በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ምንዝር

ምንዝር

ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሥነ ምግባር ቢሆንም ምንዝር ብዙ ቤተሰቦችን ማፍረሱ አልቀረም።

ምንዝር ምንድን ነው?

ሰዎች ምን ይላሉ?

በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ባለትዳሮች በተለይም ባሎች ከትዳር ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው እንደ መጥፎ ድርጊት አይታይም። አንዳንዶች ደግሞ ጋብቻን ዘላቂ እንደሆነ ጥምረት አድርገው አይመለከቱትም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንዝር የሚለው ቃል አንድ ያገባ ሰው፣ ወንድም ይሁን ሴት፣ የትዳር ጓደኛው ካልሆነ ሰው ጋር ወዶና ፈቅዶ የፆታ ግንኙነት መፈጸሙን ያመለክታል። (ኢዮብ 24:15፤ ምሳሌ 30:20) ምንዝር በአምላክ ዓይን አስጸያፊ የሆነ ድርጊት ነው። በጥንቷ እስራኤል አንድ ሰው ምንዝር ከፈጸመ በሞት ይቀጣ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:20, 22, 29) ኢየሱስ ተከታዮቹ ከምንዝር መራቅ እንዳለባቸው አስተምሯል።—ማቴዎስ 5:27, 28፤ ሉቃስ 18:18-20

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

አንድ ሰው ምንዝር በሚፈጽምበት ጊዜ በሠርጉ ዕለት ለትዳር ጓደኛው የገባውን ቃለ መሐላ ያፈርሳል። በተጨማሪም ‘በአምላክ ላይ ኃጢአት ይሠራል።’ (ዘፍጥረት 39:7-9) ምንዝር ልጆችን ከወላጆች አሰቃቂ በሆነ መንገድ ይነጥላል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ . . . አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋል” በማለት ያስጠነቅቃል።—ዕብራውያን 13:4

“ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን።” ዕብራውያን 13:4

ምንዝር ለትዳር መፍረስ ምክንያት ይሆናል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ያገቡ ሰዎች የትዳር ጓደኛቸው ምንዝር ከፈጸመ መፋታት እንደሚችሉ ይናገራል። (ማቴዎስ 19:9) ይህ ሲባል አንድ ሰው በትዳር ጓደኛው ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ቢፈጽም የተበደለው ወገን ከትዳር ጓደኛው ጋር አብሮ ለመኖር ወይም ለመፋታት ሊወስን ይችላል ማለት ነው። ይህ የግል ውሳኔ ነው።—ገላትያ 6:5

በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ ጋብቻን የሚመለከተው እንደ ዕድሜ ልክ ጥምረት አድርጎ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ‘ከትዳር ጓደኛዬ ጋር መኖር አያስደስተኝም’ እንደሚሉት ባሉ ጥቃቅን ምክንያቶች የተነሳ የትዳር ጓደኛን ለመፍታት መፈለግ በአምላክ ዘንድ የተጠላ ድርጊት ነው። ስለዚህ መፋታት እንደ ቀላል ነገር የሚታይ ውሳኔ አይደለም።—ሚልክያስ 2:16፤ ማቴዎስ 19:3-6

“እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ምንዝር ለመፈጸም እንድትጋለጥ ያደርጋታል።”ማቴዎስ 5:32

ምንዝር ይቅር የማይባል ኃጢአት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አይደለም። ምንዝር የፈጸሙም ሆኑ ሌላ ዓይነት ኃጢአት የሠሩ ሰዎች ንስሐ ከገቡና ከተመለሱ አምላክ ምሕረት እንደሚያደርግላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19፤ ገላትያ 5:19-21) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ምንዝር መፈጸማቸውን ትተው የአምላክ ወዳጅ መሆን ስለቻሉ ሰዎች ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

አምላክ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት ምሕረት አድርጓል። ዳዊት ከጦር መኮንኖቹ አንዱ ከነበረው ሰው ሚስት ጋር ምንዝር ፈጸመ። (2 ሳሙኤል 11:2-4) “ዳዊት ያደረገው ነገር ይሖዋን በጣም አሳዝኖት” እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (2 ሳሙኤል 11:27) ዳዊት ናታን ከወቀሰው በኋላ ስለተጸጸተ አምላክ ይቅርታ አደረገለት። ይሁን እንጂ ዳዊት ድርጊቱ ካስከተለበት መዘዝ ማምለጥ አልቻለም። (2 ሳሙኤል 12:13, 14) ከጊዜ በኋላ ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ምንዝር የሚፈጽም ሁሉ ማስተዋል ይጎድለዋል” በማለት ተናግሯል።—ምሳሌ 6:32

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ምንዝር ፈጽመህ ከነበረ አምላክንና የትዳር ጓደኛህን ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልግሃል። (መዝሙር 51:1-5) ልክ አንደ አምላክ ለምንዝር ጥላቻ ይኑርህ። (መዝሙር 97:10) የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ከመመልከት፣ ስለ ፆታ ግንኙነት ከማውጠንጠን፣ ከማሽኮርመም ወይም የትዳር ጓደኛህ ካልሆነ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ፍላጎት እንዲያድርብህ ከሚያደርግ ማንኛውም ነገር ራቅ።—ማቴዎስ 5:27, 28፤ ያዕቆብ 1:14, 15

የትዳር ጓደኛህ ምንዝር ፈጽሞ ከሆነ አምላክ ስሜትህን እንደሚረዳልህ እርግጠኛ ሁን። (ሚልክያስ 2:13, 14) መጽናኛና መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክ ጸልይ፤ “እሱም ይደግፍሃል።” (መዝሙር 55:22) የትዳር ጓደኛህን ይቅር ለማለትና ትዳራችሁን ለመታደግ ከወሰንክ ሁለታችሁም የጋብቻ ጥምረታችሁን ለማጠናከር ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርባችኋል።—ኤፌሶን 4:32

ምንዝር ከፈጸመ በኋላ በድርጊቱ የተጸጸተውን ዳዊትን ነቢዩ ናታን “ይሖዋም ኃጢአትህን ይቅር ይላል” ብሎታል።2 ሳሙኤል 12:13