በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

ዛጎል አልባ ቀንድ አውጣ የሚያመነጨው የሚያጣብቅ ዝልግልግ ፈሳሽ

ዛጎል አልባ ቀንድ አውጣ የሚያመነጨው የሚያጣብቅ ዝልግልግ ፈሳሽ

 የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት ለቀዶ ሕክምና የሚያገለግል እንዲሁም ቁስል ቶሎ እንዲድን የሚረዳ ሙጫ ለማግኘት ሲሞክሩ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ያሉትን አብዛኞቹን ማጣበቂያዎች በሰው አካል ውስጥ መጠቀም አይቻልም። ምክንያቱም እነዚህ ሙጫዎች መርዛማ ከመሆናቸውም ሌላ ሲደርቁ ጠጣር ይሆናሉ፤ በተጨማሪም እርጥበታማ በሆኑ የሰውነት ክፍሎች ላይ መጣበቅ አይችሉም። ሳይንቲስቶች ዛጎል አልባ ቀንድ አውጣ a የሚያመነጨውን ዝልግልግ ፈሳሽ በማጥናት ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ማግኘት ችለዋል።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ዛጎል አልባ ቀንድ አውጣ አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሚያጣብቅ ዝልግልግ ፈሳሽ ያመነጫል፤ ይህ ፈሳሽ እርጥብ በሆነ ቅጠል ላይም ጭምር እንዲጣበቅ ያስችለዋል። ይህ ዘዴ ቀንድ አውጣው ራሱን እንዲከላከል ይረዳዋል፤ ሆኖም እንቅስቃሴውን ሙሉ በሙሉ አይገድብበትም።

 ተመራማሪዎች ይህ ፈሳሽ የማጣበቅ ችሎታው በጣም ጥሩ እንዲሆን የረዱት ነገሮች ምን እንደሆኑ ደርሰውበታል። ለምሳሌ ያህል ይህ ፈሳሽ ኬሚካላዊ ጥምረትንና በቻርጆች መካከል ያለውን የመሳሳብ ኃይል ይጠቀማል። ከዚህም ሌላ ሙጫው ቀንድ አውጣው በተጣበቀበት ነገር ላይ ወደ ውስጥ ዘልቆ የሚገባ ሲሆን ጫና ሲያርፍበት ደግሞ የመለጠጥ ባሕርይ አለው። ተመራማሪዎች ዛጎል አልባ ቀንድ አውጣ ከሚያመነጨው የሚያጣብቅ ፈሳሽ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሙጫ ሠርተዋል፤ ይህ ሙጫ እስካሁን ከነበሩት ለሕክምና የሚውሉ ማጣበቂያዎች በሙሉ የበለጠ ጥንካሬ ያለው ሲሆን በውስጣዊ የአካል ክፍሎች ላይ መጣበቅ ይችላል። እንዲያውም ይህ ሙጫ “በአካል ክፍሎች ላይ የመጣበቅ አቅሙ ካርቲሌጅ ካለው ከአጥንት ጋር የመጣበቅ አቅም ጋር ተመሳሳይ” እንደሆነ ተነግሮለታል።

 ይህ ሙጫ ሁሉም የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች አዘውትረው የሚጠቀሙበት መሣሪያ እንደሚሆን እንዲሁም ወደፊት በቀዶ ሕክምና ወቅት ስፌትና ስቴፕለር መጠቀም ላያስፈልግ እንደሚችል ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ሙጫው በካርቲሌጅ ላይ የደረሰን ጉዳት ለመጠገን እንዲሁም በሰውነት ውስጥ የሚገቡ የሕክምና መሣሪያዎችን በተገቢው ቦታ ለማጣበቅ ሊያገለግል ይችላል። የተለያዩ ሙከራዎች እንደሚያሳዩት በዚህ ሙጫ አማካኝነት በአንድ አሳማ ልብ ውስጥ የነበረን ቀዳዳ መድፈን እንዲሁም በአይጦች ጉበት ውስጥ የነበሩ ቀዳዳዎችን መሙላት ተችሏል።

 ሳይንቲስቶች አብዛኛውን ጊዜ ተፈጥሮን በማጥናት አዘውትረው ለሚያጋጥሙ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ያገኛሉ። ሙጫውን የሠራው ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዶናልድ ኢንግበር “ከእኛ የሚጠበቀው ነገር መፍትሔውን ከየት መፈለግ እንዳለብን ማወቅ እንዲሁም ለእኛ የሚሆነው መፍትሔ የትኛው እንደሆነ ማስተዋል ነው” በማለት ተናግረዋል።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? ዛጎል አልባ ቀንድ አውጣ የሚያመነጨው የሚያጣብቅ ፈሳሽ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

a የዛጎል አልባ ቀንድ አውጣ (ስላግ) ሳይንሳዊ ስም አራየን ሰብፈስከስ ነው።