በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዓለም አቀፍ ሰላም—የሕልም እንጀራ የሆነው ለምንድን ነው?

ዓለም አቀፍ ሰላም—የሕልም እንጀራ የሆነው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የሰው ልጆች፣ በዓለም ዙሪያ ሰላም ለማስፈን ያደረጓቸው ጥረቶች አልተሳኩም፤ ወደፊት የሚያደርጓቸው ጥረቶችም ቢሆኑ ሊሳኩ አይችሉም፤ እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

  •   ‘ሰው አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ አይችልም።’ (ኤርምያስ 10:23) የሰው ልጆች የተፈጠሩት ራሳቸውን መምራት እንዲችሉ ተደርገው አይደለም፤ እንዲህ የማድረግ መብትም አልተሰጣቸውም፤ በመሆኑም ዘላቂ የሆነ ሰላም ማስፈን አይችሉም።

  •   “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ። መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።” (መዝሙር 146:3, 4) የፖለቲካ መሪዎች የተነሳሱበት ዓላማ ጥሩ ቢሆን እንኳ ለጦርነት መንስኤ የሆኑ ነገሮችን ለዘለቄታው ማስወገድ አይችሉም።

  •   ‘በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን ይመጣል። ምክንያቱም ሰዎች ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ ይሆናሉ።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:1–4) የምንኖረው ይህ ክፉ ዓለም ሊጠፋ በተቃረበበት “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ነው፤ በዚህ ወቅት ሰዎች የሚኖራቸው ባሕርይ ሰላምን ማስፈን ከባድ እንዲሆን ያደርጋል።

  •   “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።” (ራእይ 12:12) የአምላክ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በምድር አካባቢ ብቻ ተወስኖ እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን ሰዎች እንደ እሱ ክፉዎች እንዲሆኑ ተጽዕኖ ያሳድራል። በመሆኑም “የዚህ ዓለም ገዥ” ሰይጣን እስከሆነ ድረስ በምድር ላይ ሰላም ሊሰፍን አይችልም።——ዮሐንስ 12:31

  •   “[የአምላክ መንግሥት፣ አምላክን የሚቃወሙትን] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳንኤል 2:44) በዓለም ዙሪያ ዘላቂ የሆነ ሰላም ሰፍኖ የማየት ፍላጎታችን እውን የሚሆነው በሰብዓዊ መንግሥታት ሳይሆን በአምላክ መንግሥት ነው።—መዝሙር 145:16