መዝሙር 119:1-176

  • ውድ ለሆነው የአምላክ ቃል አድናቆት ማሳየት

    • “ወጣቶች በንጽሕና መመላለስ የሚችሉት እንዴት ነው?” (9)

    • “ማሳሰቢያዎችህን እወዳቸዋለሁ” (24)

    • “ቃልህ ተስፋዬ ነው” (74, 81, 114)

    • “ሕግህን ምንኛ ወደድኩ!” (97)

    • “ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥልቅ ማስተዋል አለኝ” (99)

    • ‘ቃልህ ለእግሬ መብራት ነው’ (105)

    • “የቃልህ ፍሬ ነገር እውነት ነው” (160)

    • የአምላክን ሕግ የሚወዱ ሰላም አላቸው (165)

א [አሌፍ] 119  በመንገዳቸው ነቀፋ የሌለባቸው፣*በይሖዋ ሕግ የሚመላለሱ ሰዎች ደስተኞች ናቸው።+   ማሳሰቢያዎቹን የሚጠብቁ፣+እሱን በሙሉ ልባቸው የሚፈልጉ ደስተኞች ናቸው።+   ክፉ ነገር አያደርጉም፤በመንገዶቹ ይሄዳሉ።+   አንተ መመሪያዎችህንበጥብቅ እንድንከተል አዘኸናል።+   ሥርዓትህን እጠብቅ ዘንድምነው በአቋሜ በጸናሁ!*+   ይህ ቢሆንልኝ፣ትእዛዛትህን ሁሉ በትኩረት ስመለከት አላፍርም።+   የጽድቅ ፍርዶችህን በተማርኩ ጊዜበቀና ልብ አወድስሃለሁ።   ሥርዓትህን አከብራለሁ። አቤቱ እርግፍ አድርገህ አትተወኝ። ב [ቤት]   ወጣቶች በንጽሕና መመላለስ የሚችሉት እንዴት ነው? በቃልህ መሠረት ራሳቸውን በመጠበቅ ነው።+ 10  በሙሉ ልቤ አንተን እሻለሁ። ከትእዛዛትህ እንድርቅ አትፍቀድ።+ 11  በአንተ ላይ ኃጢአት እንዳልሠራ፣+አንተ የተናገርከውን በልቤ ውስጥ እንደ ውድ ሀብት እሸሽጋለሁ።+ 12  ይሖዋ ሆይ፣ ውዳሴ ይድረስህ፤ሥርዓትህን አስተምረኝ። 13  የተናገርካቸውን ፍርዶች ሁሉበከንፈሮቼ አስታውቃለሁ። 14  ውድ ከሆኑ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ይበልጥ፣+በማሳሰቢያዎችህ ሐሴት አደርጋለሁ።+ 15  በመመሪያዎችህ ላይ አሰላስላለሁ፤*+ዓይኖቼንም በመንገዶችህ ላይ እተክላለሁ።+ 16  ያወጣሃቸውን ደንቦች እወዳቸዋለሁ። ቃልህን አልረሳም።+ ג [ጊሜል] 17  በሕይወት መኖርና ቃልህን መጠበቅ እችል ዘንድ፣ለአገልጋይህ ደግነት አሳይ።+ 18  በሕግህ ውስጥ ያሉትን አስደናቂ ነገሮችአጥርቼ እንዳይ ዓይኖቼን ክፈት። 19  በምድሪቱ ላይ የባዕድ አገር ሰው ነኝ።+ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር። 20  እኔ* ፍርዶችህንዘወትር ከመናፈቄ የተነሳ ዛልኩ። 21  እብሪተኛ የሆኑትን፣ከትእዛዛትህ የራቁትን የተረገሙ ሰዎች ትገሥጻለህ።+ 22  ማሳሰቢያዎችህን ጠብቄአለሁና፣ዘለፋንና ንቀትን ከእኔ አስወግድ።* 23  መኳንንትም እንኳ አንድ ላይ ተቀምጠው ስለ እኔ መጥፎ ነገር ሲያወሩ፣አገልጋይህ በሥርዓትህ ላይ ያሰላስላል።* 24  ማሳሰቢያዎችህን እወዳቸዋለሁ፤+መካሪዎቼ ናቸው።+ ד [ዳሌት] 25  አፈር ላይ ተደፍቻለሁ።*+ በቃልህ መሠረት በሕይወት አቆየኝ።+ 26  መንገዶቼን ለአንተ ተናገርኩ፤ አንተም መለስክልኝ፤ሥርዓትህን አስተምረኝ።+ 27  አስደናቂ በሆኑት ሥራዎችህ ላይ አሰላስል ዘንድ፣*+የመመሪያዎችህን ትርጉም እንዳስተውል አድርገኝ። 28  ከሐዘን የተነሳ እንቅልፍ አጣሁ።* በቃልህ መሠረት አበርታኝ። 29  የአታላይነትን መንገድ ከእኔ አርቅ፤+ሕግህንም በማሳወቅ ሞገስ አሳየኝ። 30  የታማኝነትን ጎዳና መርጫለሁ።+ ፍርዶችህ ትክክል እንደሆኑ እገነዘባለሁ። 31  ማሳሰቢያዎችህን የሙጥኝ እላለሁ።+ ይሖዋ ሆይ፣ ለሐዘን* እንድዳረግ አትፍቀድ።+ 32  በልቤ ውስጥ ቦታ ስለሰጠኸው፣*የትእዛዛትህን መንገድ በጉጉት እከተላለሁ።* ה [] 33  ይሖዋ ሆይ፣ የሥርዓትህን መንገድ አስተምረኝ፤+እኔም እስከ መጨረሻው እከተለዋለሁ።+ 34  ሕግህን እንዳከብርናበሙሉ ልቤ እንድጠብቅማስተዋል ስጠኝ። 35  በትእዛዛትህ መንገድ ምራኝ፤*+በእሱ ደስ እሰኛለሁና። 36  ልቤ የግል ጥቅም* ከማሳደድ+ ይልቅወደ ማሳሰቢያዎችህ እንዲያዘነብል አድርግ። 37  ከንቱ ነገር እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ፤+በመንገድህ ላይ በሕይወት እንድቀጥል አድርገኝ። 38  አንተ በሌሎች ትፈራ ዘንድ፣ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል* ፈጽም።* 39  በጣም የምፈራውን ውርደት ከእኔ አርቅ፤ፍርዶችህ ጥሩ ናቸውና።+ 40  መመሪያዎችህን ምን ያህል እንደናፈቅኩ ተመልከት። በጽድቅህ ሕያው ሆኜ እንድኖር አድርገኝ። ו [ዋው] 41  ይሖዋ ሆይ፣ ቃል በገባኸው* መሠረትታማኝ ፍቅርህንና ማዳንህን ልቅመስ፤+ 42  በዚህ ጊዜ ለሚሳለቅብኝ መልስ መስጠት እችላለሁ፤በቃልህ እታመናለሁና። 43  የእውነትን ቃል ከአፌ አታርቅ፤በፍርድህ ተስፋ አድርጌአለሁና።* 44  እኔ ሕግህን ዘወትር፣አዎ፣ ለዘላለም እጠብቃለሁ።+ 45  ደህንነት በማገኝበት ስፍራ* እንደ ልቤ እመላለሳለሁ፤+መመሪያዎችህን ከልቤ እፈልጋለሁና። 46  ስለ ማሳሰቢያዎችህ በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ደግሞም አላፍርም።+ 47  ትእዛዛትህ ደስ ያሰኙኛል፤አዎ፣ እወዳቸዋለሁ።+ 48  ትእዛዛትህን ስለምወዳቸው+ እጆቼን ከፍ አድርጌ ወደ አንተ እጸልያለሁ፤በሥርዓትህም ላይ አሰላስላለሁ።*+ ז [ዛየን] 49  ለአገልጋይህ የተናገርከውን ቃል* አስታውስ፤በዚህ ቃል ተስፋ ሰጥተኸኛል።* 50  በመከራዬ ወቅት መጽናኛ የማገኘው በዚህ ነው፤+የተናገርከው ቃል በሕይወት አቆይቶኛልና። 51  እብሪተኞች እጅግ ይሳለቁብኛል፤እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም።+ 52  ይሖዋ ሆይ፣ ከጥንት ጀምሮ የነበሩትን ፍርዶችህን አስታውሳለሁ፤+በእነዚህም መጽናኛ አገኛለሁ።+ 53  ሕግህን ከተዉ ክፉ ሰዎች የተነሳበቁጣ በገንኩ።+ 54  በምኖርበት ቦታ* ሁሉሥርዓትህ መዝሙር ሆነልኝ። 55  ይሖዋ ሆይ፣ ሕግህን እጠብቅ ዘንድበሌሊት ስምህን አስታውሳለሁ።+ 56  ይህን ልማድ አድርጌዋለሁ፤ምክንያቱም መመሪያዎችህን ጠብቄአለሁ። ח [ኼት] 57  ይሖዋ ድርሻዬ ነው፤+ሕግህን ለመጠበቅ ቃል ገብቻለሁ።+ 58  በሙሉ ልቤ አንተን እማጸናለሁ፤+በገባኸው ቃል* መሠረት ሞገስ አሳየኝ።+ 59  እግሮቼን ወደ ማሳሰቢያዎችህ እመልስ ዘንድመንገዴን መረመርኩ።+ 60  ትእዛዛትህን ለመጠበቅ ፈጠንኩ፤ፈጽሞ አልዘገየሁም።+ 61  የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ሆኖም ሕግህን አልረሳሁም።+ 62  ስለ ጽድቅ ፍርዶችህ አንተን ለማመስገንእኩለ ሌሊት ላይ እነሳለሁ።+ 63  አንተን ለሚፈሩ ሁሉ፣መመሪያዎችህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ።+ 64  ይሖዋ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርህ ምድርን ይሞላል፤+ሥርዓትህን አስተምረኝ። ט [ቴት] 65  ይሖዋ ሆይ፣ በቃልህ መሠረትለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርገህለታል። 66  ማስተዋልንና እውቀትን አስተምረኝ፤+በትእዛዛትህ ታምኛለሁና። 67  መከራ ላይ ከመውደቄ በፊት፣ መንገድ ስቼ እሄድ ነበር፤*አሁን ግን የተናገርከውን እጠብቃለሁ።+ 68  አንተ ጥሩ ነህ፤+ ሥራህም ጥሩ ነው። ሥርዓትህን አስተምረኝ።+ 69  እብሪተኞች በውሸት ስሜን ያጎድፋሉ፤እኔ ግን በሙሉ ልቤ መመሪያዎችህን እጠብቃለሁ። 70  ልባቸው ደንዝዟል፤*+እኔ ግን ሕግህን እወዳለሁ።+ 71  ሥርዓትህን እማር ዘንድበመከራ ውስጥ ማለፌ ጥሩ ሆነልኝ።+ 72  አንተ ያወጅከው ሕግ ጠቅሞኛል፤+ለእኔ ከብዙ ወርቅና ብር እጅግ የተሻለ ነው።+ י [ዮድ] 73  እጆችህ ሠሩኝ፤ ደግሞም አበጁኝ። ትእዛዛትህን እማር ዘንድማስተዋል ስጠኝ።+ 74  አንተን የሚፈሩ ሰዎች እኔን አይተው ሐሴት ያደርጋሉ፤ቃልህ ተስፋዬ ነውና።*+ 75  ይሖዋ ሆይ፣ ፍርዶችህ በጽድቅ ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑና+ከታማኝነትህ የተነሳ እንደቀጣኸኝ አውቃለሁ።+ 76  ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል* መሠረት፣እባክህ፣ ታማኝ ፍቅርህ+ ያጽናናኝ። 77  በሕይወት መኖሬን እንድቀጥል ምሕረት አሳየኝ፤+ሕግህን እወዳለሁና።+ 78  እብሪተኞች ኀፍረት ይከናነቡ፤ያላንዳች ምክንያት* በድለውኛልና። እኔ ግን በመመሪያዎችህ ላይ አሰላስላለሁ።*+ 79  አንተን የሚፈሩ፣ ማሳሰቢያዎችህንም የሚያውቁ፣ወደ እኔ ይመለሱ። 80  ለኀፍረት እንዳልዳረግ፣ልቤ ነቀፋ በሌለበት መንገድ ሥርዓትህን ይከተል።+ כ [ካፍ] 81  ማዳንህን እናፍቃለሁ፤*+ቃልህ ተስፋዬ ነውና።* 82  አንተ የተናገርከው ቃል ሲፈጸም ለማየት ዓይኖቼ ይጓጓሉ፤+“የምታጽናናኝ መቼ ነው?”+ እያልኩ እጠይቃለሁ። 83  ጭስ እንዳደረቀው አቁማዳ ሆኛለሁና፤ሆኖም ሥርዓትህን አልረሳም።+ 84  ባሪያህ በሕይወት የሚቆየው እስከ መቼ ነው? ስደት በሚያደርሱብኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ነው?+ 85  ሕግህን የሚጥሱእብሪተኛ ሰዎች እኔን ለማጥመድ ጉድጓድ ይቆፍራሉ። 86  ትእዛዛትህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው። ሰዎች ያለምክንያት ያሳድዱኛል፤ አቤቱ እርዳኝ!+ 87  ከምድር ገጽ ሊያጠፉኝ ምንም ያህል አልቀራቸውም ነበር፤እኔ ግን መመሪያዎችህን አልተውኩም። 88  የተናገርካቸውን ማሳሰቢያዎች እጠብቅ ዘንድ፣ከታማኝ ፍቅርህ የተነሳ በሕይወት አቆየኝ። ל [ላሜድ] 89  ይሖዋ ሆይ፣ ቃልህ በሰማያት፣ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።+ 90  ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው።+ ምድር ለዘለቄታው እንድትኖር በጽኑ መሠረትካት።+ 91  በፍርዶችህ መሠረት እስከ ዛሬ ጸንተው ኖረዋል፤*ሁሉም አገልጋዮችህ ናቸውና። 92  ሕግህን ባልወድ ኖሮ፣በደረሰብኝ ጉስቁልና በጠፋሁ ነበር።+ 93  መመሪያዎችህን ፈጽሞ አልረሳም፤ምክንያቱም በእነሱ አማካኝነት በሕይወት አቆይተኸኛል።+ 94  እኔ የአንተ ነኝ፤መመሪያዎችህን ፈልጌአለሁና+ አድነኝ።+ 95  ክፉዎች እኔን ለማጥፋት ያደባሉ፤እኔ ግን ለማሳሰቢያዎችህ ትኩረት እሰጣለሁ። 96  ፍጽምና ሁሉ ገደብ እንዳለው አይቻለሁ።ትእዛዝህ ግን ገደብ የለውም።* מ [ሜም] 97  ሕግህን ምንኛ ወደድኩ!+ ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።*+ 98  ትእዛዝህ ለዘላለም ስለማይለየኝ፣ከጠላቶቼ ይበልጥ ጥበበኛ ያደርገኛል።+ 99  በማሳሰቢያዎችህ ላይ ስለማሰላስል፣*ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥልቅ ማስተዋል አለኝ።+ 100  መመሪያዎችህን ስለማከብር፣ከሽማግሌዎች ይበልጥ በማስተዋል እመላለሳለሁ። 101  ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣በየትኛውም ክፉ መንገድ ከመሄድ እቆጠባለሁ።+ 102  አንተ አስተምረኸኛልና፣ከፍርዶችህ ፈቀቅ አልልም። 103  የተናገርከው ነገር ለምላሴ እጅግ ጣፋጭ ነው፤ለአፌም ከማር የበለጠ ይጥማል!+ 104  ከመመሪያዎችህ የተነሳ በማስተዋል እመላለሳለሁ።+ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ እጠላለሁ።+ נ [ኑን] 105  ቃልህ ለእግሬ መብራት፣ለመንገዴም ብርሃን ነው።+ 106  የጽድቅ ፍርዶችህን ለመጠበቅ ምያለሁ፤ደግሞም እፈጽመዋለሁ። 107  ከፍተኛ ጉስቁልና ደርሶብኛል።+ ይሖዋ ሆይ፣ በቃልህ መሠረት በሕይወት አቆየኝ።+ 108  ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ በፈቃደኝነት የማቀርበውን የውዳሴ መባ* በደስታ ተቀበል፤+ፍርዶችህንም አስተምረኝ።+ 109  ሕይወቴ ሁልጊዜ አደጋ ላይ ናት፤*እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም።+ 110  ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤እኔ ግን ከመመሪያዎችህ ዝንፍ አላልኩም።+ 111  ማሳሰቢያዎችህ ልቤን ደስ ስለሚያሰኙ፣+ቋሚ ንብረቴ* አደርጋቸዋለሁ። 112  ሥርዓትህን በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣እስከ መጨረሻው ለመጠበቅ ቆርጫለሁ።* ס [ሳሜኽ] 113  በግማሽ ልብ የሚመላለሱትን* እጠላለሁ፤+ሕግህን ግን እወዳለሁ።+ 114  አንተ መጠለያዬና ጋሻዬ ነህ፤+ቃልህ ተስፋዬ ነውና።*+ 115  እናንተ ክፉዎች፣የአምላኬን ትእዛዛት መጠበቅ እንድችል ከእኔ ራቁ።+ 116  በሕይወት እንድቀጥልቃል በገባኸው* መሠረት ደግፈኝ፤+ተስፋዬ ሳይፈጸም ቀርቶ እንዳዝን አትፍቀድ።*+ 117  እድን ዘንድ ደግፈኝ፤+ያን ጊዜ ለሥርዓትህ ዘወትር ትኩረት እሰጣለሁ።+ 118  ከሥርዓትህ የሚርቁትን ሁሉ ገሸሽ ታደርጋቸዋለህ፤+ውሸታሞችና አታላዮች ናቸውና። 119  በምድር ላይ ያሉ ክፉዎችን ሁሉ ከላይ እንደሚሰፍ የማይረባ ቆሻሻ ታስወግዳቸዋለህ።+ ስለዚህ ማሳሰቢያዎችህን እወዳለሁ። 120  አንተን እጅግ ከመፍራቴ የተነሳ ሰውነቴ* ይንቀጠቀጣል፤ፍርዶችህን እፈራለሁ። ע [አይን] 121  ትክክልና ጽድቅ የሆነውን አድርጌአለሁ። ለሚጨቁኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ! 122  ለአገልጋይህ ደህንነት ዋስትና ስጥ፤እብሪተኞች እንዲጨቁኑኝ አትፍቀድ። 123  ዓይኖቼ ማዳንህንናየገባኸውን* የጽድቅ ቃል በመጠባበቅ ደከሙ።+ 124  ለአገልጋይህ ታማኝ ፍቅርህን አሳየው፤+ሥርዓትህንም አስተምረኝ።+ 125  እኔ አገልጋይህ ነኝ፤ማሳሰቢያዎችህን እንዳውቅ ማስተዋል ስጠኝ።+ 126  ይሖዋ ሆይ፣ እርምጃ የምትወስድበት ጊዜ ደርሷል፤+ሰዎች ሕግህን ጥሰዋልና። 127  ስለዚህ እኔ ትእዛዛትህን ከወርቅ፣ምርጥ ከሆነ* ወርቅ ይበልጥ እወዳለሁ።+ 128  በመሆኑም የምታስተምረው ትምህርት* በሙሉ ትክክል እንደሆነ አምናለሁ፤+የሐሰትን መንገድ ሁሉ እጠላለሁ።+ פ [] 129  ማሳሰቢያዎችህ ድንቅ ናቸው። ስለዚህ እጠብቃቸዋለሁ።* 130  አንተ የምትገልጣቸው ቃላት ብርሃን ይፈነጥቃሉ፤+ተሞክሮ የሌላቸውን አስተዋዮች ያደርጋሉ።+ 131  ትእዛዛትህን ለመስማት ከመጓጓቴ የተነሳ+አፌን ከፍቼ በረጅሙ እተነፍሳለሁ።* 132  ስምህን ለሚወዱ ሰዎች+ ከምትሰጠው ፍርድ ጋር በሚስማማ መንገድ፣ወደ እኔ ተመለስ፤ ሞገስም አሳየኝ።+ 133  በቃልህ መሠረት አካሄዴን በሰላም ምራ፤*ማንኛውም ክፉ ነገር በእኔ ላይ አይሠልጥን።+ 134  ጨቋኝ ከሆኑ ሰዎች ታደገኝ፤*እኔም መመሪያዎችህን እጠብቃለሁ። 135  በአገልጋይህ ላይ ፊትህን አብራ፤*+ሥርዓትህንም አስተምረኝ። 136  ሰዎች ሕግህን ስለማያከብሩእንባ ከዓይኖቼ እንደ ውኃ ፈሰሰ።+ צ [ጻዴ] 137  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጻድቅ ነህ፤+ፍርዶችህም ትክክል ናቸው።+ 138  የምትሰጣቸው ማሳሰቢያዎች በጽድቅ ላይ የተመሠረቱናሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ናቸው። 139  ጠላቶቼ ቃልህን ስለረሱቅንዓቴ ይበላኛል።+ 140  ቃልህ እጅግ የጠራ ነው፤+አገልጋይህም ይወደዋል።+ 141  እኔ በሌሎች ዘንድ የተናቅኩና የማልረባ ነኝ፤+ሆኖም መመሪያዎችህን አልረሳሁም። 142  ጽድቅህ የዘላለም ጽድቅ ነው፤+ሕግህም እውነት ነው።+ 143  ጭንቀትና ችግር ቢደርስብኝምትእዛዛትህን ምንጊዜም እወዳለሁ። 144  ማሳሰቢያህ ለዘላለም ጽድቅ ነው። በሕይወት መኖሬን እንድቀጥል ማስተዋል ስጠኝ።+ ק [ኮፍ] 145  በሙሉ ልቤ እጣራለሁ። ይሖዋ ሆይ፣ መልስልኝ። ሥርዓትህን እጠብቃለሁ። 146  አንተን እጣራለሁ፤ አቤቱ አድነኝ! ማሳሰቢያዎችህን እጠብቃለሁ። 147  ጎህ ሳይቀድ* ተነስቼ እርዳታ ለማግኘት እጮኻለሁ፤+ቃልህ ተስፋዬ ነውና።* 148  በተናገርከው ቃል ላይ ማሰላሰል* እንድችል፣ክፍለ ሌሊቶቹ ከማብቃታቸው በፊት እነቃለሁ።+ 149  ከታማኝ ፍቅርህ የተነሳ ድምፄን ስማ።+ ይሖዋ ሆይ፣ ከአንተ ፍትሕ ጋር በሚስማማ መንገድ በሕይወት አቆየኝ። 150  አሳፋሪ በሆነ ድርጊት* የተጠመዱ ሰዎች ወደ እኔ ቀርበዋል፤ከሕግህም ርቀዋል። 151  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ቅርብ ነህ፤+ትእዛዛትህም ሁሉ እውነት ናቸው።+ 152  በቀድሞው ዘመን ስለ ማሳሰቢያዎችህ ተምሬአለሁ፤ለዘላለም ይጸኑ ዘንድ እንደመሠረትካቸው ተረድቻለሁ።+ ר [ረሽ] 153  የደረሰብኝን ጉስቁልና ተመልከት፤ ደግሞም ታደገኝ፤+ሕግህን አልረሳሁምና። 154  ተሟገትልኝ፤* ደግሞም ታደገኝ፤+በገባኸው * ቃል መሠረት በሕይወት አቆየኝ። 155  ክፉዎች ሥርዓትህን ስላልፈለጉመዳን ከእነሱ ርቋል።+ 156  ይሖዋ ሆይ፣ ምሕረትህ ታላቅ ነው።+ ከአንተ ፍትሕ ጋር በሚስማማ መንገድ በሕይወት አቆየኝ። 157  አሳዳጆቼና ጠላቶቼ ብዙ ናቸው፤+እኔ ግን ከማሳሰቢያዎችህ ፈቀቅ አላልኩም። 158  ከዳተኛ የሆኑ ሰዎችን ተጸየፍኩ፤ምክንያቱም አንተ የተናገርከውን አይጠብቁም።+ 159  መመሪያዎችህን ምን ያህል እንደምወድ ተመልከት! ይሖዋ ሆይ፣ ከታማኝ ፍቅርህ የተነሳ በሕይወት አቆየኝ።+ 160  የቃልህ ፍሬ ነገር እውነት ነው፤+በጽድቅ ላይ የተመሠረተው ፍርድህ ሁሉ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ש [ሲን] ወይም [ሺን] 161  መኳንንት ያለምክንያት ያሳድዱኛል፤+ልቤ ግን ለቃልህ ጥልቅ አክብሮት አለው።+ 162  ብዙ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፣እኔም አንተ በተናገርከው ነገር ሐሴት አደርጋለሁ።+ 163  ውሸትን እጠላለሁ፤ ደግሞም እጸየፈዋለሁ፤+ሕግህን ግን እወዳለሁ።+ 164  በጽድቅ ላይ ከተመሠረቱት ፍርዶችህ የተነሳበቀን ሰባት ጊዜ አወድስሃለሁ። 165  ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤+ሊያደናቅፋቸው የሚችል ምንም ነገር የለም።* 166  ይሖዋ ሆይ፣ የማዳን ሥራህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ትእዛዛትህንም እፈጽማለሁ። 167  ማሳሰቢያዎችህን እጠብቃለሁ፤*ደግሞም እጅግ እወዳቸዋለሁ።+ 168  መመሪያዎችህንና ማሳሰቢያዎችህን እጠብቃለሁ፤የማደርገውን ነገር ሁሉ ታውቃለህና።+ ת [ታው] 169  ይሖዋ ሆይ፣ እርዳታ ለማግኘት የማሰማው ጩኸት ወደ አንተ ይድረስ።+ እንደ ቃልህ ማስተዋል ስጠኝ።+ 170  ሞገስ ለማግኘት የማቀርበው ልመና ወደ አንተ ይድረስ። ቃል በገባኸው* መሠረት አድነኝ። 171  ሥርዓትህን ስለምታስተምረኝከንፈሮቼ ውዳሴን ያፍልቁ።+ 172  አንደበቴ ስለተናገርከው ቃል ይዘምር፤+ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና። 173  መመሪያዎችህን ለመታዘዝ ስለምመርጥ፣+እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን።+ 174  ይሖዋ ሆይ፣ ማዳንህን እናፍቃለሁ፤ሕግህንም እወዳለሁ።+ 175  አወድስህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤*+አንተ ያወጣሃቸው ፍርዶች ይርዱኝ። 176  እንደጠፋ በግ ተቅበዘበዝኩ።+ አገልጋይህን ፈልገው፤ትእዛዛትህን አልረሳሁምና።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ።”
ቃል በቃል “ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ!”
ወይም “መመሪያዎችህን አጠናለሁ።”
ወይም “ነፍሴ . . . ከመናፈቋ የተነሳ ዛለች።”
ቃል በቃል “ከላዬ ላይ አርቅ።”
ወይም “ሥርዓትህን ያጠናል።”
ወይም “ነፍሴ አፈር ላይ ተደፍታለች።”
ወይም “አስደናቂ የሆኑትን ሥራዎችህን አጠና ዘንድ።”
ወይም “ነፍሴ እንቅልፍ አጣች።”
ወይም “ለኀፍረት።”
“ልቤ የመተማመን ስሜት እንዲያድርበት ስላደረግክ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እሮጣለሁ።”
ወይም “እንድሄድ አድርገኝ።”
ወይም “ትርፍ።”
ወይም “የተናገርከውን ነገር።”
“ለሚፈሩህ የገባኸውን ቃል፣ ለአገልጋይህ ፈጽም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በተናገርከው።”
ወይም “ፍርድህን እጠባበቃለሁና።”
ወይም “ሰፊ በሆነ ስፍራ።”
ወይም “ሥርዓትህንም አጠናለሁ።”
ወይም “የሰጠኸውን ተስፋ።”
ወይም “ይህን ቃል እንድጠባበቅ አድርገኸኛል።”
ወይም “የባዕድ አገር ሰው ሆኜ በምኖርበት ቤት።”
ወይም “በተናገርከው።”
ወይም “በስህተት ኃጢአት እሠራ ነበር።”
ቃል በቃል “ልባቸው እንደ ስብ ደንድኗል።”
ወይም “ቃልህን እጠባበቃለሁና።”
ወይም “በተናገርከው።”
“በውሸት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “መመሪያዎችህን አጠናለሁ።”
ወይም “ነፍሴ ማዳንህን ከመናፈቋ የተነሳ ዛለች።”
ወይም “ቃልህን እጠባበቃለሁና።”
የፍጥረት ሥራዎቹን በሙሉ ያመለክታል።
ቃል በቃል “በጣም ሰፊ ነው።”
ወይም “ቀኑን ሙሉ አጠናዋለሁ።”
ወይም “ማሳሰቢያዎችህን ስለማጠና።”
ቃል በቃል “በአፌ በፈቃደኝነት የማቀርበውን መባ።”
ወይም “ነፍሴ ሁልጊዜ እጄ ውስጥ ናት።”
ወይም “ዘላለማዊ ውርሻዬ።”
ቃል በቃል “ልቤን አዘንብያለሁ።”
ወይም “የተከፈለ ልብ ያላቸውን ሰዎች።”
ወይም “ቃልህን እጠባበቃለሁና።”
ወይም “በተናገርከው።”
ወይም “እንዳፍር አታድርግ።”
ቃል በቃል “ሥጋዬ።”
ወይም “የተናገርከውን።”
ወይም “ከጠራ።”
ወይም “መመሪያህ።”
ወይም “ነፍሴ ትጠብቃቸዋለች።”
ቃል በቃል “አፌን ከፍቼ አለከልካለሁ።”
ወይም “አካሄዴን አጽና።”
ቃል በቃል “ዋጀኝ።”
ወይም “ለአገልጋይህ ፈገግታ አሳይ።”
ወይም “በማለዳ ወጋገን።”
ወይም “ቃልህን እጠባበቃለሁና።”
ወይም “ቃልህን ማጥናት።”
ወይም “ጸያፍ በሆነ ምግባር።”
ወይም “ጥብቅና ቁምልኝ።”
ወይም “በተናገርከው።”
ወይም “እንቅፋትም የለባቸውም።”
ወይም “ነፍሴ ማሳሰቢያዎችህን ትጠብቃለች።”
ወይም “በተናገርከው።”
ወይም “ነፍሴ በሕይወት ትኑር።”