በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ተጨማሪ ክፍል

ሲኦል ምንድን ነው?

ሲኦል ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ሺኦል የተባለውን የዕብራይስጥ ቃልና ተመሳሳይ ትርጉም ያለውን ሔዲስ የተባለውን የግሪክኛ ቃል ከ70 ጊዜ በላይ ይጠቀማል። ሁለቱም ቃላት ከሞት ጋር የተያያዙ ናቸው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እነዚህን ቃላት “መቃብር” ወይም “ጉድጓድ” ብለው ተርጉመዋቸዋል። ይሁን እንጂ በአብዛኞቹ ቋንቋዎች የእነዚህን የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ትክክለኛ ትርጉም የሚያስተላልፉ ቃላት የሉም። ታዲያ እነዚህ ቃላት ትክክለኛ ትርጉማቸው ምንድን ነው? በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ እንዴት እንደተሠራባቸው እስቲ እንመልከት።

መክብብ 9:10 [የ1954 ትርጉም] “አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም” ይላል። ይህ ማለት ሲኦል በሞት የተለየንን ሰው የምንቀብርበትን አንድን የተወሰነ መቃብር ወይም የአንድን ሰው የመቃብር ቦታ ያመለክታል ማለት ነው? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ አንድን የተወሰነ የመቃብር ቦታ በሚጠቅስበት ጊዜ የሚጠቀምባቸው የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ሺኦል እና ሔዲስ ሳይሆኑ ሌሎች ቃላት ናቸው። (ዘፍጥረት 23:7-9፤ ማቴዎስ 28:1) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ መቃብርን ወይም ብዙ ሰዎች አንድ ላይ የሚቀበሩበትን መቃብር ለማመልከት “ሲኦል” የሚለውን ቃል አይጠቀምም።—ዘፍጥረት 49:30, 31

ታዲያ “ሲኦል” የሚያመለክተው ምን ዓይነት ቦታን ነው? የአምላክ ቃል እንደሚጠቁመው “ሲኦል” ብዙ ሰዎች አንድ ላይ ከሚቀበሩበት ትልቅ መቃብር የበለጠን ነገር የሚያመለክት ቃል ነው። ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ 5:14 “ሲኦል ሆዷን አሰፋች፣ አፏንም ያለ ልክ ከፈተች” በማለት ይናገራል። ምንም እንኳ ሲኦል በምሳሌያዊ ሁኔታ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ሙታን የዋጠ ቢሆንም ምንጊዜም የሚጠግብ አይመስልም። (ምሳሌ 30:15, 16) የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሙታን ብቻ መያዝ ከሚችለው ከየትኛውም የመቃብር ሥፍራ በተለየ ሁኔታ ‘ሲኦል አይጠግብም።’ (ምሳሌ 27:20) ሲኦል መቼም ቢሆን አይሞላም ማለት ነው። ምንም ገደብ የለውም። በመሆኑም ሲኦል ቃል በቃል በአንድ የተወሰነ ሥፍራ የሚገኝ ቦታን የሚያመለክት ቃል ሳይሆን ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ሲሞቱ ወደዚህ ምሳሌያዊ ቦታ እንደገቡ ይቆጠራል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚሰጠው ትምህርት ‘የሲኦልን’ ትርጉም ይበልጥ እንድናስተውል ይረዳናል። የአምላክ ቃል ሲኦልን ትንሣኤ ካለው ሞት  ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። * (ኢዮብ 14:13 የ1954 ትርጉም፤ የሐዋርያት ሥራ 2:31፤ ራእይ 20:13) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቃል ይሖዋን ሲያገለግሉ የኖሩ ብቻ ሳይሆኑ ይሖዋን ሳያገለግሉ ሕይወታቸው ያለፈ በርካታ ሰዎችም ሲኦል ውስጥ እንዳሉ ይገልጽልናል። (ዘፍጥረት 37:35፤ መዝሙር 55:15) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ” ይናገራል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

^ አን.4 በአንጻሩ ትንሣኤ የማያገኙ ሙታን ሲኦል ውስጥ ሳይሆን “ገሃነም” ውስጥ እንዳሉ ተደርጎ ተገልጿል። (ማቴዎስ 5:30፤ 10:28፤ 23:33) ልክ እንደ ሲኦል ሁሉ ገሃነምም ቃል በቃል አንድን የተወሰነ ሥፍራ የሚያመለክት ቃል አይደለም።