በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ስምምነት

የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ስምምነት

ምዕራፍ 11

የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ስምምነት

አንድ ሺህ ስድስት መቶ በሚያክሉ ዓመታት ውስጥ 40 የተለያዩ ሰዎች የጻፏቸው 66 መጻሕፍት የሚገኙበት ቤተ መጻሕፍት አለ እንበል። በተለያዩ ቦታዎች የነበሩት እነዚህ ጸሐፊዎች ሦስት ቋንቋዎችን ተጠቅመዋል። ጸሐፊዎቹ የተለያየ ባሕርይ፣ ችሎታና አስተዳደግ የነበራቸው ናቸው። ይሁን እንጂ የጻፏቸው መጻሕፍት ከጊዜ በኋላ አንድ ላይ ሲሰባሰቡ ከዳር እስከ ዳር አንድ ጭብጥ ያለው ታላቅ መጽሐፍ ወጥቷቸዋል። ይህ ይሆናል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። አይደለም? ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ቤተ መጻሕፍት ነው።

1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚመሰክረው በውስጡ የተንጸባረቀው የትኛው አስገራሚ ስምምነት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ መጻሕፍት ስብስብ ሆኖ ሳለ አንድ ወጥ መጽሐፍ ሆኖ መገኘቱ የማያስገርመው ሐቀኛ የሆነ ተማሪ አይኖርም። መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ የሚያበረታታው የማይለዋወጡ ባሕርያት ላሉት አንድ አምላክ አምልኮ ማቅረብን ነው። ከዚህም በላይ ሁሉም መጻሕፍት ጎላ ብሎ የሚታይ አንድ ጭብጥ የሚያዳብሩ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚንጸባረቀው ይህ አጠቃላይ ስምምነት በእርግጥም መጽሐፉ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።

2, 3. በኤደን የተነገረው ተስፋ ሰጭ ትንቢት የትኛው ነው? ይህ ትንቢት እንዲነገር ያደረጉት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

2 ዋናው የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ በመጀመሪያው የዘፍጥረት መጽሐፍ መክፈቻ ምዕራፎች ውስጥ ተገልጿል። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ፍጹም ሆነው እንደተፈጠሩና ኤደን በምትባል ገነታዊ የአትክልት ስፍራ እንደተቀመጡ እናነባለን። ይሁን እንጂ አንድ እባብ ወደ ሔዋን ቀረብ አለና የአምላክን ሕግ ትክክለኛነት አጠያያቂ አስመስሎ በማቅረብ መሰሪ በሆነ ውሸት አታልሎ ወደ ኃጢአት መራት። አዳምም የእርሷን ፈለግ በመከተል አምላክን ሳይታዘዝ ቀረ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ሁለቱም ሞት ተፈርዶባቸው ከገነት ተባረሩ። እኛ ዛሬ እየተሰቃየን ያለነው ያ የመጀመሪያ ዓመፅ ባስከተለው መዘዝ ነው። ሁላችንም ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአትንና ሞትን ወርሰናል።​—⁠ዘፍጥረት 3:​1-7, 19, 24፤ ሮሜ 5:​12

3 ይሁን እንጂ በዚያ አሳዛኝ ወቅት አምላክ ተስፋ የሚሰጥ አንድ ትንቢት ተናገረ። ትንቢቱ የተነገረው ለእባቡ ቢሆንም አዳምና ሔዋንም ለልጆቻቸው ሊነግሯቸው ይችሉ ዘንድ እነርሱም እየሰሙ ነበር። አምላክ እንደሚከተለው ብሏል:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።”​—⁠ዘፍጥረት 3:​15፤ ሮሜ 8:​20, 21

4. ይሖዋ በኤደን በተናገረው ትንቢት ውስጥ የተጠቀሱት ወገኖች የትኞቹ ናቸው? በዘመናት ሂደት በመካከላቸው የሚኖረው ሁኔታስ ምን ይመስላል?

4 የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ በተመሠረተበት በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተገለጹትን አራት ወገኖች ልብ በል። እነርሱም እባቡና ዘሩ እንዲሁም ሴቲቱና የእርሷ ዘር ናቸው። በቀጣዮቹ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በሚከናወኑት ነገሮች ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱት እነዚህ ወገኖች ነበሩ። በአንድ ወገን ሴቲቱና ዘርዋ በሌላው ወገን ደግሞ እባቡና ዘሩ ሆነው በመካከላቸው ቋሚ የሆነ ጠላትነት ሊኖር ነው። ይህ ጠላትነት በእውነተኛው አምልኮና በሐሰተኛ አምልኮ እንዲሁም በትክክለኛ ምግባርና በክፋት መካከል ያለውን ዘላቂ የሆነ ጠላትነትም የሚጨምር ነው። አንድ ወቅት ላይ እባቡ የሴቲቱን ዘር ተረከዝ ሲቀጠቅጥ የቀናው መስሎ ይታያል። ይሁንና የሴቲቱ ዘር የኋላ ኋላ የእባቡን ራስ ሲቀጠቅጠውና የመጀመሪያው ዓመፀኛ ርዝራዦች በሙሉ ሲጠፉ የአምላክ ሉዓላዊነት ይረጋገጣል።

5. በትንቢቱ ውስጥ የተገለጸችው ሴት ሔዋን እንዳልሆነች እንዴት እናውቃለን?

5 ሴቲቱ ማን ነች? እባቡስ ማን ነው? እንዲሁም ዘሮቻቸው እነማን ናቸው? ሔዋን የመጀመሪያ ልጅዋን ቃየንን በወለደች ጊዜ “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ” ብላ ነበር። (ዘፍጥረት 4:​1) ምናልባትም በትንቢቱ ላይ የተገለጸችው ሴት እርሷ እንደሆነችና ዘሩም ልጅዋ እንደሆነ ተሰምቷት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ቃየን ራሱ እንደ እባቡ መጥፎ ልብ የነበረው ሰው ነው። የገዛ ታናሽ ወንድሙን የአቤልን ሕይወት በማጥፋት ነፍሰ ገዳይ መሆኑን አሳይቷል። (ዘፍጥረት 4:​8) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ትንቢቱ አምላክ ብቻ ሊያብራራው የሚችለውን ጥልቅ ምሳሌያዊ ትርጉም ያዘለ ነበር። ደግሞም አምላክ በየጊዜው ደረጃ በደረጃ አብራርቶታል። በዚህም ሆነ በዚያ 66ቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የመጀመሪያው ትንቢት ያዘለው ትርጉም ግልጽ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

እባቡ ማን ነው?

6-8. ከእባቡ በስተጀርባ የነበረውን ኃይል ማንነት እንድናስተውል የሚረዱን የትኞቹ የኢየሱስ ቃላት ናቸው? አብራራ።

6 በመጀመሪያ ደረጃ በዘፍጥረት 3:​15 ላይ የተጠቀሰው እባብ ማን ነው? ዘገባው በኤደን ውስጥ አንድ እባብ ሔዋንን ቀርቦ እንዳነጋገራት ይገልጻል፤ ሆኖም እባቦች መናገር አይችሉም። ስለዚህ ከበስተጀርባ ሆኖ እባቡ እንዲናገር ያደረገ ሌላ ኃይል መኖር አለበት። ይህ ኃይል ምንድን ነበር? ኢየሱስ በዚህች ምድር ላይ አገልግሎቱን እስካከናወነበት እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ የዚህ ኃይል ማንነት ግልጽ አልነበረም።

7 በአንድ ወቅት ኢየሱስ የአብርሃም ልጆች ነን በማለት ይኩራሩ ከነበሩ ተመጻዳቂ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጋር ሲነጋገር ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ይሰብከው የነበረውን እውነት ለመቀበል በግትርነት አሻፈረን ብለው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”​—⁠ዮሐንስ 8:​44

8 እነዚህ የኢየሱስ ቃላት ኃይለኛና ቀጥተኛ ነበሩ። ዲያብሎስን “ነፍሰ ገዳይ” እና ‘የሐሰት አባት’ ሲል ጠርቶታል። በጽሑፍ ሰፍሮ የምናገኘው የመጀመሪያው ውሸት እባቡ በኤደን የተናገረው ውሸት ነው። ይህንን ውሸት የተናገረው ማንም ይሁን ማን በእውነትም “የሐሰት አባት” መባሉ ተገቢ ነው። ከዚህም ሌላ ይህ ውሸት አዳምና ሔዋን እንዲሞቱ ምክንያት ስለሆነ ይህ የመጀመሪያው ሐሰተኛ ነፍሰ ገዳይም ሆኗል። ከዚህ በግልጽ እንደምንረዳው በኤደን ገነት ከእባቡ በስተጀርባ የነበረው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ይሖዋም ያንን ጥንታዊ ትንቢት የተናገረው ለሰይጣን ነበር።

9. ሰይጣን ከየት መጣ?

9 አንዳንድ ሰዎች አምላክ ክፋት የሌለበት ከሆነ እንደ ዲያብሎስ ያለ ፍጡር ለምን ፈጠረ? ብለው ይጠይቃሉ። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ለዚህ ጥያቄም የሚሆን መልስ ይዘዋል። ኢየሱስ ስለ ሰይጣን ሲገልጽ “እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር” ብሏል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በመሆኑም ሰይጣን መሆን የጀመረው በኤደን ለሔዋን ውሸት በነገራት ጊዜ ነበር። ሰይጣን የሚለው ቃል “ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። ቀደም ሲል የታመነ የነበረ አንድ መልአክ በልቡ የተሳሳተ ምኞት እንዲያድግ በመፍቀዱ ምክንያት ሰይጣን ሆነ እንጂ አምላክ ሰይጣን አድርጎ አልፈጠረውም።​—⁠ዘዳግም 32:​4፤ ከኢዮብ 1:​6-12፤ 2:​1-10፤ ያዕቆብ 1:​13-15 ጋር አወዳድር።

የእባቡ ዘር

10, 11. ኢየሱስና ሐዋርያው ዮሐንስ የእባቡን ዘር ማንነት እንድናውቅ የሚረዱን እንዴት ነው?

10 ይሁንና ስለ እባቡ ዘርስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ይህንን የእንቆቅልሹን ክፍልም ለመፍታት ይረዱናል። እነዚያን የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች “እናንተ ከአባታችሁ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ” ብሏቸዋል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እነዚህ አይሁዳውያን በእርግጥም እንዳሉት የአብርሃም ዘር ነበሩ። ይሁን እንጂ የክፋት አድራጎታቸው የኃጢአት ምንጭ የሆነው የሰይጣን መንፈሳዊ ልጆች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

11 ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲጽፍ የእባቡ ማለትም የሰይጣን ዘር የሚሆኑት እነማን እንደሆኑ በግልጽ አስረድቷል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፣ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። . . . የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።” (1 ዮሐንስ 3:​8, 10) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የእባቡ ዘር በሰው ልጅ ታሪክ ሁሉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ኖሯል!

የሴቲቱ ዘር ማን ነው?

12, 13. (ሀ) ይሖዋ የሴቲቱ ዘር ከልጆቹ መካከል እንደሚገኝ ለአብርሃም የገለጸለት እንዴት ነው? (ለ) ዘሩን በተመለከተ የተሰጠውን የተስፋ ቃል የወረሰው ማን ነው?

12 ታዲያ ‘የሴቲቱ ዘር’ ማን ነው? የሰይጣንን ራስ በመቀጥቀጥ የመጀመሪያው ዓመፅ ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች በሙሉ የሚያስወግደው የሴቲቱ ዘር በመሆኑ ይህ ጥያቄ እስከ ዛሬ ድረስ ከተነሡት ጥያቄዎች ሁሉ ይበልጥ አንገብጋቢ ነው። በ20ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አምላክ ታማኝ ሰው ለነበረው ለአብርሃም ስለዚህ ዘር ማንነት ጎላ ያለ ፍንጭ ሰጥቶታል። አብርሃም ትልቅ እምነት ስለነበረው ለእርሱ የሚወለድለትን ልጅ በተመለከተ አምላክ በተከታታይ ቃል ገብቶለታል። ከተገባለት ቃል መካከል አንዱ ‘የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው’ ‘የሴቲቱ ዘር’ ከአብርሃም ልጆች መካከል እንደሚወጣ የሚገልጽ ነበር። አምላክ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ዘርህም የጠላቶችህን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፣ ቃሌን ሰምተሃልና።”​—⁠ዘፍጥረት 22:​17, 18

13 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይሖዋ ለአብርሃም የገባውን ቃል ለአብርሃም ልጅ ለይስሐቅ ከዚያም ለልጅ ልጁ ለያዕቆብ በድጋሚ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 26:​3-5፤ 28:​10-15) በኋላም የያዕቆብ ልጆች አሥራ ሁለት ነገድ በሆኑ ጊዜ ይሁዳ አንድ ልዩ የተስፋ ቃል ተሰጠው። “በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፣ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፣ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል።” (ዘፍጥረት 49:​10) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ዘሩ የሚመጣው በይሁዳ ነገድ በኩል ነበር።

14. ለዘሩ መምጣት ዝግጅት ለማድረግ የተደራጀው ብሔር የትኛው ነው?

14 በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጨረሻ ላይ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች የአምላክ ልዩ ሕዝብ በመሆን በብሔር ደረጃ ተዋቀሩ። አምላክም ይህን ለማድረግ ሲል ከእነርሱ ጋር በቃል ኪዳን ተሳሰረ፤ ሕግም ሰጣቸው። ይህንን ያደረገበት ዋነኛው ምክንያት ለዘሩ መምጫ የሚሆን ሕዝብ ለማዘጋጀት ነበር። (ዘጸአት 19:​5, 6፤ ገላትያ 3:​24) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሰይጣን ለሴቲቱ ዘር ያለው ጥላቻ አሕዛብ ለተመረጡት የአምላክ ሕዝቦች በሚያሳዩት ጥላቻ ይንጸባረቅ ጀመር።

15. ከአብርሃም ዝርያዎች መካከል ዘሩ የሚገኝበትን ቤተሰብ በሚመለከት ምን የመጨረሻ ፍንጭ ተሰጥቷል?

15 ዘሩ ከየትኛው ቤተሰብ እንደሚገኝ የሚጠቁመው የመጨረሻው ፍንጭ የተገኘው በ11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነበር። በዚያ ወቅት አምላክ የእስራኤል ሁለተኛ ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት ዘሩ በእርሱ መስመር እንደሚመጣና ዙፋኑም ‘ለዘላለም እንደሚጸና’ ገለጸለት። (2 ሳሙኤል 7:​11-16) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ይህ ዘር የዳዊት ልጅ ተብሎ ሊጠራ ችሏል።​—⁠ማቴዎስ 22:​42-45

16, 17. ኢሳይያስ ዘሩ የሚያስገኛቸውን በረከቶች የገለጸው እንዴት ነው?

16 ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታትም አምላክ በመንፈስ ተነሳስተው ስለ መጪው ዘር ተጨማሪ መረጃዎችን የሚሰጡ ነቢያትን አስነሥቷል። ለምሳሌ ያህል በስምንተኛው መቶ ዘመን ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። . . . በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።”​—⁠ኢሳይያስ 9:​6, 7

17 ኢሳይያስ ይህንኑ ዘር በሚመለከት ተጨማሪ ትንቢት ተናግሯል:- “ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ . . . ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ . . . በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:​4-9) እንዴት ያሉ የተትረፈረፉ በረከቶችን የሚያስገኝ ዘር ነው!

18. ዳንኤል ዘሩን በሚመለከት ምን ተጨማሪ መረጃ ዘግቧል?

18 በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ዳንኤል ስለዚህ ዘር ተጨማሪ ትንቢት ተናግሯል። የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ የሚታይበት ጊዜ እንደሚመጣ ከገለጸ በኋላ “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩም ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው” ብሏል። (ዳንኤል 7:​13, 14) በመሆኑም ይህ መጪው ዘር ሰማያዊ መንግሥት የሚወርስ ከመሆኑም ሌላ ንጉሣዊ ሥልጣኑ መላዋን ምድር የሚጠቀልል ይሆናል።

እንቆቅልሹ ተፈታ

19. መልአኩ እንደገለጸው ማርያም በዘሩ አመጣጥ ረገድ የምትጫወተው ሚና ምን ነበር?

19 የሴቲቱ ዘር ማንነት ከብዙ ጊዜ በኋላ በዘመናችን አቆጣጠር መባቻ ላይ ተገለጠ። በ2 ከዘአበ አንድ መልአክ ከዳዊት ዘር ለሆነች ማርያም ለምትባል አንዲት አይሁዳዊት ወጣት ተገለጠላት። መልአኩ አንድ ልዩ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ከገለጸላት በኋላ እንዲህ አለ:- “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:​32, 33) በመሆኑም ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የነበረው “ዘር” በመጨረሻ ተገለጠ።

20. የተስፋው ዘር ማን ነው? በእስራኤልስ ምን መልእክት ሰብኳል?

20 በ29 እዘአ (ይህን ዘመን በሚመለከት ዳንኤል ከረጅም ዘመን በፊት ተናግሮ ነበር) ኢየሱስ ተጠመቀ። በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደበት፤ አምላክም ልጁ መሆኑን አሳወቀ። (ዳንኤል 9:​24-27፤ ማቴዎስ 3:​16, 17) ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” እያለ ለአይሁዳውያን ሲያውጅ ቆይቷል። (ማቴዎስ 4:​17) በዚህ ወቅት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ትንቢቶችን በማስፈጸሙ የተስፋው ዘር እርሱ መሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አልነበረም።

21. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የዘሩን ማንነት በሚመለከት ምን ነገር ተረድተው ነበር?

21 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ነገር በሚገባ ተረድተው ነበር። ጳውሎስ በገላትያ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል አስረድቷል:- “ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር:- ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን:- ለዘርህም ይላል፣ እርሱም ክርስቶስ።” (ገላትያ 3:​16) ኢሳይያስ ­አስቀድሞ የተናገረለት “የሰላም አለቃ” ኢየሱስ ነው። በመጨረሻ በመንግሥቱ ሲመጣ በዓለም ዙሪያ ጽድቅና ፍትሕ ይሰፍናል።

ታዲያ ሴቲቱ ማን ነች?

22. በኤደን በተነገረው የይሖዋ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰችው ሴት ማን ነች?

22 ዘሩ ኢየሱስ ከሆነ ታዲያ በኤደን የተጠቀሰችው ሴት ማን ነች? ከእባቡ በስተጀርባ የነበረው ኃይል መንፈሳዊ ፍጥረት ስለነበር ሴቲቱም ሰብዓዊ ፍጥረት ሳትሆን መንፈሳዊ መሆኗ ሊያስገርመን አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት” ባለ ጊዜ ስለ አንዲት ሰማያዊት ‘ሴት’ እየተናገረ ነበር። (ገላትያ 4:​26) “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ለብዙ ሺህ ዓመታት እንደኖረች ከሌሎች ጥቅሶች መረዳት እንችላለን። ይህች ሴት መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችው የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት ስትሆን ኢየሱስ ‘የሴቲቱ ዘር’ በመሆን ተልእኮውን ለመፈጸም የመጣው ከዚያው ነው። ‘በቀደመው እባብ’ እና በእርሷ መካከል ያለው ጠላትነት ለብዙ ሺህ ዓመታት ሊዘልቅ የሚችለው መንፈሳዊ “ሴት” ከሆነች ብቻ ነው።​—⁠ራእይ 12:​9፤ ኢሳይያስ 54:​1, 13፤ 62:​2-6

23. ይሖዋ በኤደን የተናገረው ትንቢት ትርጉም ደረጃ በደረጃ እየተገለጠ መሄዱ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

23 በዘፍጥረት 3:​15 ላይ የሚገኘው ጥንታዊ ትንቢት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዴት ግልጽ እየሆነ እንደመጣ በአጭሩ የተመለከትነው ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ስምምነት የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው። ትንቢቱን መረዳት የቻልነው በ20ኛው፣ በ11ኛው፣ በ8ኛው እንዲሁም በ6ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተከናወኑትንና የተነገሩትን ነገሮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ከተደረጉትና ከተነገሩት ነገሮች ጋር በማጣመር መሆኑ በእርግጥም አስገራሚ ያደርገዋል። ይህ እንዲሁ ባጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም። ይህን እንዲሆን ያቀነባበረው ወገን መኖር አለበት።​—⁠ኢሳይያስ 46:​9, 10

ለእኛ የሚኖረው ትርጉም

24. የዘሩ ማንነት መገለጥ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

24 ይህ ሁሉ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ‘የሴቲቱ ዋነኛ ዘር’ ኢየሱስ ነው። በዘፍጥረት 3:​15 ላይ የሚገኘው ጥንታዊ ትንቢት ተረከዙ በእባቡ ‘እንደሚቀጠቀጥ’ አስቀድሞ ገልጾ ነበር። ይህም ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ በሞተ ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። ተረከዙ ላይ መቀጥቀጡ ዘላቂ ጉዳት የሚያመጣ ነገር አልነበረም። በመሆኑም ኢየሱስ ትንሣኤ ሲያገኝ እባቡ ያገኘው ይመስል የነበረው ድል ወደ ሽንፈት ተለወጠ። (በምዕራፍ 6 ላይ እንዳየነው የኢየሱስን ትንሣኤ የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃዎች አሉ።) የኢየሱስ መሞት ቅን ልብ ያላቸው የሰው ልጆች መዳን እንዲያገኙ የሚያስችል መሠረት በመጣሉ አምላክ ለአብርሃም ቃል እንደገባለት ዘሩ በረከት ሆኗል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰማያዊ መንግሥት ይዞ ምድራዊ ግዛቱን በሙሉ እንደሚቆጣጠር የሚናገሩት ትንቢቶችስ?

25, 26. በራእይ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው ‘በሴቲቱ ዘርና’ በእባቡ መካከል ያለው ጠላትነት ምን ነገሮችን ይጨምራል?

25 በራእይ ምዕራፍ 12 ላይ ተገልጾ በምናገኘው ግልጽ ትንቢታዊ መግለጫ ውስጥ የዚህ መንግሥት አጀማመር አንድ ወንድ ልጅ በሰማይ ከመወለዱ ጋር ተመሳስሏል። የተስፋው ዘር “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም ያለው ሚካኤል የሚል የማዕረግ ስም ተሰጥቶት በዚህ መንግሥት ውስጥ ሥልጣኑን ይረከባል። ‘የቀደመውን እባብ’ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሰማይ በመጣል ማንም የይሖዋን ሉዓላዊነት ሊገዳደር እንደማይችል ያሳያል። እንዲህ እናነባለን:- “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ።”​—⁠ራእይ 12:​7-9

26 ይህም በሰማይ እፎይታ እንዲሰፍን ሲያደርግ በምድር ላይ ወዮታን አስከትሏል። “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ” የሚል የድል ድምፅ ተሰምቷል። ከዚህም በመቀጠል እንዲህ የሚል ቃል እናነባለን:- “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”​—⁠ራእይ 12:​10, 12

27. ሰይጣን ከሰማይ እንደሚጣል የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነው? እንዴት እናውቃለን?

27 ይህ ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ እንደሆነ መናገር እንችላለንን? በምዕራፍ 10 ውስጥ እንደተወያየነው ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ጠጋ ብለው ‘የመገኘቱና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቱ’ ምን እንደሚሆን ሲጠይቁ ይህንኑ ጥያቄ ማንሳታቸው ነበር። (ማቴዎስ 24:​3 NW) ቀደም ሲል እንዳየነው ኢየሱስ በ1914 የሰማያዊ መንግሥቱን ሥልጣን እንደጨበጠ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። በእርግጥም ከዚያ ጊዜ አንስቶ ‘በምድር ላይ ወዮታ’ ሆኗል!

28, 29. ገና ወደፊት በምድር ላይ የሚካሄዱት ታላላቅ ለውጦች ምንድን ናቸው? በቅርቡ እንደሚከናወኑስ እንዴት እናውቃለን?

28 ይሁን እንጂ አንድ ነገር አስተውል:- ከሰማይ የተሰማው ታላቅ ድምፅ ሰይጣን “ጥቂት ጊዜ” ብቻ እንደቀረው አስታውቋል። በመሆኑም በዘፍጥረት 3:​15 ላይ የተገለጸው የመጀመሪያ ትንቢት ወደማይቀረው ታላቅ መደምደሚያው እየገሰገሰ ነው። እባቡና የእርሱ ዘር እንዲሁም ሴቲቱና የእርሷ ዘር እነማን መሆናቸው ታውቋል። ዘሩ ‘ተረከዙ ተቀጥቅጦ’ ነበር፤ ይሁን እንጂ ድኗል። በቅርቡ ደግሞ አሁን በመግዛት ላይ ባለው ንጉሥ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰይጣን (ከነዘሩ) ይቀጠቀጣል።

29 ይህም በምድርም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል። ሰይጣንና የእርሱ ዘር ለመሆን የመረጡ ሁሉ ይጠፋሉ። መዝሙራዊው አስቀድሞ እንደተናገረው “ገና ጥቂት ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።” (መዝሙር 37:​10) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ለውጥ ይሆናል! ከዚህ በኋላ መዝሙራዊው የተናገራቸው ተጨማሪ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ:- “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”​—⁠መዝሙር 37:​11

30. ከእውነታው የራቁት መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በመንፈስ አነሳሽነት ነው በሚለው ሐሳብና በአምላክ መኖር ላይ እንኳ ሳይቀር የጥርጣሬ ደመና እንዲያጠላ የሚያደርጉት ሰዎች ራሳቸው ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

30 ‘የሰላሙ ገዥ’ በመጨረሻ በዚህ ሁኔታ ለሰው ልጅ ሰላም ያጎናጽፈዋል። በኢሳይያስ 9:​6, 7 ላይ እንዳየነው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ ነው። በዚህ የጥርጣሬ መንፈስ በተጠናወተው ዓለም ብዙዎች እንዲህ ያለውን ተስፋ ከእውነታው የራቀ ሆኖ ይታያቸዋል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የሚያቀርበው ምን ሌላ አማራጭ አለ? ምንም አማራጭ የለም! በአንጻሩ ግን ይህ ተስፋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የሚናገረው ሁሉ መሬት ጠብ የማይል የአምላክ ቃል ነው። በእርግጥም ከእውነታው የራቁት ይህን የሚጠራጠሩት ሰዎች ናቸው። (ኢሳይያስ 55:​8, 11) መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ አማካኝነት ላስጻፈውና ከሁሉ በላይ ለሆነው አካል ለአምላክ ጀርባቸውን ሰጥተዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 151 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ችግር ላይ ለወደቀው የሰው ልጅ ተስፋ ሰጥቶታል

[በገጽ 154 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተስፋው ዘር የሚመጣው በአብርሃም ዝርያዎች በኩል መሆኑን በ20ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይሖዋ ለአብርሃም ነግሮታል

[በገጽ 155 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሥ ዳዊት ዘሩ በእርሱ የንግሥና መስመር በኩል እንደሚመጣ በ11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ተነግሮታል

[በገጽ 156 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ኢሳይያስ ዘሩ የሚያስገኛቸውን በረከቶች ገልጿል

[በገጽ 157 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዘሩ በሰማያዊ መንግሥት እንደሚገዛ ዳንኤል በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አስታውቋል

[በገጽ 159 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርያም የአንደኛው መቶ ዘመን እዘአ መባቻ ሲቃረብ ዘሩ እርሷ የምትወልደው ኢየሱስ የሚባለው ወንድ ልጅ እንደሚሆን አውቃ ነበር