በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ አሥራ ስድስት

ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ቁም

ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ቁም
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን በተመለከተ ምን ይላል?

  • ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ በዓላትን በተመለከተ ምን አመለካከት አላቸው?

  • ሌሎችን ቅር ሳታሰኝ ስለ እምነትህ ማስረዳት የምትችለው እንዴት ነው?

1, 2. የሐሰት ሃይማኖትን ለቅቀህ ከወጣህ በኋላ ራስህን ምን ብለህ መጠየቅ ይኖርብሃል? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የምትኖርበት ሰፈር በሙሉ ተበክሏል እንበል። አንድ ሰው በድብቅ መርዛማ የሆነ ቆሻሻ ሰፈራችሁ ውስጥ ሲጥል በመቆየቱ የአካባቢው ነዋሪ ሕይወት ለአደጋ ተጋልጧል። ይህን ስታውቅ ምን ታደርጋለህ? በተቻለ መጠን አካባቢውን ለቅቀህ ለመውጣት ጥረት እንደምታደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ይህን ካደረግክ በኋላም ‘ተመርዤ ይሆን?’ የሚለው ጥያቄ በእጅጉ እንደሚያሳስብህ የታወቀ ነው።

2 የሐሰት ሃይማኖትን በተመለከተ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው አምልኮ በረከሱ ትምህርቶችና ልማዶች የተበከለ እንደሆነ ይገልጻል። (2 ቆሮንቶስ 6:17) የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ መውጣትህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው። (ራእይ 18:2, 4) ይህን እርምጃ ወስደሃል? ወስደህ ከሆነ ጥሩ አድርገሃል። ሆኖም ከሐሰት ሃይማኖት መለየትህ ወይም መውጣትህ ብቻውን በቂ አይደለም። ይህን እርምጃ ከወሰድክ በኋላም ‘የሐሰት አምልኮ ርዝራዦች በውስጤ ቀርተው ይሆን?’ ብለህ ራስህን መጠየቅ ይኖርብሃል። አንዳንድ ምሳሌዎች ተመልከት።

 ምስሎችንና የቀድሞ አባቶችን ማምለክ

3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በምስሎች መጠቀምን በተመለከተ ምን ይላል? አንዳንዶች አምላክ ያለውን አመለካከት መቀበል ሊከብዳቸው የሚችለውስ ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) በእጅህ የሚገኙትን ከሐሰት አምልኮ ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

3 አንዳንዶች በቤታቸው ውስጥ ለብዙ ዓመታት ለአምልኮ ሲጠቀሙባቸው የኖሩ ምስሎች ወይም ለዚህ ዓላማ የተለዩ ቦታዎች ነበሯቸው። አንተስ በቤትህ ውስጥ ለአምልኮ የምትጠቀምባቸው ምስሎች ወይም ቅዱስ ስፍራዎች አሉህ? ካሉህ እንዲህ ባሉ የሚታዩ ነገሮች ሳይታገዙ ወደ አምላክ መጸለይ እንግዳ ሊሆንብህ ወይም ስህተት እንደሆነ አድርገህ ልታስብ ትችላለህ። እንዲያውም ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን በጣም ትወዳቸው ይሆናል። ሆኖም እንዴት መመለክ እንዳለበት የመወሰን መብት ያለው አምላክ ሲሆን አምላክ ደግሞ ምስሎችን እንድንጠቀም የማይፈልግ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። (ዘፀአት 20:4, 5፤ መዝሙር 115:4-8፤ ኢሳይያስ 42:8፤ 1 ዮሐንስ 5:21) ስለዚህ በእጅህ የሚገኙትን ከሐሰት አምልኮ ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ በማስወገድ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን መቆም ትችላለህ። ልክ እንደ ይሖዋ አንተም እንደ “አስጸያፊ” ነገር አድርገህ ልትመለከታቸው ይገባል።—ዘዳግም 27:15

4. (ሀ) የቀድሞ አባቶችን ማምለክ ከንቱ መሆኑን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ሕዝቡ በማንኛውም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት እንዳይካፈሉ ያዘዛቸው ለምንድን ነው?

 4 የቀድሞ አባቶችን ማምለክ በብዙዎቹ የሐሰት ሃይማኖቶች ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኝ ልማድ ነው። አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከመማራቸው በፊት ሙታን በማይታየው ዓለም ውስጥ እንደሚኖሩና ሕያዋንን ሊረዱ አሊያም ሊጎዱ እንደሚችሉ አድርገው ያምኑ ነበር። ምናልባት አንተም የሞቱትን የቀድሞ አባቶችህን ፍላጎት ለማርካት ብዙ ጥረት ታደርግ የነበርክ ሰው ልትሆን ትችላለህ። ሆኖም በዚህ መጽሐፍ ስድስተኛ ምዕራፍ ላይ እንደተማርከው ሙታን ምንም ዓይነት ሕልውና የላቸውም። በመሆኑም ከእነሱ ጋር ለመነጋገር የሚደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ነው። አንድ ሰው በሞት ካጣው ወዳጁ ወይም ዘመዱ እንደመጣ አድርጎ የሚያስበው መልእክት ሁሉ የሚመጣው ከአጋንንት ነው። በዚህ ምክንያት ይሖዋ እስራኤላውያንን ሙታንን ለማነጋገር እንዳይሞክሩ ወይም በማንኛውም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት እንዳይካፈሉ አዟቸው ነበር።—ዘዳግም 18:10-12

5. ቀደም ሲል በምስሎች ትጠቀም ወይም የቀድሞ አባቶችን ታመልክ ከነበረ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

5 ቀደም ሲል በምስሎች ትጠቀም ወይም የቀድሞ አባቶችን ታመልክ ከነበረ ምን ልታደርግ ትችላለህ? አምላክ እንዲህ ያሉ ነገሮችን በተመለከተ ምን አመለካከት እንዳለው የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማንበብ አሰላስልባቸው። ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ለመቆም ያለህን ፍላጎት በየዕለቱ በጸሎት ለይሖዋ ግለጽለት፤ እንዲሁም የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበር እንድትችል እንዲረዳህ ጠይቀው።—ኢሳይያስ 55:9

የጥንት ክርስቲያኖች ገናን አላከበሩም

6, 7. (ሀ) ገና የምን ክብረ በዓል እንደሆነ ይነገራል? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ተከታዮችስ አክብረውታል? (ለ) ጥንት በነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ዘመን የልደት በዓላት ይከበሩ የነበረው ከምን ጋር በተያያዘ ነው?

6 ተወዳጅ ከሆኑ በዓላት ጋር በተያያዘ የአንድ ሰው አምልኮ በሐሰት አምልኮ ሊበከል ይችላል። ገናን እንደ ምሳሌ ተመልከት። ገና የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚከበርበት በዓል እንደሆነ የሚነገር ሲሆን ክርስቲያን ነን የሚሉ ሃይማኖቶች በሙሉ ማለት ይቻላል፣ ይህን በዓል ያከብራሉ። ይሁንና  በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲህ ያለ በዓል ያከብሩ እንደነበረ የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። ሴክረድ ኦሪጅንስ ኦቭ ፕሮፋውንድ ቲንግስ የተባለው መጽሐፍ “ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ በነበሩት ሁለት መቶ ዘመናት መቼ እንደተወለደ የሚያውቅ ሰው አልነበረም፤ ይህን ለማወቅ ይፈልጉ የነበሩ ሰዎችም እምብዛም አልነበሩም” ሲል ይገልጻል።

7 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የተወለደበትን ትክክለኛ ቀን ቢያውቁ ኖሮም እንኳ ቀኑን አያከብሩትም ነበር። ለምን? ምክንያቱም ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚለው የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “የማንኛውንም ሰው የልደት ቀን ማክበር የአረማውያን ልማድ እንደሆነ ያምኑ ነበር።” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው የሚገኙት የልደት በዓሎች ይሖዋን የማያመልኩ ሁለት ገዥዎች ያከበሯቸው ብቻ ናቸው። (ዘፍጥረት 40:20፤ ማርቆስ 6:21) ለአረማውያን አማልክት ክብር ተብለው የሚከበሩ የልደት በዓላትም ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ሮማውያን ዳያና የተባለችውን የሴት አምላክ የልደት በዓል ግንቦት 24 ያከብሩ ነበር። በቀጣዩ ቀን ደግሞ የፀሐይ አምላካቸውን ማለትም የአፖሎን የልደት በዓል ያከብሩ ነበር። ስለዚህ የልደት ክብረ በዓላት ከክርስትና ጋር ሳይሆን ከአረማውያን እምነት ጋር የተያያዙ ናቸው።

8. በልደት በዓላትና በአጉል እምነት መካከል ያለውን ዝምድና ግለጽ።

8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የኢየሱስን ልደት ያላከበሩበት ሌላም ምክንያት አለ። ደቀ መዛሙርቱ የልደት በዓላት ከአጉል እምነቶች ጋር የተቆራኙ እንደሆኑ ሳይገነዘቡ አልቀሩም። ለምሳሌ ያህል በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ብዙዎቹ ግሪካውያንና ሮማውያን እያንዳንዱ ሰው ሲወለድ አንዲት መንፈስ እንደምትገኝና ያንን ግለሰብ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንደምትጠብቀው ያምኑ ነበር። “ይህች መንፈስ ግለሰቡ በተወለደበት ቀን የልደት በዓሉ ከሚከበርለት አምላክ ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት ነበራት” ሲል ዘ ሎር ኦቭ በርዝዴይስ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። ይሖዋ፣ ኢየሱስን ከአጉል እምነት ጋር በሚያያይዝ በየትኛውም ዓይነት ክብረ በዓል እንደማይደሰት የተረጋገጠ ነው። (ኢሳይያስ 65:11, 12) ታዲያ ብዙ ሰዎች ገናን የሚያከብሩት ለምንድን ነው?

 የገና አመጣጥ

9. ታኅሣሥ 25 የኢየሱስ ልደት የሚከበርበት ቀን እንዲሆን የተመረጠው እንዴት ነው?

9 ሰዎች የኢየሱስን ልደት ታኅሣሥ 25 ቀን ማክበር የጀመሩት ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖረ በርከት ካሉ መቶ ዓመታት በኋላ ነው። ሆኖም ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ የተወለደው በጥቅምት ወር በመሆኑ ይህ ቀን ትክክል አይደለም። * ታዲያ ታኅሣሥ 25 የተመረጠው ለምንድን ነው? ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን ነን ማለት የጀመሩ አንዳንድ ሰዎች “ቀኑ ‘ድል የማትደረገው ፀሐይ የልደት ቀን’ ከሚከበርበት የሮማውያን አረማዊ ክብረ በዓል ጋር እንዲገጣጠም ፈልገው” የነበረ ይመስላል። (ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ) በክረምት ወራት የፀሐይ ኃይል በጣም የቀነሰ በሚመስልበት ወቅት አረማውያን የሙቀትና የብርሃን ምንጭ የሆነችው ፀሐይ ከሄደችበት ሩቅ ቦታ ተመልሳ እንድትመጣ ለማድረግ ብለው የሚያከብሯቸው ክብረ በዓላት ነበሯቸው። ታኅሣሥ 25 ፀሐይ ተመልሳ ለመምጣት ጉዞዋን የምትጀምርበት ዕለት እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። የሃይማኖት መሪዎች የአረማውያንን እምነት ለማስለወጥ ሲሉ ይህን በዓል በመቀበል “የክርስቲያን” በዓል አስመስለው ለማቅረብ ሞከሩ። *

10. ቀደም ባሉት ዘመናት አንዳንድ ሰዎች ገናን ያላከበሩት ለምንድን ነው?

10 ገና ከአረማውያን የመጣ በዓል መሆኑ ከብዙ ዓመታት በፊትም ይታወቅ ነበር። ገና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሌለው በዓል በመሆኑ በ17ኛው መቶ ዘመን በእንግሊዝና በአንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች ታግዶ ነበር። እንዲያውም በገና ዕለት ከሥራ ቀርቶ ቤቱ የሚውል ሰው ይቀጣ  ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ የቀድሞዎቹ ልማዶች እንደገና ተወዳጅነት እያገኙ ከመምጣታቸውም በላይ አዳዲስ ልማዶችም ተጨመሩ። ገና እንደገና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ሆነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በብዙ አገሮች ውስጥ ተወዳጅነት ያለው በዓል ነው። ሆኖም ገና ከሐሰት ሃይማኖት ጋር የተያያዘ በመሆኑ አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ይህን በዓልም ሆነ ከአረማውያን አምልኮ የመጡ ሌሎች በዓላትን አያከብሩም። *

የበዓላት አመጣጥ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል?

11. አንዳንድ ሰዎች በዓላትን የሚያከብሩት ለምንድን ነው? ሆኖም በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

11 አንዳንዶች እንደ ገና ያሉ በዓላት ከአረማውያን የመጡ መሆናቸውን ቢያምኑም እነዚህን በዓላት ማክበሩ ምንም ስህተት እንደሌለው ይሰማቸዋል። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች በዓላትን ሲያከብሩ ስለ ሐሰት አምልኮ አያስቡም። በተጨማሪም እነዚህ ወቅቶች ቤተሰቦችን እርስ በርስ ለማቀራረብ የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥራሉ። አንተም የሚሰማህ እንደዚህ ነው? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን መቆም ከባድ መስሎ እንዲታይህ እያደረገ ያለው ለሐሰት ሃይማኖት ያለህ ፍቅር ሳይሆን ለቤተሰብ ያለህ ፍቅር ሊሆን ይችላል። የቤተሰብ መሥራች የሆነው ይሖዋ ከቤተሰብህ አባላት ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖርህ እንደሚፈልግ እርግጠኛ ሁን። (ኤፌሶን 3:14, 15) ሆኖም እንዲህ ያለውን ዝምድና አምላክ በሚቀበለው መንገድ ማጠናከር ትችላለህ። ሐዋርያው ጳውሎስ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ ሲገልጽ “ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ” ሲል ጽፏል።—ኤፌሶን 5:10

ቦይ ውስጥ የወደቀ ከረሜላ አንስተህ ትበላለህ?

12. መጥፎ አመጣጥ ያላቸውን ልማዶችና በዓላት ማስወገድ ያለብን ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

12 የበዓላት አመጣጥ በዛሬው ጊዜ በዓላቱ ከሚከበሩበት ሁኔታ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ብለህ ታስብ ይሆናል። የበዓላት አመጣጥ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል? አዎን፣ ለውጥ ያመጣል! ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ቦይ ውስጥ የወደቀ ከረሜላ አየህ እንበል። ከረሜላውን አንስተህ ትበላዋለህ? እንደማትበላው የታወቀ ነው! ምክንያቱም ከረሜላው ቆሽሿል። ልክ እንደ ከረሜላው በዓላትም ሊያጓጉ ቢችሉም  እንኳ ከቆሻሻ ቦታ የተገኙ ናቸው። ከእውነተኛው አምልኮ ጎን መቆም እንድንችል “ርኵስ ነገር አትንኩ” ሲል እውነተኛ አምላኪዎችን ያሳሰበውን የነቢዩ ኢሳይያስን አመለካከት መኮረጅ አለብን።—ኢሳይያስ 52:11

ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት አስተዋይ ሁን

13. በበዓላት ላለመካፈል በምትወስንበት ጊዜ ምን ፈታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ?

13 በበዓላት ላለመካፈል ስትወስን አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል አብረውህ የሚሠሩ ሰዎች ከበዓላት ጋር በተያያዘ በሥራ ቦታህ በሚካሄዱ አንዳንድ ዝግጅቶች የማትካፈልበት ምክንያት ግራ ሊገባቸው ይችላል። እንበልና የገና ስጦታ ቢቀርብልህ ምን ታደርጋለህ? ስጦታውን መቀበል ስህተት ነው? የትዳር ጓደኛህ የአንተ ዓይነት እምነት ባይኖራትስ? ልጆችህ በዓላትን ባለማክበራቸው የቀረባቸው ነገር እንዳለ እንዳይሰማቸው ምን ልታደርግ ትችላለህ?

14, 15. በበዓል ሰሞን አንድ ሰው እንኳን አደረሰህ ቢልህ ወይም ስጦታ ሊሰጥህ ቢፈልግ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

14 እያንዳንዱን ሁኔታ እንዴት ልትወጣው እንደምትችል ለማገናዘብ አስተዋይ መሆን ያስፈልጋል። ከአንድ ሰው ጋር በአጋጣሚ ስትገናኝ እንኳን አደረሰህ ቢልህ መልካም ምኞቱን የገለጸልህን ሰው ልታመሰግነው ትችላለህ። ይሁንና እንዲህ ያለህ ሰው አዘውትረህ የምታገኘው ወይም አብሮህ የሚሠራ ሰው ከሆነ ተጨማሪ ሐሳብ መስጠት ትፈልግ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ዘዴኛ መሆንህ በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን” ሲል ምክር ይሰጣል። (ቈላስይስ 4:6) ለሌሎች ንቀት እንዳታሳይ ተጠንቀቅ። ከዚህ ይልቅ አቋምህን በዘዴ ግለጽ። ስጦታ መለዋወጡንም ሆነ አንድ ላይ ተሰባስቦ መጫወቱን እንደማትቃወም ሆኖም እንዲህ ባሉት እንቅስቃሴዎች በሌላ ጊዜ ብትካፈል እንደምትመርጥ በግልጽ ንገራቸው።

15 አንድ ሰው ስጦታ ሊሰጥህ ቢፈልግስ? ይህ በአብዛኛው በሁኔታዎቹ ላይ የተመካ ነው። ሰጪው “በዓሉን እንደማታከብር አውቃለሁ። ሆኖም ይህን ስጦታ ብትቀበለኝ ደስ ይለኛል” ሊልህ ይችላል። እንዲህ ባለው ሁኔታ ስጦታውን መቀበል በበዓሉ እንደመካፈል ሊያስቆጥር እንደማይችል በማሰብ ስጦታውን ለመቀበል ልትወስን ትችል ይሆናል። እርግጥ  ስጦታውን ያቀረበልህ ሰው እምነቶችህን የማያውቅ ከሆነ በዓሉን እንደማታከብር ልትገልጽለት ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ስጦታ ብትቀበልም እንኳ በዚያ ወቅት ስጦታ የማትሰጥበትን ምክንያት እንዲገነዘብ ሊያደርገው ይችላል። በሌላ በኩል ግን እምነትህን አጥብቀህ እንደማትከተል ወይም ለቁሳዊ ጥቅም ስትል አቋምህን እንደምታላላ ለማሳየት ተብሎ የሚሰጥህን ስጦታ መቀበል አይኖርብህም።

ከቤተሰብህ አባላት ጋር ባለህ ግንኙነትስ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

16. ከበዓላት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ዘዴኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

16 የቤተሰብህ አባላት የአንተ ዓይነት እምነት ባይኖራቸውስ? አሁንም ዘዴኛ መሆን ያስፈልግሃል። ቤተሰቦችህ የሚያከብሩትን እያንዳንዱን ልማድ ወይም በዓል እያነሱ መከራከር አያስፈልግም። የራስህን አመለካከት የመከተል መብትህን እንዲያከብሩልህ እንደምትፈልግ ሁሉ አንተም የእነሱን መብት አክብርላቸው። (ማቴዎስ 7:12) የበዓሉ ተካፋይ እንድትሆን ሊያደርጉህ ከሚችሉ ድርጊቶች ራቅ። ሆኖም በበዓሉ እንደተካፈልክ በማያስቆጥሩ ጉዳዮች ረገድ ምክንያታዊ መሆን ያስፈልግሃል። እርግጥ ነው፣ ምንጊዜም ቢሆን የምታደርገው ነገር ሕሊናህን የሚያቆሽሽ መሆን የለበትም።—1 ጢሞቴዎስ 1:18, 19

17. ልጆችህ ሌሎች ሰዎች በዓላትን ሲያከብሩ ሲያዩ የቀረባቸው ነገር እንዳለ ሆኖ እንዳይሰማቸው ልትረዳቸው የምትችለው እንዴት ነው?

17 ልጆችህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌላቸውን በዓላት ባለማክበራቸው የቀረባቸው ነገር እንዳለ እንዳይሰማቸው ምን ልታደርግ ትችላለህ? ይህ በአብዛኛው በዓመቱ ውስጥ ከበዓላት ውጪ ባሉት ጊዜያት በምታደርገው ነገር ላይ የተመካ ነው። አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ስጦታ የሚሰጡበት ዝግጅት ያደርጋሉ። ለልጆችህ ልትሰጣቸው ከምትችላቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀውን ቦታ የሚይዘው ለእነሱ የምትመድበው ጊዜና የምታሳያቸው ፍቅራዊ አሳቢነት ነው።

እውነተኛውን አምልኮ ተከተል

እውነተኛውን አምልኮ መከተል እውነተኛ ደስታ ያስገኛል

18. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን እንድትቆም ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

18 አምላክን ማስደሰት እንድትችል ከሐሰት አምልኮ በመራቅ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን መቆም አለብህ። ይህ ምን ነገርን ይጨምራል? መጽሐፍ  ቅዱስ “እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ” ሲል ይገልጻል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ ለማምለክ የሚያስችሉህ አስደሳች ወቅቶች ናቸው። (መዝሙር 22:22፤ 122:1) ታማኝ ክርስቲያኖች እንዲህ ባሉ ስብሰባዎች ላይ ‘እርስ በርስ ይበረታታሉ።’—ሮሜ 1:12

19. ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርከውን ነገር ለሌሎች መናገርህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

19 ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ልትቆም የምትችልበት ሌላው መንገድ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና የቀሰምካቸውን ትምህርቶች ለሌሎች በመናገር ነው። ብዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እየተፈጸመ ባለው ክፋት ‘እያዘኑና እያለቀሱ’ ነው። (ሕዝቅኤል 9:4) ምናልባትም እንዲህ ያለ ስሜት እየተሰማቸው ያሉ አንዳንድ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል። የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ያለህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋ ለምን አትነግራቸውም? ምናልባት አሁንም በልብህ ውስጥ የቀረ የሐሰት አምልኮ ልማዶችን የመከተል ፍላጎት ካለ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር ስትሰበሰብና የተማርካቸውን አስደናቂ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለሌሎች ስትናገር ቀስ በቀስ ይወገዳል። ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ከቆምክ በጣም ደስተኛ እንደምትሆንና ብዙ በረከቶች እንደምታገኝ እርግጠኛ ሁን።—ሚልክያስ 3:10

^ አን.9 የሳተርኔሊያ በዓልም ታኅሣሥ 25 የኢየሱስ ልደት የሚከበርበት ቀን ሆኖ እንዲመረጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። ለሮማውያን የእርሻ አምላክ ክብር የሚደረገው ይህ በዓል ከታኅሣሥ 17-24 ድረስ ይከበር ነበር። በሳተርኔሊያ ክብረ በዓል ወቅት ትልቅ ድግስና ፈንጠዝያ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሰዎች ስጦታ ይሰጣጡ ነበር።

^ አን.10 እውነተኛ ክርስቲያኖች ተወዳጅነት ያላቸውን ሌሎች በዓላት በተመለከተ ምን አመለካከት እንዳላቸው የሚገልጽ ማብራሪያ ለማግኘት ከገጽ 222-223 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።