በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ተጨማሪ ክፍል

‘ታላቂቱ ባቢሎንን’ ለይቶ ማወቅ

‘ታላቂቱ ባቢሎንን’ ለይቶ ማወቅ

የራእይ መጽሐፍ ቃል በቃል ሳይሆን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ልንረዳቸው የሚገቡ አገላለጾችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል በግምባሯ ላይ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል ስም የተጻፈባትን አንዲት ሴት ይጠቅሳል። ይህች ሴት ‘በብዙ ሰዎችና በሕዝቦች’ ላይ እንደተቀመጠች ተገልጿል። (ራእይ 17:1, 5, 15) ቃል በቃል ይህን ልታደርግ የምትችል ሴት ስለሌለች ታላቂቱ ባቢሎን ምሳሌያዊት መሆን አለባት። ታዲያ ይህች ምሳሌያዊት አመንዝራ የምታመለክተው ማንን ነው?

ራእይ 17:18 ላይ ይህችው ምሳሌያዊት ሴት “በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ” ተብላ ተገልጻለች። “ከተማ” የሚለው ቃል  የተደራጀ የሰዎች ቡድንን ያመለክታል። “ታላቂቱ ከተማ” ‘የምድር ነገሥታትን’ የምትቆጣጠር በመሆኗ ታላቂቱ ባቢሎን ተብላ የተጠራችው ሴት ዓለም አቀፋዊ ስፋትና ከፍተኛ ተሰሚነት ያላት ድርጅት መሆን አለባት። ስለዚህ ዓለም አቀፋዊ ግዛት ናት ልትባል ትችላለች። ምን ዓይነት ግዛት ናት? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ሃይማኖታዊ የሚል ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ጥቅሶች ወደዚህ መደምደሚያ እንድንደርስ የሚያደርጉን እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

አንድ ግዛት የፖለቲካ፣ የንግድ ወይም የሃይማኖት ግዛት ሊሆን ይችላል። የአምላክ ቃል “የምድር ነገሥታት” ወይም የዚህ ዓለም የፖለቲካ ኃይሎች ከእሷ ጋር ‘እንዳመነዘሩ’ ስለሚናገር ታላቂቱ ባቢሎን ተብላ የተጠራችው ይህች ሴት የፖለቲካ ግዛት ልትሆን አትችልም። ዝሙቷ ከምድር ገዥዎች ጋር የፈጠረችውን ኅብረት የሚያመለክት ከመሆኑም በላይ ‘ታላቂቱ አመንዝራ’ የተባለችው ለምን እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል።—ራእይ 17:1, 2፤ ያዕቆብ 4:4

የንግዱን ዓለም የሚወክሉት “የምድርም ነጋዴዎች” ጥፋት በሚደርስባት ወቅት የሚያለቅሱላት በመሆኑ ታላቂቱ ባቢሎን የንግድ ግዛት ልትሆን አትችልም። እንዲያውም ነገሥታትም ሆኑ ነጋዴዎች ታላቂቱ ባቢሎንን “በሩቅ” ሆነው እንደሚመለከቷት ተደርጎ ተገልጿል። (ራእይ 18:3, 9, 10, 15-17) ስለዚህ ታላቂቱ ባቢሎን የፖለቲካ ወይም የንግድ ግዛት ሳትሆን ሃይማኖታዊ ግዛት ነች ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቦችን ‘በአስማቷ’ እንደምታስት የሚገልጸው ሐሳብ ታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖታዊ ግዛት እንደሆነች ይበልጥ ያረጋግጥልናል። (ራእይ 18:23) ሁሉም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊቶች ሃይማኖታዊና አጋንንታዊ በመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ታላቂቱ ባቢሎንን “የአጋንንት መኖሪያ” ብሎ መጥራቱ ምንም አያስደንቅም። (ራእይ 18:2፤ ዘዳግም 18:10-12) ይህች ግዛት ‘ነቢያትንና ቅዱሳንን’ በማሳደድ እውነተኛውን ሃይማኖት አጥብቃ እንደምትቃወምም ተገልጿል። (ራእይ 18:24) እንዲያውም ታላቂቱ ባቢሎን ለእውነተኛ ሃይማኖት ከፍተኛ ጥላቻ ያላት በመሆኑ “በኢየሱስ ምስክሮች” ላይ ከፍተኛ ስደት ታደርሳለች አልፎ ተርፎም ግድያ ትፈጽማለች። (ራእይ 17:6) ስለዚህ ታላቂቱ ባቢሎን ተብላ የተጠራችው ይህች ሴት ይሖዋ አምላክን የሚጻረሩ ሃይማኖቶችን በሙሉ የሚያጠቃልለውን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት እንደምታመለክት በግልጽ መረዳት ይቻላል።