በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ንድፍ አውጪ አለው?

የቢራቢሮ ክንፍ

የቢራቢሮ ክንፍ

የቢራቢሮ ክንፍ በቀላሉ ሊጎዳ የሚችል ከመሆኑ የተነሳ የአቧራ ብናኝ ቢያርፍበት ወይም ትንሽ እርጥበት ቢነካው እንኳ ቢራቢሮው መብረር አስቸጋሪ ይሆንበታል። የሚገርመው ግን ክንፎቹ ሁልጊዜ ንጹሕና ከእርጥበት የጸዱ ናቸው። የዚህ ሚስጥሩ ምንድን ነው?

የቢራቢሮ ክንፍ የተነባበሩ ጥቃቅን ቅርፊቶች አሉት

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ጃይንት ብሉ ሞርፎ በተባለው ቢራቢሮ (ሞርፎ ዲድየስ) ላይ ጥናት የሚያካሂዱ የኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንደገለጹት የዚህ ቢራቢሮ ክንፎች እንዲሁ ሲታዩ ልሙጥ ይምሰሉ እንጂ በጣም ጥቃቅን በሆኑ ልክ እንደ ጣሪያ ሸክላ በተነባበሩ ቅርፊቶች የተሸፈኑ ናቸው። በእነዚህ ቅርፊቶች ላይ ያሉ በጣም ጥቃቅን የሆኑ ሸንተረሮች የውኃ ጠብታዎችና የአቧራ ቅንጣቶች ተንሸራትተው እንዲወርዱ ያደርጋሉ። መሐንዲሶች ውኃና አቧራ የሚከላከሉ የተራቀቁ የኢንዱስትሪና የሕክምና መሣሪያዎችን ለመሥራት የዚህን ቢራቢሮ ክንፎች ለመኮረጅ ጥረት እያደረጉ ነው።

ተመራማሪዎች የቢራቢሮን ክንፍ አስመስለው ለመሥራት መሞከራቸው ሳይንስ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚታየውን ንድፍ ለመኮረጅ ጥረት እያደረገ እንዳለ የሚያሳይ አንድ ተጨማሪ ምሳሌ ነው። ብሃራት ቡሻን የተባለ አንድ ተመራማሪ “በተፈጥሮ ውስጥ ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ ለቁጥር የሚያታክቱ አስደናቂ የምሕንድስና ውጤቶችን ማግኘት ይቻላል” ብሏል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የቢራቢሮ ክንፍ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?