በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አርማጌዶን ምንድን ነው?

አርማጌዶን ምንድን ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

አርማጌዶን ምንድን ነው?

▪ ብዙ ሰዎች “አርማጌዶን” የሚለውን ቃል ሲሰሙ ወደ አእምሮአቸው የሚመጣው በኑክሌር ጦርነት ወይም መጠነ ሰፊ በሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች አሊያም የምድር ሙቀት መጨመር በአካባቢ ላይ በሚያስከትለው ጉዳት የተነሳ የሚከሰት ጅምላ ጨራሽ እልቂት ነው። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ይህ ቃል እነዚህን ነገሮች አያመለክትም። ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው አርማጌዶን ምንድን ነው?

“አርማጌዶን” (“ሐር ማጌዶን”) የሚለው ቃል የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የራእይ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ይህ ቃል አንድን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጦርነት ማለትም ‘ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ የሚያመለክት ሲሆን በዚያን ጊዜ ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ ከአምላክ ጋር የመጨረሻ ጦርነት ለማድረግ በአንድነት ይንቀሳቀሳሉ። እንዲህ ዓይነቱ ጦርነት በሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይም ተጠቅሶ ይገኛል።​—ራእይ 16:14-16፤ ሕዝቅኤል 38:22, 23፤ ኢዩኤል 3:12-14፤ ሉቃስ 21:34, 35፤ 2 ጴጥሮስ 3:11, 12

ይህ ጦርነት ምን ያስከትላል? የራእይ መጽሐፍ “የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት” እንደተሰበሰቡ የሚገልጽ ምሳሌያዊ አነጋገር በመጠቀም ይህ ጦርነት ምን መልክ እንደሚኖረው ይነግረናል። ‘በፈረሱ ላይ የተቀመጠ’ የተባለው፣ የመላእክትን ሠራዊት በመምራት በአምላክ ጠላቶች ላይ ድል እንዲቀዳጅ አምላክ ራሱ የሾመው የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ራእይ 19:11-16, 19-21) ኤርምያስ 25:33 በክፉዎች ላይ የሚደርሰው ይህ ጥፋት ምን ያህል ስፋት እንደሚኖረው ሲገልጽ “በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ” ይላል።

የአርማጌዶን ጦርነት መካሄዱ ለምን አስፈለገ? ብሔራት የአምላክን ሉዓላዊነት አምነው ከመቀበል ይልቅ የራሳቸውን ሉዓላዊነት ያውጃሉ። (መዝሙር 24:1) ይህ እብሪታቸው ደግሞ በ⁠መዝሙር 2:2 ላይ “የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ፣ ሊመክሩ ተሰበሰቡ” ተብሎ ተገልጿል።

በመሆኑም እነዚህ ብሔራት ንብረታቸው ያልሆነውን ርስት ከመውሰድም አልፈው በዚያ ያላግባብ ከሚጠቀሙና ርስቱን ከሚያበላሹ ዓመፀኛ ከሆኑ ሕገ ወጥ ሰፋሪዎች ጋር ይመሳሰላሉ። ዛሬ ያሉት ብሔራት ምድርን እያበላሹ እንዲሁም እየበከሉ ናቸው። የአምላክ ቃል “ሕዝቦች ተቆጡ፤ [የአምላክም] ቁጣ መጣ” በማለት ቅጣት ስለሚገባው ስለዚህ ድርጊት አስቀድሞ ተናግሯል። በመሆኑም አምላክ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን” ያጠፋል። (ራእይ 11:18) እንግዲያው አርማጌዶን፣ ‘በመላው የሰው ዘር ላይ የመግዛት መብት ያለው ማን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ እልባት ለመስጠት ሲል አምላክ የሚወስደው እርምጃ ነው።​—መዝሙር 83:18

የአርማጌዶን ጦርነት የሚካሄደው መቼ ነው? የአምላክ ልጅ “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:36) ሆኖም ተዋጊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ አርማጌዶንን አስመልክቶ ሲናገር ‘እነሆ፣ እንደ ሌባ እመጣለሁ። ነቅቶ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው’ በማለት አስጠንቅቋል። (ራእይ 16:15) በዚህም ምክንያት ይህ ዓለም አቀፍ ጦርነት ከክርስቶስ መገኘት ጋር የሚያያዝ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ደግሞ አሁን በዚያ ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር ያሳያሉ።

አርማጌዶን የሚያጠፋው ከስህተታቸው ለመታረም ፈቃደኛ ያልሆኑ ክፉ ሰዎችን ብቻ ሲሆን ከጥፋቱ የሚተርፍ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ይኖራል። (ራእይ 7:9-14) ይህ ሕዝብ የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሲፈጸም ይመለከታል፦ “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”​—መዝሙር 37:10, 11

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ”