በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ራሴን ከፆታዊ ትንኮሳ መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?

ራሴን ከፆታዊ ትንኮሳ መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ሐሳቦች ተመልከቺ፦

  1.   ኮስታራ ሁኚ። ከሥራ ባልደረቦችሽ ጋር ባለሽ ግንኙነት ተግባቢና ሰው አክባሪ ሁኚ፤ ያም ቢሆን የሥራ ባልደረቦችሽ አንቺን ለማሽኮርመም የሚያደርጉትን ጥረት እንደማትቀበይ በግልጽ በሚያሳይ መንገድ ቅርርባችሁ ላይ ገደብ ማበጀት ይኖርብሻል።​—ማቴዎስ 10:16፤ ቆላስይስ 4:6

  2.   ሥርዓታማ አለባበስ ይኑርሽ። ሰውነትን የሚያጋልጥ አለባበስ መጥፎ መልእክት ያስተላልፋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በልከኝነትና በማስተዋል” መልበስ ተገቢ እንደሆነ ይናገራል።​—1 ጢሞቴዎስ 2:9

  3.   ጓደኞችሽን በጥበብ ምረጪ። ማሽኮርመምን እንደ ተራ ነገር ከሚቆጥሩ ወይም ሌሎች ሲያሽኮረምሟቸው ደስ ከሚላቸው ሰዎች ጋር የምትውዪ ከሆነ አንቺም እንደዚያ ዓይነት ሰው ልትመስያቸው ትችያለሽ።​—ምሳሌ 13:20

  4.   መጥፎ ወሬ ሲጀመር ዘወር በይ። በጭውውታችሁ መሃል “አሳፋሪ ምግባር፣ [“የብልግና ንግግር፣” ሕያው ቃል] የማይረባ ንግግርም ሆነ ጸያፍ ቀልድ” ከተነሳ ጭውውቱን አቋርጠሽ ሂጂ።​—ኤፌሶን 5:4

  5.   ለአደጋ ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች ራቂ። ለምሳሌ፣ አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር ከሥራ ሰዓት ውጪ እንድትሠሪ ከተጠየቅሽ ሁኔታውን ቆም ብለሽ አስቢበት።​—ምሳሌ 22:3

  6.   ፊት ለፊትና በግልጽ ተናገሪ። አንድ ሰው ፆታዊ ትንኮሳ ካደረሰብሽ እንዲህ ያለውን ድርጊት እንደማትታገሺ በግልጽ ተናገሪ። (1 ቆሮንቶስ 14:9) ለምሳሌ ያህል “በጣም ስትጠጋኝ ይጨንቀኛል። ሁለተኛ እንድትነካኝ አልፈልግም” ልትዪው ትችያለሽ። የፆታ ትንኮሳ ያደረሰብሽ ሰው ምን እንዳደረገሽ፣ በዚህ የተነሳ የተሰማሽንና ወደፊት ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት በጽሑፍ ልትገልጪለት ትችያለሽ። እንዲህ የተሰማሽ በሥነ ምግባራዊና ሃይማኖታዊ አቋምሽ ምክንያት እንደሆነ ግልጽ አድርጊለት።​—1 ተሰሎንቄ 4:3-5

  7.   እርዳታ ጠይቂ። ግለሰቡ የሚያደርስብሽን ትንኮሳ ከቀጠለ ለምታምኚው ጓደኛሽ፣ ለቤተሰብሽ አባል፣ ለሥራ ባልደረባሽ ወይም እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠማቸውን ሰዎች በመርዳት ረገድ ልምድ ላለው ሰው ስለ ሁኔታው ተናገሪ። (ምሳሌ 27:9) የፆታ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ብዙ ሰዎች በጸሎት አማካኝነት እርዳታ ማግኘት ችለዋል። ከዚህ ቀደም ጸልየሽ ባታውቂ እንኳ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ የምታገኚውን እርዳታ አቅልለሽ አትመልከቺ።​—2 ቆሮንቶስ 1:3

 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሥራ ቦታቸው ላይ የሚደርስባቸው የፆታ ትንኮሳ ሥራቸውን እንዲጠሉ አድርጓቸዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህን ሁኔታ እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው ይችላል።