በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

የወንጀል ሰለባ እንዳትሆን ራስህን ጠብቅ!

የወንጀል ሰለባ እንዳትሆን ራስህን ጠብቅ!

“አብዛኛውን ጊዜ ሲመሽ ጓደኞቼ ወደ ቤቴ ይሸኙኛል። አንድ ቀን ምሽት ግን በጣም ደክሞኝ ስለነበረ ታክሲ ለመያዝ ወሰንኩ።

“ባለ ታክሲው ወደ ቤቴ አልወሰደኝም። ከዚህ ይልቅ ጭር ወዳለ ቦታ ወሰደኝና ሊደፍረኝ ሞከረ። ባለ በሌለ ኃይሌ ስጮኽ ወደ ኋላ አፈገፈገ። በድጋሚ ወደ እኔ ሲመጣ ጮኽኩና ሮጥኩ።

“ከዚህ በፊት ‘መጮኽ ምን ይጠቅማል?’ ብዬ አስብ ነበር። አሁን ግን ጥቅም እንዳለው ተገነዘብኩ!”—ካረን *

በብዙ አገሮች ወንጀል በማንኛውም ጊዜ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ አገር የሚኖሩ አንድ ዳኛ “ይዋል ይደር እንጂ ማንኛውም ሰው የወንጀል ሰለባ የሚሆንበት አጋጣሚ የሰፋ መሆኑ አሳዛኝ ነው” በማለት ተናግረዋል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ወንጀል እምብዛም አያጋጥም ይሆናል። እንደዚያም ሆኖ መዘናጋት ለጥቃት ሊያጋልጥ ስለሚችል መጠንቀቁ ብልህነት ነው።

የምትኖረው ወንጀል በበዛበት አካባቢም ይሁን እምብዛም በማያጋጥምበት ቦታ፣ ራስህን፣ ቤተሰቦችህንና ወዳጆችህን ከወንጀል መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግህ ጠቃሚ ነው፦ “ጥበበኛ ሰው አደጋን አስቀድሞ አይቶ ይሸሻል፤ ሞኞች ግን ዝም ብለው ይሄዳሉ፤ ችግር ላይም ይወድቃሉ።” (ምሳሌ 22:3 ኒው ሴንቸሪ ቨርዥን) የፖሊስ ባለሥልጣናት መጀመሪያውኑ የወንጀል ሰለባ ከመሆን ለመዳን የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች መውሰድን አጥብቀው ያበረታታሉ።

ወንጀል የሚያስከትለው መዘዝ አካላዊ ጉዳትና የንብረት ኪሳራ ብቻ አይደለም። የወንጀል ሰለባ የሆኑ ብዙ ሰዎች ዘላቂ የሆነ አእምሯዊና ስሜታዊ ጉዳትም ይደርስባቸዋል። እንግዲያው የወንጀል ሰለባ ላለመሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይህን በአእምሮህ ይዘህ ከአራት የወንጀል ዓይነቶች ማለትም ከዝርፊያ፣ ከፆታ ጥቃት፣ በኢንተርኔት ከሚፈጸም ወንጀልና ከማንነት ስርቆት ራስህን ለመጠበቅ የተለያዩ እርምጃዎች መውሰድ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

 ዝርፊያ

ምንድን ነው? ዝርፊያ ኃይል በመጠቀም ወይም በማስፈራራት የሚፈጸም ስርቆት ነው።

ምን ችግር ያስከትላል? በብሪታንያ መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች ተከታታይ የሆነ ዝርፊያ ከተፈጸመ በኋላ የተዘረፉት ሰዎች አካላዊ ጉዳት ባይደርስባቸውም እንኳ ሁሉም ስሜታቸው በእጅጉ ተረብሾ እንደነበረ አንዲት አቃቤ ሕግ ገልጸዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “አንዳንዶቹ የደረሰባቸው ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ ጭንቀትና የእንቅልፍ ችግር አስከትሎባቸዋል፤ ደግሞም ሁሉም ማለት ይቻላል፣ የደረሰባቸው ነገር በዕለት ተዕለት ሥራቸው ላይ በእጅጉ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይናገራሉ።”

ምን ማድረግ ይቻላል?

  • ሌቦች በተገኘው አጋጣሚ ይጠቀማሉ፤ ስለዚህ ዙሪያ ገባውን በደንብ አስተውል

    ንቁ ሁን። ሌቦች በተገኘው አጋጣሚ ይጠቀማሉ። ብዙውን ጊዜ የጥቃታቸው ሰለባ የሚያደርጉት ያልጠረጠሩ ሰዎችን ነው። በመሆኑም በዓይን የሚከታተሉህን ሰዎች በንቃት መመልከትና ዙሪያ ገባውን ማስተዋል የሚያስፈልግህ ሲሆን ከልክ በላይ በመጠጣት ወይም ዕፆችን በመውሰድ ንቃትህ እንዲቀንስም ሆነ የማመዛዘን ችሎታህ እንዲዛባ ማድረግ የለብህም። “አንድ ሰው የአልኮል መጠጥ ሲጠጣ ወይም ዕፅ ሲወስድ አጥርቶ ማሰብና አደገኛ ሁኔታን ማስተዋል እንደሚሳነው” አንድ የጤና ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል።

  • ንብረትህን ጠብቅ። መኪናህን ቆልፍ፤ እንዲሁም የቤትህን በርና መስኮት ዝጋ። የማታውቀውን ሰው አታስገባ። ውድ የሆኑ ንብረቶችህን ሰው እንዲያይልህ ከማድረግ ይልቅ ስውር በሆነ ቦታ አስቀምጥ። ምሳሌ 11:2 “በትሑት ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። ችግረኛ የሆኑ ልጆችን ጨምሮ ሌቦች ብዙውን ጊዜ ዒላማቸው የሚያደርጉት ይታይልኝ በሚል ስሜት ውድ ጌጣጌጦችን አድርገውና የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን በግልጽ ይዘው የሚዞሩ ሰዎችን ነው።

  • ምክር ጠይቅ። “ተላላ ሰው መንገዱ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ምክር ይሰማል።” (ምሳሌ 12:15) በጉዞ ላይ ከሆንክ ባለሥልጣናትን ጨምሮ አካባቢውን በደንብ የሚያውቁ ነዋሪዎች የሚሰጡህን ምክር በጥንቃቄ ስማ። እነሱም ልትሄድባቸው የማይገቡ ስፍራዎችን ሊጠቁሙህ እንዲሁም ራስህንና ንብረቶችህን እንዴት መጠበቅ እንደምትችል ሊነግሩህ ይችላሉ።

ፆታዊ ጥቃት

ምንድን ነው? ፆታዊ ጥቃት አስገድዶ መድፈርን ብቻ ሳይሆን በመዛት፣ በማስገደድ ወይም በማስፈራራት አንድ ግለሰብ ማንኛውንም ዓይነት ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ድርጊቶችን እንዲፈጽም ማድረግን ያጠቃልላል።

ምን ችግር ያስከትላል? ተገድዳ የተደፈረች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “እጅግ የሚያሳዝነው ነገር፣ ጉዳቱ ጥቃቱ እየተፈጸመ ባለበት ጊዜ ብቻ ተወሰኖ የሚቀር አለመሆኑ ነው። የስሜት ሥቃዩ ለረጅም ጊዜ ሊቀጥል ብሎም ትዝታው ቶሎ ከአእምሯችሁ ላይወጣ ይችላል፤ ይህም ለሕይወት ያላችሁ አመለካከት እንዲለወጥ ያደርጋል። የቤተሰባችሁንና የወዳጆቻችሁን ሕይወት ጭምር የሚነካ ነው።” እርግጥ ነው፣ ለተፈጸመው ፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆነው ግለሰብ ተጠያቂ አይሆንም። ተጠያቂ የሚሆነው ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ነው።

ምን ማድረግ ይቻላል?

  • ስሜታችሁን አዳምጡ። በኖርዝ ካሮላይና፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ የፖሊስ ቢሮ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ቦታ ወይም ከአንድ ሰው ጋር መሆን ከጨነቃችሁ ቦታውን ወይም ግለሰቡን ትታችሁ ሂዱ። ውስጣችሁ አደጋ መኖሩን እየነገራችሁ ከሆነ ማንም ሰው ቢያግባባችሁ እዚያ ቦታ አትቆዩ።”

  • በራስ የመተማመን ስሜት ይኑራችሁ፤ ሁኔታዎችን በትኩረት ተከታተሉ። ፆታዊ ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎች ሰለባ የሚያደርጉት ያልጠረጠሩና ፈሪ ሰዎችን ነው። ስለዚህ አረማመዳችሁ በራሳችሁ እንደምትተማመኑ የሚያሳይ ይሁን፤ እንዲሁም ንቁዎች ሁኑ።

  • እርምጃ ለመውሰድ አታመንቱ። ጩኹ። (ዘዳግም 22:25-27) ሸሽታችሁ አምልጡ ወይም ድንገተኛ  ጥቃት ሰንዝሩ። እንዲሁም የሚቻል ከሆነ ከአደጋው ልታመልጡ ወደምትችሉበት ቦታ በመሮጥ ፖሊስ ጥሩ። *

በኢንተርኔት የሚፈጸም ወንጀል

ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቱ ወንጀል ግብር ማጭበርበርን፣ ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት መንግሥትን ማታለልን፣ በተሰረቀ ክሬዲት ካርድ መጠቀምን እንዲሁም ገንዘብ የተከፈለባቸውን ዕቃዎች ሳይልኩ መቅረትን ያጠቃልላል። በኢንተርኔት ላይ ከኢንቨስትመንትና ከጨረታዎች ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶችንም ይጨምራል።

ምን ችግር ያስከትላል? በኢንተርኔት የሚፈጸም ወንጀል የወንጀሉ ሰለባ በሆኑት ሰዎችም ሆነ በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ኪሳራ ያስከትላል። አንድ ምሳሌ እንመልከት። ሳንድራ በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት ከምታገኝበት ድርጅት የተላከ የሚመስል ኢ-ሜይል ደረሳት፤ መልእክቱ ዝርዝር የባንክ መረጃዎቿ ላይ ለውጥ እንድታደርግ የሚጠይቅ ነበር። የግል መረጃዎቿን ከላከች ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከባንክ ሒሳቧ ላይ 4,000 የአሜሪካ ዶላር በውጭ አገር ወደሚገኝ ባንክ እንደተዛወረ ስታውቅ ደነገጠች። ሳንድራ እንደተታለለች ወዲያውኑ ተገነዘበች።

ምን ማድረግ ይቻላል?

  • ጠንቃቃ ሁኑ! ሕጋዊ መስለው በሚቀርቡ ድረ ገጾች እንዳትታለል ተጠንቀቅ፤ እንዲሁም ሕጋዊ የሆኑ የገንዘብ ተቋማት ከፍተኛ ሚስጥራዊነት ያላቸውን መረጃዎች በኢ-ሜይል እንድትልክላቸው እንደማይጠይቁህ አስታውስ። በኢንተርኔት አማካኝነት አንድ ነገር ከመግዛትህ ወይም ኢንቨስት ከማድረግህ በፊት ኩባንያው እምነት የሚጣልበት መሆኑን አረጋግጥ። ምሳሌ 14:15 “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። በተጨማሪም በውጭ አገር ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር ስትዋዋል ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ። ምክንያቱም ችግር ቢፈጠር እንኳ ማስተካከል ከባድ ሊሆን ይችላል።

  • ስለ ድርጅቱና ስለ ፖሊሲዎቹ ጠንቅቃችሁ እወቁ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ኩባንያው የሚገኝበት ቦታ የት ነው? የስልክ ቁጥሩ ትክክል ነው? የምገዛው ዕቃ ከተተመነለት ዋጋ ሌላ ተጨማሪ እንድከፍል የሚጠይቅ ነው? ያዘዝኩት ነገር መቼ ይደርሰኛል? ዕቃውን ካልፈለግኩት ገንዘቤ ሊመለስልኝ ይችላል?’

  • ታገኛላችሁ የተባለው ነገር ለማመን የሚያዳግት ከሆነ ጠርጥሩ። በኢንተርኔት አማካኝነት ለሚፈጸም ስርቆት ሰለባ የሚሆኑት ብዙውን ጊዜ ስግብግቦችና ያለምንም ወጪ የሆነ ነገር ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። በኢንተርኔት ላይ፣ አነስተኛ ሥራ በመሥራት ብዙ ገንዘብ ማግኘትን ወይም ብቃቱን ሳያሟሉ ከፍተኛ ብድር ወይም ክሬዲት ካርድ መውሰድን አሊያም አነስተኛ ገንዘብ በማውጣት ከፍተኛ ትርፍ ማጋበስን የመሳሰሉ የሚያጓጉ ግብዣዎች ይቀርባሉ። የዩናይትድ ስቴትስ የፌደራል ንግድ ኮሚሽን እንዲህ ብሏል፦ “ገንዘብህን በአንድ ዓይነት ኢንቨስትመንት ላይ እንድታውል ግብዣ ሲቀርብልህ ጊዜ ወስደህ ሕጋዊ መሆኑን አጣራ። ታገኛለህ የተባለው ትርፍ ከፍተኛ በሆነ መጠን የመጭበርበር አጋጣሚህም ያንኑ ያህል ከፍ ያለ ነው። አንድ የንግድ አስተዋዋቂ ስለገፋፋህ ብቻ ሕጋዊነቱን ሳታረጋግጥ አንድ ዓይነት ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዳትገባ ተጠንቀቅ።”

የማንነት ስርቆት

ምንድን ነው? የማንነት ስርቆት ሲባል የማጭበርበር ድርጊት ወይም ሌላ ዓይነት ወንጀል ለመፈጸም የአንድን ሰው ማንነት የሚገልጽ የግል መረጃ መስረቅ ማለት ነው።

ምን ችግር ያስከትላል? ሌቦች ክሬዲት ካርድ ወይም ብድር ለማግኘት አሊያም አዲስ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት የአንተን የግል መረጃዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ። ከዚያም ከፍተኛ ዕዳ እንዲከመርብህ ያደርጋሉ! የኋላ ኋላ ዕዳው እንዲሰረዝልህ ማድረግ ብትችል እንኳ በገንዘብ አያያዝ ረገድ ያለህ ስም ይጎድፋል። የዚህ ወንጀል ሰለባ የሆነ አንድ ሰው ሲናገር “ገንዘብህ ከመሰረቁ ይበልጥ የሚጎዳህ በገንዘብ አያያዝ ረገድ መጥፎ ስም ማትረፍህ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ሁኔታ በብዙ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብሏል።

ምን ማድረግ ይቻላል?

  • ሚስጥራዊ መረጃዎችህን ጠብቅ። የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ወይም ዕቃ ለመግዛት በኢንተርኔት በተለይም  ብዙ ሰው በሚጠቀምበት ኮምፒውተር የምትጠቀም ከሆነ የይለፍ ቃልህን በየጊዜው ለውጥ። እንዲሁም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሚስጥራዊ የሆኑ የግል መረጃዎችህን እንድትሰጥ የሚጠይቁ ኢ-ሜይሎች ሲደርሱህ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ።

    የማንነት ስርቆት የሚፈጽሙ ሰዎች የሚጠቀሙት በኮምፒውተር ብቻ አይደለም። የባንክ ደብተሮችን፣ ቼኮችን፣ ክሬዲት ካርዶችን፣ የማኅበራዊ ዋስትና ቁጥሮችንና (ሶሻል ሰኪዩሪቲ ነምበርስ) እነዚህን የመሳሰሉ አስፈላጊ ሰነዶችን በእጃቸው ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቶቹን ሰነዶች በሙሉ በጥንቃቄ ማስቀመጥ፣ የማትፈልጋቸው ከሆነ ደግሞ ከማስወገድህ በፊት በሚገባ መቀዳደድ አለብህ። አንድ ሰነድ እንደጠፋ ወይም እንደተሰረቀ ከተሰማህ ወዲያውኑ ለሚመለከተው አካል አሳውቅ።

  • የባንክ ሒሳብህን ተከታተል። “የማንነት ስርቆትን . . . ለመከላከል ውጤታማ የሆነው ዘዴ በንቃት መከታተል ነው” በማለት የዩናይትድ ስቴትስ የፌደራል ንግድ ኮሚሽን ገልጿል። አክሎም “አንድ ሰው በስሙ ስርቆት ሊፈጸም እንደሚችል አስቀድሞ መጠርጠሩ ትልቅ ልዩነት ሊያመጣ ይችላል” ብሏል። ስለዚህ የባንክ ሒሳብህን በየጊዜው መከታተልና ከባንክ ሒሳብህ ላይ አንተ ሳታውቅ ገንዘብ እንደወጣ ካስተዋልክ ሁኔታውን ማጣራት ይኖርብሃል። የሚቻል ከሆነ ጥሩ ስም ካተረፈ ድርጅት የክሬዲት ካርድ የሒሳብ መግለጫህን መጠየቅና የሒሳብ መግለጫው ትክክል መሆኑን በጥንቃቄ መመርመር አለብህ።

እርግጥ ነው፣ በዚህ ዓለም ውስጥ ምንም ዓይነት ዋስትና የለም። በጣም ጠንቃቃ የሆኑ ሰዎችም እንኳ የወንጀል ሰለባ ሆነዋል። ያም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብና ማስተዋል ብንከተል ምንጊዜም ተጠቃሚዎች እንሆናለን። “ጥበብን አትተዋት፤ እርሷም ከለላ ትሆንሃለች፤ አፍቅራት፤ እርሷም ትጠብቅሃለች።” (ምሳሌ 4:6) ከሁሉም በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ወንጀል የማይኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል።

በቅርቡ ወንጀል ይወገዳል

አምላክ ወንጀልን እንደሚያስወግድ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት፦

  • አምላክ ወንጀልን ማስወገድ ይፈልጋል“እኔ እግዚአብሔር ፍትሕን ስለምወድ፣ ዝርፊያንና በደልን እጠላለሁ።”—ኢሳይያስ 61:8

  • አምላክ ወንጀልን ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል አለው። “የእግዚአብሔር ኀይል እጅግ ታላቅ [ነው] . . . ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ጻድቅና ቅን ነው።”—ኢዮብ 37:23 የ1980 ትርጉም

  • ክፉዎችን ለማጥፋትና ጻድቃንን በሕይወት ለማኖር ቃል ገብቷል“ክፉ ሰዎች ይጠፋሉ።” እንዲሁም “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:9, 29

  • ለታማኝ አገልጋዮቹ ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ለማምጣት ቃል ገብቷል“ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:11

እነዚህ ጥቅሶች ልብ የሚነኩ አይደሉም? ታዲያ አምላክ ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ የበለጠ ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር ለምን ጊዜ አትመድብም? የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ጥበብ ያዘለ ሌላ መጽሐፍ የለም። እንዲሁም ወደፊት ከወንጀል ነፃ የሆነ ዓለም እንደሚመጣ የተረጋገጠ ተስፋ የሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። *

አምላክ ወንጀል የማይኖርበትና ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ለማምጣት ቃል ገብቷል

^ አን.5 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.22 አብዛኞቹ ሰዎች ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው በሚያውቁት ሰው ነው። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፍ በገጽ 228 ላይ “ፆታዊ ጥቃት እንዳይደርስብኝ ራሴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት። ይህ መጽሐፍ www.dan124.com በተሰኘው ድረ ገጻችን ላይ ይገኛል።

^ አን.44 ጠቃሚ በሆኑ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፉን እንዲሰጡህ መጠየቅ አሊያም www.dan124.com በተባለው ድረ ገጽ ላይ መጽሐፉን ማንበብ ትችላለህ።