በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ አንተ ያስባል?

አምላክ ስለ አንተ ያስባል?

አምላክ ስለ አንተ ያስባል?

“እኔ ድኻና ችግረኛ ነኝ፤ ጌታ ግን ያስብልኛል።” *እስራኤላዊው ዳዊት፣ 11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.

ብሔራት በሙሉ “ከአንድ የውሃ ጠብታ ያነሱ ናቸው።”—ኢሳይያስ 40:15

ዳዊት፣ አምላክ ስለ እሱ እንዲያስብ መጠበቁ ምክንያታዊ ነበር? አምላክ ለአንተስ ያስብልሃል? ብዙዎች፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እነሱን ከቁም ነገር እንደሚቆጥራቸው ለማመን ይቸገራሉ። ለምን?

አንዱ ምክንያት አምላክ ከሰዎች እጅግ በጣም ከፍ ያለ በመሆኑ ነው። አምላክ ከሰው ልጆች በጣም የላቀ በመሆኑ ብሔራት በሙሉ ከእሱ አንጻር ሲታዩ “ከአንድ የውሃ ጠብታ ያነሱ ናቸው፤ . . . ምንም ክብደት እንደሌላቸው እንደ ትቢያ የቀለሉ ናቸው።” (ኢሳይያስ 40:15 የ1980 ትርጉም) በዘመናችን ያለ በአምላክ የማያምን አንድ ጸሐፊ “ለአንተም ሆነ ለምታደርገው ነገር ሁልጊዜ ትኩረት የሚሰጥ መለኮታዊ አካል አለ ብሎ ማመን ከሁሉ የከፋ እብሪት ነው” እስከ ማለት ደርሷል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በሚያደርጓቸው ነገሮች የተነሳ የአምላክን ትኩረት ለማግኘት እንደማይበቁ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጂም የሚባል በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ሰላም እንዲኖረኝና ራሴን መግዛት እንድችል አዘውትሬ ብጸልይም ይዋል ይደር እንጂ የግልፍተኝነት ባሕርዬ ያገረሽብኛል። በመጨረሻም በጣም መጥፎ ሰው ስለሆንኩ አምላክ ሊረዳኝ አልቻለም ብዬ ደመደምኩ።”

አምላክ ለሰው ልጆች ትኩረት መስጠት እስከማይችል ድረስ ከእኛ በጣም የራቀ ነው? ፍጹም ስላልሆኑት ፍጥረታቱ ምን ይሰማዋል? አምላክ ራሱ፣ ካልነገረን በስተቀር ማንኛውም የሰው ልጅ ስለ አምላክ ሆኖ መናገርም ሆነ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አይችልም። ይሁን እንጂ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለሰው ልጆች የሰጠው መልእክት ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ እሱ ከሰዎች የራቀና ለግለሰቦች ትኩረት የማይሰጥ አምላክ እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” በማለት ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 17:27) በቀጣዮቹ አራት ርዕሶች ላይ አምላክ ለግለሰቦች እንደሚያስብ የሚያሳዩ ሐሳቦችን እንመረምራለን፤ እንዲሁም እንደ አንተው ላሉ ሰዎች እንዲህ ያለውን አሳቢነት እንዴት እንዳሳየ እንመለከታለን።