በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የአዞ መንጋጋ

የአዞ መንጋጋ

የአዞ መንጋጋ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ከሚኖሩ አራዊት ሁሉ ይበልጥ ከፍተኛ የመቀርጠፍ ኃይል አለው። ለምሳሌ ያህል፣ አውስትራሊያ አቅራቢያ በጨዋማ ውኃ ውስጥ የሚኖረው አዞ የመንከስ ኃይሉ ከአንበሳ ወይም ከነብር ጋር ሲወዳደር ሦስት እጥፍ ያህል ከፍ ያለ ነው። በጣም የሚያስገርመው ግን የአዞ መንጋጋ ትንሽ ነገር እንኳ ሲነካው የሚሰማው ወዲያውኑ ነው፤ ሌላው ቀርቶ ከጣታችን ጫፍ ይበልጥ ቶሎ ይሰማዋል። አዞ እንደ ቅርፊት ያለ እጅግ ጠንካራ ቆዳ ያለው ከመሆኑ አንፃር ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

የአዞ መንጋጋ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የስሜት ሕዋሳት አሉት። ዳንከን ሊች የተባሉ ተመራማሪ በዚህ ላይ ጥናት ካደረጉ በኋላ “እያንዳንዱ የነርቭ ጫፍ የሚወጣው በጭንቅላቱ ውስጥ ከሚገኝ ቀዳዳ” እንደሆነ አስተውለዋል። በመንጋጋው ውስጥ ያሉት ነርቮች በዚህ መንገድ መቀመጣቸው ምንም ነገር እንዳይጎዳቸው የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ የነርቭ ሴሎቹ አንድ ነገር ሲነካቸው ቶሎ እንዲሰማቸው ያስችላል፤ እንዲያውም በመንጋጋው ላይ ያሉ አንዳንድ ነርቮች አንድ ነገር ሲነካቸው የሚሰጡት ምላሽ በጣም ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ በመሣሪያ እንኳ መለካት አይቻልም። በዚህም የተነሳ አዞ አፉ ውስጥ ያለ አንድ ነገር ምግብ ይሁን አይሁን በቀላሉ መለየት ይችላል። ይህም አንዲት አዞ ጫጩቶቿን በአፏ ይዛ ስትሄድ ተሳስታ እንኳ እንዳትጨፈልቃቸው ይረዳታል። የሚያስገርመው፣ የአዞ መንጋጋ እጅግ ኃይለኛ የመቀርጠፍ ብቃትና ትንሽ ነገር ሲነካው ቶሎ የመለየት ችሎታን አጣምሮ የያዘ ነው።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? በአዞ መንጋጋ ላይ የሚታየው ንድፍ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?