ጋርዛን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት።