በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለመጠቀም የሚረዱ ሰባት ዘዴዎች

ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለመጠቀም የሚረዱ ሰባት ዘዴዎች

ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለመጠቀም የሚረዱ ሰባት ዘዴዎች

“መጽሐፍ ቅዱስ በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሽያጭ በማግኘት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው ከመሆኑም በላይ ከዓመት እስከ ዓመት በብዛት በመሸጥ ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ መጽሐፍ ነው።” —ታይም መጽሔት

“አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን አነባለሁ፤ ሆኖም በጣም አሰልቺ ይሆንብኛል።” —ኪት፣ በእንግሊዝ የሚኖር ታዋቂ ሙዚቀኛ

ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ በእጃቸው ቢኖርም መጽሐፉን በማንበብ እምብዛም ጥቅም የማያገኙ መሆናቸው ያስገርማል። ሌሎች ሰዎች ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያነቡት ነገር ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ናንሲ የተባለች ሴት እንደሚከተለው ትላለች፦ “በየቀኑ ማለዳ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ባነበብኩት ላይ ማሰላሰል ከጀመርኩ ወዲህ በዕለቱ የሚያጋጥመኝን ማንኛውንም ችግር ለመጋፈጥ ዝግጁ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ይህ ልማዴ ያለብኝን የመንፈስ ጭንቀት ለማስታገስ ባለፉት 35 ዓመታት ውስጥ ከሞከርኩት ከማናቸውም ነገር የበለጠ ረድቶኛል።”

መጽሐፍ ቅዱስን አንብበህ የማታውቅ ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች ይህን መጽሐፍ ማንበባቸው እንደጠቀማቸው ሲናገሩ መስማትህ የማወቅ ፍላጎትህን ይቀሰቅሰዋል? መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ ያለህ ሰው ከሆንክ ደግሞ ከንባብህ የበለጠ ጥቅም ማግኘት ብትችል ደስ ይልሃል? ከሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ የተገለጹትን ሰባት ዘዴዎች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።

ዘዴ 1​—ትክክለኛ ዝንባሌ ይኑርህ

▪ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አንድ ጥሩ ሥነ ጽሑፍ በመቁጠር ወይም የማንበብ ግዴታ እንዳለብህ ተሰምቶህ አለዚያም በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለም ውስጥ መመሪያ ለማግኘት በማሰብ ልታነበው ትችል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የበለጠ ጥቅም የምታገኘው ግን ዓላማህ ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ ሲሆን ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን የምታነበው መልእክቱ ሕይወትህን እንዲለውጠው በማሰብ ከሆነ ብዙ በረከት ታጭዳለህ።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ቃል በትክክለኛ ዝንባሌ ተነሳስቶ የማንበብን አስፈላጊነት ያጎላል፤ ቃሉን ከመስታወት ጋር በማነጻጸር እንዲህ ይላል፦ “ማንም ቃሉን የሚሰማ እንጂ የማያደርገው ከሆነ ይህ ሰው የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት እያየ ካለ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ይህ ሰው ራሱን ካየ በኋላ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል። ሆኖም ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ በትኩረት የሚመለከትና በዚያም የሚጸና ሰው ሰምቶ የሚረሳ ሳይሆን በሥራ ላይ የሚያውል ሰው ስለሆነ ይህን በማድረጉ ደስተኛ ይሆናል።”—ያዕቆብ 1:23-25

በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሰው ፊቱን በመስታወት ቢያይም በመልኩ ላይ ያለውን እንከን ሳያስተካክል ቀርቷል። ይህ ሰው ፊቱን የተመለከተው በችኮላ ሊሆን ይችላል፤ ወይም አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ፍላጎት አልነበረውም። በተመሳሳይ እኛም መጽሐፍ ቅዱስን የምናነበው እንደነገሩ ከሆነ ወይም የምናነበውን በሥራ ላይ ካላዋልነው እምብዛም አይጠቅመንም። በተቃራኒው ቃሉን ‘በሥራ ላይ ለማዋል’ ብለን መጽሐፍ ቅዱስን የምንመረምር ይኸውም የአምላክ ቃል አስተሳሰባችንን እንዲቀርጸውና በድርጊታችን ላይ ለውጥ ለማድረግ እንዲያነሳሳን የምንፈቅድ ከሆነ እውነተኛ ደስታ ልናገኝ እንችላለን።

ዘዴ 2​—እምነት የሚጣልበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ምረጥ

▪ በቋንቋህ የተዘጋጁ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይኖሩ ይሆናል። ማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሊጠቅምህ ቢችልም አንዳንዶቹ ትርጉሞች በአሁኑ ጊዜ የማይዘወተሩ የድሮ ቃላትን ወይም የምሑራንን ቋንቋ ስለሚጠቀሙ ‘ተራው ሰው’ ለመረዳት አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 4:13) እንዲያውም አንዳንድ ትርጉሞች በወግና በባሕል በመመራት ንጹሕ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በርዘውታል። ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ መጽሔት የመጀመሪያዎቹ ርዕሶች ላይ እንደተገለጸው አንዳንዶቹ ተርጓሚዎች ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም “አምላክ” ወይም “ጌታ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ተክተውታል። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በትክክል የሚያስቀምጥ፣ ለመረዳት ቀላል የሆነና የማንበብ ፍላጎትን የሚቀሰቅስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ምረጥ።

በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢያን በዚህ ረገድ አዲስ ዓለም ትርጉምን ተስማሚ ሆኖ አግኝተውታል። * በቡልጋሪያ የሚኖሩ አንድ አረጋዊ ሰው ምን እንዳጋጠማቸው እንመልከት። እኚህ ሰው በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኝተው ሳሉ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተሰጣቸው። በኋላ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ለብዙ ዓመታት አንብቤያለሁ፤ ይሁን እንጂ እንደ አዲስ ዓለም ትርጉም ያለ ለመረዳት ቀላል የሆነና ልብን በጥልቅ የሚነካ ትርጉም አይቼ አላውቅም።”

ዘዴ 3​—ጸልይ

▪ “ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት” ብሎ እንደጸለየው መዝሙራዊ አንተም የመጽሐፍ ቅዱስን ባለቤት እርዳታ የምትጠይቅ ከሆነ ስለ መጽሐፉ የበለጠ ማስተዋል ማግኘት ትችላለህ። (መዝሙር 119:18) መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብክ ቁጥር ቃሉን መረዳት እንድትችል አምላክ እንዲረዳህ በጸሎት ጠይቀው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ስለሰጠህ አምላክን ልታመሰግነው ትችላለህ፤ ምክንያቱም ይህ መጽሐፍ ባይኖር ኖሮ ስለ እሱ አናውቅም ነበር።—መዝሙር 119:62

አምላክ እርዳታ ለማግኘት የሚቀርቡ ጸሎቶችን ይሰማል? በኡራጓይ የሚኖሩ ሁለት ወጣት እህትማማቾች ያጋጠማቸውን ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዳንኤል 2:44 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ግራ ስላጋባቸው አምላክ ይህን ጥቅስ የሚያብራራላቸው ሰው እንዲልክላቸው ጸለዩ። ወጣቶቹ ገና መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ሳይከድኑት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታቸው መጡ፤ ከዚያም ወጣቶቹ በጸሎታቸው ላይ አንስተውት የነበረውን ያንኑ ጥቅስ አውጥተው ካነበቡ በኋላ ይህ ጥቅስ የሚገልጸው ወደፊት ሰብዓዊ መንግሥታት በአምላክ መንግሥት እንደሚተኩ መሆኑን አብራሩላቸው። * እህትማማቾቹ አምላክ ጸሎታቸውን እንደመለሰላቸው እርግጠኞች ነበሩ።

ዘዴ 4​—በየቀኑ አንብብ

▪ አንድ የመጻሕፍት አሳታሚ መስከረም 11, 2001 በዩናይትድ ስቴትስ ላይ አሸባሪዎች ጥቃት ካደረሱ ወዲህ “የመጽሐፍ ቅዱስ ሽያጭ በአንድ ጊዜ እንደተተኮሰ” ገልጿል። ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ ቃል ፊታቸውን የሚያዞሩት ሲጨነቁ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ እንድናነበው ሲያበረታታ እንዲህ ይላል፦ “ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ እንድትፈጽመውም ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው፤ ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም።”—ኢያሱ 1:8

መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማንበብ ያለውን ጠቀሜታ ለማስረዳት ልቡን የታመመ ሰውን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፤ ግለሰቡ ከወትሮው የበለጠ ለጤናው ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን ለመመገብ ወሰነ እንበል። ሰውየው እንዲህ ዓይነቱን አመጋገብ የሚከተለው ደረቱ አካባቢ ኃይለኛ ሕመም ሲሰማው ብቻ ቢሆን ይጠቅመዋል? በጭራሽ። የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ይህን ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ያለማቋረጥ ሊከተለው ይገባል። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበብ ‘ያሰብኸው እንዲቃና’ ይረዳሃል።

ዘዴ 5​—የተለያዩ መንገዶችን ተጠቀም

▪ መጽሐፍ ቅዱስን ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ማንበብ ጥሩ ቢሆንም ሌሎች መንገዶችንም መጠቀምህ ንባብህ አስደሳች እንዲሆንልህ ሊረዳህ ይችላል። ከዚህ በታች አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል።

በአንድ ግለሰብ ላይ ትኩረት አድርገህ አንብብ። በአንድ የአምላክ አገልጋይ ላይ ትኩረት በማድረግ ስለ እሱ የሚገልጹትን ምዕራፎች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሙሉ አንብባቸው፤ ለምሳሌ፦

ዮሴፍ፦ ዘፍጥረት 37 እስከ 50

ሩት፦ ሩት 1 እስከ 3

ኢየሱስ፦ ማቴዎስ 1 እስከ 28፤ ማርቆስ 1 እስከ 16፤ ሉቃስ 1 እስከ 24፤ ዮሐንስ 1 እስከ 21 *

በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገህ አንብብ። ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጥቅሶች አንብባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ጸሎት ምርምር ማድረግ ትችላለህ፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸሎት የሚሰጠውን ምክርና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት በርካታ ጸሎቶች መካከል አንዳንዶቹን አንብብ። *

ጮክ ብለህ አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስን ጮክ ብለህ በማንበብ በእጅጉ ልትጠቀም ትችላለህ። (ራእይ 1:3) እንዲያውም በቤተሰብ ይህን ዘዴ መጠቀም ትችላላችሁ፤ አንቀጾቹን በመከፋፈል ወይም የተለያዩ የቤተሰብ አባላት በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች ወክለው እንዲያነቡ በመመደብ መጽሐፍ ቅዱስን ጮክ ብላችሁ ልታነቡ ትችላላችሁ። አንዳንዶች በድምፅ የተቀረጸ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ማዳመጥ ያስደስታቸዋል። አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለመጀመር በጣም ከብዶኝ ስለነበር በድምፅ የተቀረጸውን ማዳመጥ ጀመርኩ። አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ ጥሩ ልብ ወለድ የበለጠ ስሜት የሚመስጥ መጽሐፍ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ።”

ዘዴ​—6 አሰላስል

▪ ያለንበት ዘመን ወከባ የበዛበትና ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮች የሞሉበት በመሆኑ ለማሰላሰል የሚያስችል ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ የተመገብነው ነገር ጥቅም እንዲሰጠን ከሰውነታችን ጋር መዋሐድ እንዳለበት ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጥቅም ለማግኘትም በምናነበው ነገር ላይ ማሰላሰል አለብን። ይህን የምናደርገው ያነበብነውን ነገር በአእምሯችን በመከለስና ራሳችንን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች በመጠየቅ ነው፦ ‘ያነበብኩት ነገር ስለ ይሖዋ አምላክ ምን ያስተምረኛል? በእኔ ሕይወት ውስጥ የሚሠራው እንዴት ነው? ሌሎችን ለመርዳት ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?’

እንዲህ እያሉ ማሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ልባችንን እንዲነካው የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ የአምላክን ቃል በማንበብ የምናገኘውን ደስታ ከፍ ለማድረግ ያስችላል። መዝሙር 119:97 “አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” ይላል። መዝሙራዊው በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ቀኑን ሙሉ ማሰላሰሉ ለተማረው ነገር ጥልቅ ፍቅር እንዲያዳብር ረድቶታል።

ዘዴ 7​—መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት እርዳታ ጠይቅ

▪ አምላክ ቃሉን ያለ ማንም እርዳታ ሙሉ በሙሉ እንድንረዳ አይጠብቅብንም። ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ “ለመረዳት የሚከብዱ አንዳንድ ነገሮች” እንደያዘ ይገልጻል። (2 ጴጥሮስ 3:16) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን ያነበው የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመረዳት ተቸግሮ እንደነበረ ይገልጻል። አምላክ ይህን ሰው ለመርዳት ከአገልጋዮቹ አንዱን ላከለት፤ በውጤቱም ኢትዮጵያዊው ሰው “ደስ ብሎት ጉዞውን [ቀጥሏል]።”—የሐዋርያት ሥራ 8:26-39

አንተም እንዲሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የበለጠ ጥቅም ማግኘት እንድትችል የምታነበውን ለመረዳት እገዛ ማግኘት ትችላለህ። በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች አነጋግራቸው፤ አለዚያም መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለማጥናት ከፈለግህ በዚህ መጽሔት ገጽ 4 ላይ ካሉት አድራሻዎች ለአንተ አመቺ ወደሆነው ጻፍ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም በሙሉ አሊያም በከፊል አማርኛን ጨምሮ በ83 ቋንቋዎች ታትሟል፤ በተጨማሪም www.watchtower.org በሚለው ድረ ገጻችን ላይ በ17 ቋንቋዎች ይገኛል።

^ አን.15 ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ምን እንደሚያከናውን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ተመልከት።

^ አን.24 መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ የመጀመሪያ ጊዜህ ከሆነ የኢየሱስን አገልግሎት አጠር አድርጎ ከዘገበው ከማርቆስ መጽሐፍ ጀምር።

^ አን.25 ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን በርዕስ ከፋፍሎ ለማጥናት አመቺ ሆኖ አግኝተውታል። ለምሳሌ ምዕራፍ 17 ጸሎትን በተመለከተ ቅዱሳን መጻሕፍት ምን እንደሚሉ ያብራራል።