በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ንድፍ አውጪ አለው?

ብርሃን የመሰብሰብ ችሎታ ያለው የቢራቢሮ ክንፍ

ብርሃን የመሰብሰብ ችሎታ ያለው የቢራቢሮ ክንፍ

የሳይንስ ሊቃውንት የሰው ልጅ ከከርሰ ምድር በሚወጡ ነዳጆች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ ሲሉ ከፀሐይ ብርሃን የሚገኘውን ኃይል የሚሰበስቡ መሣሪያዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እየጣሩ ነው። አንድ የሳይንስ ሊቅ “የዚህ ችግር መፍትሔ . . . እዚሁ አጠገባችን ባሉ በራሪ ነፍሳት ላይ ሳይገኝ አይቀርም” ብለዋል።

በቢራቢሮ ክንፍ ላይ ያሉት ቅርፊቶች በማር እንጀራ ላይ የሚገኙት ዓይነት ቀዳዳዎች አሏቸው

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ቢራቢሮዎች ቅዝቃዜ በሚኖርበት ወቅት ሰውነታቸውን ለማሞቅ ክንፎቻቸውን ፀሐይ ላይ ይዘረጋሉ። ስዋሎቴይል የሚባለው ቢራቢሮ አንዳንድ ዝርያዎች፣ የፀሐይ ብርሃንን የመሰብሰብና ይዞ የማስቀረት አስደናቂ ችሎታ አላቸው። የእነዚህ ቢራቢሮዎች ሚስጥር ክንፋቸው ጥቁር መሆኑ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ በተጨማሪ በክንፋቸው ላይ ተነባብረው የተቀመጡት በዓይን የማይታዩ ቅርፊት መሰል ነገሮች ለዚህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ቅርፊቶቹ በማር እንጀራ ላይ የሚገኙት ዓይነት ቀዳዳዎች ያሏቸው ሲሆን የተገለበጠ የV ቅርጽ ባላቸው መስመሮች በረድፍ በረድፍ የተከፋፈሉ ናቸው፤ የፀሐይ ብርሃን እነዚህን መስመሮች ተከትሎ ወደ ቀዳዳዎቹ ይገባል። ይህ የተራቀቀ ንድፍ የፀሐይ ብርሃንን ስቦ ስለሚያስቀር የቢራቢሮው ክንፍ በጣም እንዲጠቁር የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ቢራቢሮው ከፀሐይ ብርሃን የሚገኘውን ኃይል ያለምንም ብክነት በመጠቀም ሰውነቱን ለማሞቅ ያስችለዋል።

ሳይንስ ዴይሊ እንዲህ ብሏል፦ “የቢራቢሮ ክንፍ በቀላሉ ሊጎዱ ከሚችሉ ነገሮች የሚመደብ ቢሆንም ተመራማሪዎች የፀሐይ ብርሃንን ተጠቅመው ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ከውኃ ሃይድሮጅን የሚያወጡበትን አዲስ ዘዴ ጠቁሟቸዋል፤ ይህ ዘዴ ብክለት የማያስከትል የኃይል ምንጭ የሆነውን የሃይድሮጅንን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ ያስችላል።” በተጨማሪም ይህ ዘዴ፣ ብርሃንን የሚጠቀሙ መሣሪያዎችንና ከፀሐይ ብርሃን የሚገኘውን ኃይል ወደ ኤሌክትሪክ የሚለውጡ መሣሪያዎችን መሥራት እንደሚያስችል ይታሰባል።

ምን ይመስልሃል? ብርሃን የመሰብሰብ ችሎታ ያለው የቢራቢሮ ክንፍ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?