በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጡብኝም

ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጡብኝም

መጠጥና ዓመፅ እወድ ነበር። አንድ ቀን ግን ሕይወቴን ቆም ብዬ እንድመረምር የሚያስገድድ መርዶ ሰማሁ። እስቲ ታሪኬን ላውጋችሁ።

በ1943 በሩባተም፣ ኦክላሆማ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ተወለድኩ። ከልጅነቴ ጀምሮ ዓመፀኛ ነበርኩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ልጨርስ አካባቢ መጠጣት ጀመርኩ። አባቴም የአልኮል ሱሰኛ ስለነበረ እኔ መጠጣት ስጀምር ተወዳጀን። ለመጠጣትና ለመደባደብ ስንል ብቻ ወደ ጭፈራ ቤቶችና ግብዣዎች እንሄድ ነበር።

በ1966 ሸርሊ ከተባለች ወጣት ጋር ትዳር መሠረትሁ፤ ከዚያም አንጀላ እና ሾን የሚባሉ ሁለት ልጆች ወለድን። ያም ቢሆን ከመጠን በላይ መጠጣቴን አልተውኩም። ገቢዬን ለመጨመር ማሪዋና እያመረትኩ መሸጥ ጀመርኩ። በተጨማሪም በአካባቢያችን ባሉ ቡና ቤቶች ውስጥ ተቀጠርኩ፤ ሥራዬ የማይፈለጉ ወይም የሚያስቸግሩ ሰዎችን ማባረር ነበር። ይህ ሥራ የአልኮልና የዓመፅ ጥማቴን እንደ ልብ ለማርካት አስቻለኝ። በዚያ ወቅት ማንንም ወይም ምንም ነገር አልፈራም ነበር፤ ለሌሎች ስሜትም ቢሆን ደንታ አልነበረኝም።

“እኔን ለመስበክ አንድም ሰው እንዳታመጪ!”

የሸርሊ የአጎት ልጅ ወደ ካሊፎርኒያ ሄዶ ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንቶ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። ወደ ኦክላሆማ ሲመለስ የተማረውን ነገር ለሸርሊ ነገራት፤ እሷም የነገራት ነገር እውነት መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባትም። ሸርሊ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ካጠናች በኋላ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ስለወሰነች በ1976 ተጠመቀች። እኔ ግን ሃይማኖቷን አልወደድኩላትም። ስለዚህ “እኔን ለመስበክ አንድም ሰው እንዳታመጪ!” አልኳት። “የፈለገ ቢሆን ሐሳቤን አልለውጥም።”

ሸርሊ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ሳትጥስ እንደምትወደኝ ማሳየቷን ቀጠለች። እንዲያውም እሷና ልጆቻችን በመንግሥት አዳራሽ ወደሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ከመሄዳቸው በፊት አብሬያቸው እንድሄድ በደግነት ትጋብዘኝ ነበር። አንጀላም “አባዬ፣ ከእኛ ጋር ብትሄድ ደስ ይለን ነበር” ትለኛለች።

ሕገ ወጥ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ስለምካፈል ብዙውን ጊዜ ሽጉጥ እይዝ ነበር። ከዚህም በላይ አንዳንድ ጊዜ ለብዙ ቀናት ከቤት ጠፍቼ እሰነብታለሁ፤ ይህም በትዳራችን ውስጥ ውጥረት ይፈጥር ነበር። በመሆኑም ወደ ቤት ስመለስ ውጥረቱን ለማርገብ ስል ከሸርሊ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እሄዳለሁ። በዚያ የማገኛቸው የይሖዋ ምሥክሮች ምንጊዜም በደግነት የሚቀበሉኝ ሲሆን የሚያስተምሩት ነገርም ቢሆን ትርጉም ይሰጥ ነበር።

ከጊዜ በኋላ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ መጽሐፍ ቅዱስን አብሬው እንዳጠና ሐሳብ አቀረበልኝ። እኔም ግብዣውን ተቀበልኩ። የሚያሳዝነው ግን የተማርኩት ነገር ብዙም አልለወጠኝም፤ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አለማቋረጤ ነበር። ሽማግሌውም ይህንን ስለተገነዘበ መጥፎ ጓደኝነት ስላሉት አደጋዎች የሚገልጹ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን አሳየኝ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ምክሩን የሰጠኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቢሆንም ተከፋሁ፤ በመሆኑም ማጥናቴን አቆምኩና በቀድሞ አካሄዴ ይበልጥ ገፋሁበት። ትዕቢተኛ በመሆኔ የወሰድኩት እርምጃ ሸርሊንና ልጆቻችንን በጣም አሳዘናቸው!

“አሁንም ቢሆን እንወድሃለን”

በ1983 አንድ መርዶ ሰማሁ። በጣም የምወደው የሸርሊ እህት ልጅ ሞተ። ይህም በጥልቅ ስላሳዘነኝ ስለ ሕይወቴ ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ትዳሬንና ቤተሰቤን እንዲሁም ትልቅ ቦታ የምሰጣቸውን ሰዎች ሁሉ የሚጎዳ አካሄድ እየተከተልኩ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ይህንን ማስተዋሌ የሕይወቴን አቅጣጫ እንድቀይር አነሳሳኝ። በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጆን የሚባል አንድ አረጋዊ የይሖዋ ምሥክር በደግነት እጁን ትከሻዬ ላይ አድርጎ “አሁንም ቢሆን እንወድሃለን” አለኝ። ይህ ማበረታቻ በጥልቅ ነካኝ! በማግሥቱ ለጆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን መቀጠል እንደምፈልግ ነገርኩት፤ በዚህ ጊዜ ግን ቀድሞውኑ ላደርጋቸው ይገቡ የነበሩትን ለውጦች ለማድረግ ዝግጁ ነበርኩ።

በመጀመሪያው ጥናታችን ላይ ስለ ጸሎት ተወያየን፤ እኔም ከዚህ በኋላ ለመጸለይ እንደምሞክር ለጆን ነገርኩት። በማግሥቱ በሐቀኝነት ልሠራው የምችል ሥራ ስፈልግ ብውልም አልተሰካልኝም። መኪናዬን እየነዳሁ ሳለ ጮክ ብዬ “ይሖዋ፣ በዚህ አካባቢ እንድቆይ የምትፈልግ ከሆነ ሥራ ብታገኝልኝ ይሻላል!” አልኩ። ትንሽ ቆይቼ ግን ‘እንዴ፣ ምን ማድረጌ ነው? ብቻዬን የምለፈልፈው ምን ሆኜ ነው?’ ብዬ አሰብኩ። ‘ጸሎት ሰሚ’ በሆነው አምላክ ላይ ያለኝን እምነት ማሳደግና የጸሎቴን ይዘት ማሻሻል እንደሚያስፈልገኝ ግልጽ ነበር። (መዝሙር 65:2) የሚገርመው ግን በጸለይኩ ማግሥት ሥራ አገኘሁ!

ጸሎት ያለውን ኃይል መገንዘቤ ይሖዋን ይበልጥ እንድወደው እንዲሁም እሱ በሚሰጠኝ አመራር እንድተማመን አድርጎኛል

ከዚያ በኋላ ደጋግሜና ከልቤ መጸለይ ጀመርኩ። ደግሞም የይሖዋን በረከት በተደጋጋሚ ተመልክቻለሁ። ሁልጊዜም ቢሆን በአምላክ መኖር አምን ነበር፤ ቢሆንም እነዚህ አጋጣሚዎች በ⁠1 ዮሐንስ 5:14 ላይ የተመዘገቡትን “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” የሚሉትን ቃላት እውነተኝነት እንድመለከት ረድተውኛል። ጸሎት ያለውን ኃይል መገንዘቤ ይሖዋን ይበልጥ እንድወደው እንዲሁም እሱ በሚሰጠኝ አመራር እንድተማመን አድርጎኛል።—ምሳሌ 3:5, 6

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንደገና መገኘት ስጀምር የይሖዋ ምሥክሮች ሞቅ ባለ ስሜት ተቀበሉኝ። ከዚህም በላይ ‘እርስ በርሳቸው አጥብቀው ከልብ እንደሚዋደዱ’ ስመለከት በጥልቅ ተነካሁ። (1 ጴጥሮስ 1:22) በተጨማሪም በምሳሌ 13:20 ላይ የሚገኘው “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” የሚለው ሐሳብ ትክክል መሆኑን አስተዋልኩ።

ለብዙ ዓመታት ቤተሰቤን ሳስቸግርና ሳሳዝናቸው ኖሬያለሁ፤ አሁን ግን ሰላማዊ ሰው እንዲሁም የተሻልኩ ባልና አባት ለመሆን ብሎም ከእነሱ ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ መጣር ጀመርኩ። “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል” እንዲሁም “አባቶች ሆይ፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው” የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ።—ኤፌሶን 5:28፤ ቆላስይስ 3:21

እያደረግኋቸው የነበሩት ለውጦች በቤተሰብ ሕይወቴ ላይ ጥሩ ውጤት እንዳመጡ ለመገመት አያዳግትም። ይህን ስመለከት በማቴዎስ 5:3 ላይ ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” በማለት የተናገረው ሐሳብ እውነት እንደሆነ አረጋገጥኩ። በመጨረሻ፣ እውነተኛ ደስታ አገኘሁ!

ሰኔ 1984 ልጄ አንጀላ በይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላት ነበር። በአንድ ወቅት ምን ዓይነት ሰው እንደነበርኩ ከገለጸች በኋላ ስላደረግኋቸው ለውጦች ተናገረች። ሐሳቧን ስትደመድም በዚያ ቀን ለመጠመቅ ፊተኛው ወንበር ላይ ከተቀመጡት መካከል እኔም መገኘቴ ምን ያህል በደስታ እንዳስፈነደቃት ገለጸች።

ይሖዋ እንደ እኔ ባሉ ሰዎች ተስፋ የማይቆርጥ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ! በተጨማሪም ሸርሊና ልጆቻችን ተስፋ ስላልቆረጡብኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ክርስቲያናዊ መመሪያዎችን ከልቧ ተግባራዊ የምታደርገው ሸርሊ በ1 ጴጥሮስ 3:1 ላይ ያለውን “እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ” የሚለውን ምክር በታማኝነት ሥራ ላይ አውላለች። መጥፎ አካሄድ እከተል በነበረባቸው ዓመታት ሁሉ እሷ ያሳየችው ታማኝነት፣ ትዕግሥትና መልካም ምግባር በመጨረሻ ወደ አእምሮዬ ስመለስ እውነትን እንድማር መንገድ ከፍቷል።

ከተጠመቅሁ ጀምሮ የማያምኑ የትዳር ጓደኞች ላሏቸው ክርስቲያኖች የሸርሊን ምሳሌ በመጥቀስ ተስፋ እንዳይቆርጡ አበረታታቸዋለሁ። “መጀመሪያ ላይ የማይሆን ቢመስልም እንኳ ይሖዋ፣ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ባለው ኃይልና በእናንተ መልካም ምግባር ተጠቅሞ የትዳር ጓደኞቻችሁ እንዲለወጡ ሊረዳቸው ይችላል” እላቸዋለሁ።