በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችል ቁልፍ

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችል ቁልፍ

“መጽሐፍ ቅዱስን የምትረዱበት መንገድ ትክክል እንደሆነ እንዴት ታውቃላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስን በተለያዩ መንገዶች መረዳት ይቻላል!”

ሰዎች እንዲህ ሲሉ ሰምተህ ታውቅ ይሆናል። ሆኖም አንዳንድ ጥቅሶችን በመመርመር ሌሎቹን መረዳት እንደሚቻል ታውቅ ነበር? ቁልፉ ይኸውልህ፦ በአንድ ጥቅስ ዙሪያ ያሉት ሐሳቦች የጥቅሱን ትርጉም ግልጽ የማያደርጉ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ስለዚሁ ርዕሰ ጉዳይ የሚያወሱ ሌሎች ጥቅሶችን አመሳክር። በዚህ መንገድ የራሳችን አስተያየት ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አስተሳሰባችንን እንዲመራው እንፈቅዳለን።

ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ምን እንደሚል እንመልከት። ከተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተወሰዱ ስድስት ጥቅሶች ከዚህ በታች ቀርበዋል። እነዚህ ጥቅሶች እርስ በርስ የሚደጋገፉት እንዴት እንደሆነ ልብ በል።

  • “እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑት የሞቱት አይደሉም፤ ወደ ዝምታው ዓለም የሚወርዱም አይደሉም።”መዝሙር 115:17

  • “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ። መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።”መዝሙር 146:3, 4

  • “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም።”መክብብ 9:5

  • “ሲኦል አያመሰግንህም፤ ሞት አያወድስህም፤ . . . እኔ ዛሬ እንደማደርገው፣ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል።”ኢሳይያስ 38:18, 19

  • “ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።”ሕዝቅኤል 18:4

  • ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከሞተ ብዙም ስላልቆየው ወዳጁ አልዓዛር ሲናገር “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” ብሏል። “ደቀ መዛሙርቱም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ተኝቶ ከሆነስ ይድናል’ አሉት። . . . ስለዚህም በግልጽ እንዲህ አላቸው፤ ‘አልዓዛር ሞቶአል።’” ዮሐንስ 11:11-14 አ.መ.ት

እነዚህ ጥቅሶች ምን ሐሳብ እንደያዙ አስተዋልክ? አብዛኛው ሰው ከሚያምነው በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ከሕልውና ውጭ እንደሆኑ ያስተምራል። ሙታን ወደ ሰማይ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሄደው በሕይወት እየኖሩ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የወሰዳቸው ያህል ምንም ነገር አያውቁም። በመሆኑ አምላክን ማመስገን ሌላው ቀርቶ ማሰብ እንኳ አይችሉም። *

ዋናው ነጥብ፦ መጽሐፍ ቅዱስን ርዕስ በርዕስ ስንመረምረው መሠረታዊ የሆኑት ትምህርቶች ግልጽ ይሆኑልናል። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበት ይህ ዘዴ ጥረት ይጠይቃል። (ምሳሌ 2:1-5) ይሁን እንጂ የላቀ ጥቅም የሚያስገኝልንን ማንኛውም ነገር ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለብን የታወቀ ነው።

^ አን.11 መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ ያሉ ሙታን ወደፊት አምላክ በወሰነው ጊዜ ‘ከእንቅልፋቸው እንደሚነሱ’ ወይም ትንሣኤ እንደሚያገኙ ያስተምራል።—ኢዮብ 14:14, 15፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15