በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወጣቶችን መርዳት

በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወጣቶችን መርዳት

ተፈታታኙ ነገር

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጃችሁ ሆን ብላ በሰውነቷ ላይ ጉዳት እንደምታደርስ ብታውቁ ምን ይሰማችኋል? ‘እንዲህ የምታደርገው ለምንድን ነው? ራሷን ለመግደል እየሞከረች ይሆን?’ የሚሉት ጥያቄዎች ወደ አእምሯችሁ ይመጡ ይሆናል።

አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ የምታደርገው ሕይወቷን ለማጥፋት አስባ አይደለም። ያም ቢሆን በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ልጃችሁ ራሷ ላይ ጉዳት የምታደርስ ከሆነ እርዳታ ያስፈልጋታል። * ታዲያ እንዴት ልትረዷት ትችላላችሁ? በመጀመሪያ፣ እንዲህ የምታደርግበትን ምክንያት ለማወቅ ሞክሩ። *

ምክንያቱ ምንድን ነው?

ልጃችሁ በሰውነቷ ላይ ጉዳት የምታደርሰው ሌሎች ስለሚያደርጉት ብቻ ነው? አንዳንድ ወጣቶች በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱት ሌሎች ስለሚያደርጉት ነው። ሆኖም ብዙዎቹ ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት ይህ አይደለም። እንዴት እናውቃለን? በሰውነቷ ላይ ጉዳት የምታደርሰው ወጣት አብዛኛውን ጊዜ ይህን ድርጊቷን የምትፈጽመው በድብቅ ሲሆን ይህን ማድረጓም በጣም ያሳፍራታል። የ20 ዓመቷ ሲልያ “የማደርገውን ነገር ማንም ሰው እንዲያውቅብኝ አልፈልግም ነበር” ብላለች። * “በሰውነቴ ላይ ያሉትን ጠባሳዎች እደብቃቸው ነበር።”

ልጃችሁ በሰውነቷ ላይ ጉዳት የምታደርሰው የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ ነው? አንዳንድ ወጣቶች ዓላማቸው ይህ ሊሆን ይችላል። ይህ ርዕስ የሚያተኩረው ግን ይህን ድርጊታቸውን ለመደበቅ በሚሞክሩ ወጣቶች ላይ ነው፤ እነዚህ ወጣቶች ይህን የሚያደርጉት የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ ብለው አይደለም። ያም ቢሆን በሰውነቷ ላይ ጉዳት ታደርስ የነበረች አንዲት ወጣት፣ ቁስሏን አንድ ሰው እንዲያስተውለው ትመኝ እንደነበር ተናግራለች፤ ይህ ቢሆን ኖሮ ችግሩ ሳይባባስ ሊታወቅና ተገቢውን እርዳታ ልታገኝ ትችል እንደነበር ይሰማታል።

ታዲያ ሰዎች በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱት ለምንድን ነው? ወጣቶች በሰውነታቸው ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ የሚያነሳሷቸው ምክንያቶች ውስብስብ ቢሆኑም አብዛኛውን ጊዜ መሠረታዊው ችግር በውስጣቸው ያለውን የስሜት ሥቃይ በቃላት ለመግለጽ የሚቸገሩ መሆኑ ነው። የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ስቲቨን ሌቨንክሮን፣ ከቲንግ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎች፣ “አካላዊ ሥቃይ ለስሜታዊ ሥቃይ ፈውስ እንደሆነ ያስባሉ።”

በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ፣ በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግር የስሜት ሥቃይ አለባቸው

የጥፋተኝነት ስሜት ቢሰማችሁስ? ልጃችሁ በሰውነቷ ላይ ጉዳት የምታደርሰው እናንተ ጥሩ ወላጅ ባለመሆናችሁ እንደሆነ እያሰባችሁ ከመብሰልሰል ይልቅ ካለባት ችግር እንድትላቀቅ በመርዳት ጥሩ ወላጅ መሆን በምትችሉበት መንገድ ላይ ትኩረት አድርጉ።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ልጃችሁ ስለሚረብሻት ነገር በግልጽ እንድትነግራችሁ አበረታቷት። የሚከተሉት ሐሳቦች በዚህ ረገድ ሊረዷችሁ ይችላሉ።

አጽናኗት። ልጃችሁ ሰውነቷ ላይ ጉዳት እንደምታደርስ ብትነግራችሁ ላለመደናገጥ ወይም ላለመሸበር ጥረት አድርጉ። ከዚህ ይልቅ በሚያረጋጋና በሚያጽናና መንገድ አነጋግሯት።​—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ 1 ተሰሎንቄ 5:14

እንደምትወቅሷት የማያሳዩ ጥያቄዎችን ጠይቋት። ለምሳሌ ያህል እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ልትጠይቋት ትችላላችሁ፦ “ስለ ራስሽ ጥሩ የማይሰማሽ ጊዜ ሊኖር ይችላል፤ የሚረብሽሽ ነገር ምንድን ነው?” ወይም “በጭንቀት ወይም በሐዘን ስትዋጪ ምን ባደርግልሽ ደስ ይልሻል?” ወይም “ይበልጥ መቀራረብ እንድንችል ምን እንዳደርግ ትፈልጊያለሽ?” ሐሳቧን ስትገልጽ ሳታቋርጧት አዳምጧት።​—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ያዕቆብ 1:19

ልጃችሁ ስለ ራሷ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራት እርዷት። በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያተኩሩት በድክመታቸው ላይ በመሆኑ ልጃችሁ ጠንካራ ጎኖቿን እንድታስተውል እርዷት። እንዲያውም ስለ ራሷ ደስ የሚሏትን ቢያንስ ሦስት ነገሮች እንድትጽፍ ሐሳብ ልትሰጧት ትችላላችሁ። ብሪአና የምትባል አንዲት ወጣት “ጠንካራ ጎኖቼን መጻፌ ጥሩ ባሕርያት እንዳሉኝ እንዳስተውል ረድቶኛል” ብላለች። *

ልጃችሁ ወደ ይሖዋ እንድትጸልይ አበረታቷት። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል” ይላል። (1 ጴጥሮስ 5:7) የ17 ዓመቷ ሎሬና እንዲህ ብላለች፦ “የውስጥ ስሜቴን ለይሖዋ አምላክ ዝክዝክ አድርጌ ለመናገር እጥር ነበር፤ በተለይ በሰውነቴ ላይ ጉዳት ለማድረስ በምፈተንበት ጊዜ እንዲህ አደርጋለሁ። መጸለዬ ይህን ድርጊት ለማቆም የበለጠ ጥረት እንዳደርግ ረድቶኛል።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ 1 ተሰሎንቄ 5:17

^ አን.5 በሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስ ሲባል አካል እስኪደማ ወይም እስኪበልዝ ድረስ በስለት ወይም በሌላ ነገር ራስን መጉዳት ማለት ነው።

^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ በሰውነታቸው ላይ ጉዳት ስለሚያደርሱ ሰዎች ስንናገር በአንስታይ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

^ አን.7 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.15 በሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስ አብዛኛውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ወይም ሌላ የጤና እክል ምልክት ነው። እንደ እነዚህ ባሉት ሁኔታዎች የሕክምና እርዳታ ሊያስፈልግ ይችላል። ንቁ! አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች፣ የሚመርጡት ማንኛውም ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የማይጋጭ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው።