በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኦሊቬታ​—የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ያዘጋጀው “ትሑት የሆነው ትንሹ ተርጓሚ”

ኦሊቬታ​—የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ያዘጋጀው “ትሑት የሆነው ትንሹ ተርጓሚ”

ኦሊቬታ​—የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ያዘጋጀው “ትሑት የሆነው ትንሹ ተርጓሚ”

ጊዜው መስከረም 13, 1540 ነበር። ፖሊሶች የኮላን ፔላክን ቤት እየፈተሹ ነበር። በአንዲት ሰዋራ ክፍል ውስጥ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ አንዳንድ ሰነዶችን ያገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንድ ትልቅ መጽሐፍ ይገኝበታል። በሁለተኛው ገጽ ላይ “ፒየር ሮቤር ኦሊቬታኑስ፣ ትሑት የሆነው ትንሹ ተርጓሚ” የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል። መጽሐፉ ዋልደንሳውያን ያዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱስ ነበር! በመሆኑም ኮላን ፔላክ ታሰረ፤ ከዚያም ‘መናፍቅ ነህ’ ተብሎ ስለተፈረደበት ከነሕይወቱ በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት ተደረገ።

በዚያን ጊዜ እንደ ሌሎቹ የአውሮፓ አገሮች ሁሉ በፈረንሳይም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የተሃድሶው አራማጆች የሚያስፋፉትን “በካይ” የሆኑ መሠረተ ትምህርቶች ለማጥፋት ሰዎቹን እግር በእግር ትከታተል ነበር። ከተሃድሶው እንቅስቃሴ አራማጆች መካከል አንዱ የሆነውና በኃይለኛ ተናጋሪነቱ የሚታወቀው ጊዮም ፋረል፣ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ዋና አቀንቃኝ የነበረው የማርቲን ሉተር አመለካከት ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በሆነው ዓለም ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ቆርጦ ነበር። በፈረንሳይ ደቡባዊ ምሥራቅ በምትገኘው በዶፊኔ የተወለደው ፋረል፣ የሰዎችን አመለካከት ለመለወጥ ጽሑፎች ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ተገንዝቦ ነበር። ተልእኮውን ዳር ለማድረስ ብዛት ያለው ፓምፍሌትና መጣጥፍ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት አስፈልጎት ነበር። ይሁንና ለሥራው የሚያስፈልገውን ወጪ ማን ይሸፍናል? ዋልደንሳውያን ይችሉ ይሆን? እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመስበኩ ሥራ ትኩረት በመስጠት ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ናቸው።

በሻፎራ የተካሄደ ሲኖዶስ

በመስከረም 1532 አጋማሽ ላይ የዋልደንሳውያን ባርብ (ፓስተሮች) በቱሪን፣ ጣሊያን አቅራቢያ በምትገኝ ሻፎራ የተባለች መንደር ሲኖዶስ ወይም ስብሰባ አካሄዱ። በዋልደንሳውያን እና በተሃድሶው መሪዎች መካከል ለበርካታ ዓመታት የሐሳብ ልውውጥ ሲካሄድ ቆይቶ ነበር። በመሆኑም ፋረል እና ሌሎች በርከት ያሉ ሰዎች በሲኖዶሱ ላይ እንዲገኙ ግብዣ ቀረበላቸው። ዋልደንሳውያን መሠረተ ትምህርታቸው ሉተርና ደቀ መዛሙርቱ ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር ይስማማ እንደሆነ ለማወቅ ፈልገው ነበር። *

አንደበተ ርቱዕ የነበረው ፋረል በሻፎራ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ያቀረበው ሐሳብ አሳማኝ ሆኖ ተገኘ። የዋልደንሳውያን ባርብ በራሳቸው ቀበሌኛ የተዘጋጁ በእጅ የተጻፉ የቆዩ መጽሐፍ ቅዱሶችን ሲያሳዩት ፋረል የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለማሳተም የሚያስፈልገውን ወጪ እንዲሸፍኑ አሳመናቸው። በ1523 ሌፌቭር ዴታፕል ከላቲን ከተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒ ይኼኛው የትርጉም ሥራ ከዕብራይስጡና ከግሪክኛው ጽሑፍ እንዲተረጎም ታስቦ ነበር። ይሁንና ይህን ሥራ ማን ሊያከናውን ይችላል?

ፋረል ለዚህ ሥራ ብቁ የሆነ ሰው ያውቅ ነበር። ይህ ሰው ፒየር ሮቤር ሲሆን የሚታወቀው ግን ኦሊቬታ * በሚለው ስሙ ነው፤ ኦሊቬታ በሰሜን ፈረንሳይ በምትገኘው ፒካርዲ የተባለች መንደር የተወለደ ወጣት መምህር ነበር። የጆን ካልቪን ዘመድ የሆነው ኦሊቬታ ቀደምት ከሆኑት የተሃድሶው አራማጆች መካከል አንዱ ሲሆን እምነት የሚጣልበት ሰው ነበር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች በትጋት በማጥናት በስትራዝቡርግ የተወሰኑ ዓመታትን አሳልፏል።

ኦሊቬታ እንደ ፋረልና እንደ ሌሎች በርካታ ሰዎች ስዊዘርላንድ ውስጥ በስደት ለመኖር ተገድዶ ነበር። ጓደኞቹ የትርጉም ሥራውን እንዲያከናውን አጥብቀው ለመኑት። ይህን ሥራ ለመቀበል በተደጋጋሚ ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀርም መጨረሻ ላይ ግን መጽሐፍ ቅዱስን “በዕብራይስጥና በግሪክኛ ቋንቋ ላይ ተመሥርቶ ወደ ፈረንሳይኛ” እንዲተረጉም የተሰጠውን ተልእኮ ተቀበለ። በዚህ ጊዜ ዋልደንሳውያን የኅትመት ወጪውን ለመሸፈን ከሚያስፈልገው 800 የወርቅ ሳንቲም መካከል 500 የሚያህለውን ለመክፈል ተስማሙ፤ በወቅቱ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ነበር!

ቁራውና ዘማሪዋ ወፍ

በ1534 መጀመሪያ ላይ ኦሊቬታ ብቻውን ወደሚሆንበት ወደ አልፕስ ተራሮች በመሄድ “ድምፅ አልባ መምህራን” በሆኑት መጻሕፍቱ ተከቦ ሥራውን ማከናወን ጀመረ። የኦሊቬታን የመጻሕፍት ስብስብ የተመለከተ በዛሬው ጊዜ የሚገኝ የትኛውም ምሁር የቅናት ስሜት እንደሚያድርበት ምንም ጥርጥር የለውም። ከነበሩት መጻሕፍት መካከል በሲሪያክ፣ በግሪክኛና በላቲን የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ የረቢዎችን ትንታኔ የያዙ ጽሑፎች፣ የከለዳውያን የሰዋስው መጻሕፍትና ሌሎች በርካታ መጻሕፍት ይገኙበታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የዕብራይስጥን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጥንታዊ ቅጂ የያዘውና በወቅቱ አዲስ የነበረው የቬኒስ ትርጉም በእጁ ይገኝ ነበር።

ኦሊቬታ በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተረጎመው ሌፌቭር ዴታፕል በፈረንሳይኛ ባዘጋጀው ትርጉም ላይ ተመሥርቶ ነው፤ ይሁንና ሆላንዳዊው ምሁር ኢራስመስ ያዘጋጀውን ግሪክኛ ጽሑፍም ብዙ ጊዜ ያመሣክር ነበር። የኦሊቬታ የቃላት ምርጫ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታሳድረውን ተጽዕኖ ለማዳከም የታለመ ነበር። ለምሳሌ “ቄስ” በሚለው ፋንታ “የበላይ ተመልካች” እንዲሁም “ቤተ ክርስቲያን” በሚለው ፋንታ “ጉባኤ” የሚለውን ስያሜ መጠቀምን መርጧል።

ኦሊቬታ ብዙዎች ብሉይ ኪዳን ብለው የሚጠሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከዋናው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ላይ ቃል በቃል ተርጉሞታል። ከዕብራይስጥ ወደ ፈረንሳይኛ መተርጎም “አንዲት ዘማሪ ወፍን ጎርናና ድምፅ እንዳለው እንደ ቁራ እንድትዘምር የማስተማር ያህል ነው” ሲል በቀልድ መልክ ተናግሯል!

ኦሊቬታ ቴትራግራማተን ተብለው በሚጠሩት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት የሚወከለው መለኮታዊ ስም በዕብራይስጡ ጽሑፍ ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ጊዜያት አጋጥሞታል። ይህን ስም “ዘላለማዊው” በማለት ለመተርጎም የመረጠ ሲሆን ይህ አገላለጽ ከጊዜ በኋላ በፕሮቴስታንት የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የተለመደ ሆኗል። ይሁንና በተወሰኑ ቦታዎች ላይ “ይሖዋ” የሚለውን ስም ተጠቅሟል፤ በዚህ ረገድ ዘፀአት 6:3 ተጠቃሽ ነው።

ተርጓሚው የካቲት 12, 1535 ላይ ሥራውን እንዳጠናቀቀ መናገሩ የሚያስደንቅ ነበር፤ ምክንያቱም ሥራውን የፈጸመው በአንድ ዓመት ገደማ ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው! “ይህ [የትርጉም ሥራ] ባለፉት ጊዜያት ሁሉ አብሮት የቆየ” እንደሆነ የገለጸ ከመሆኑ አንጻር 1534/1535 ለረጅም ጊዜ ሲያከናውነው የነበረው አድካሚ ሥራ የተደመደመበት ዓመት ነበር። ይህ ተርጓሚ “አቅሜ የሚፈቅደውን ሁሉ አድርጌአለሁ” ሲል በትሕትና ተናግሯል። አሁን የቀረ ነገር ቢኖር የዕብራይስጥና የግሪክኛውን መጽሐፍ ቅዱስ ከግምት በማስገባት የተተረጎመውን የመጀመሪያውን የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ማሳተም ብቻ ነው።

የፒሮ ማተሚያ ቤት

የተሃድሶው አራማጅ የሆነውና የራሱ ማተሚያ ቤት የነበረው የፋረል ጓደኛ ፒየር ደቨንግለ (ፒሮ ፒካር ተብሎም ይጠራል) በዚህ ሥራ ላይ መሳተፍ ጀመረ። ደቨንግለ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ የተነሳ ሊዮንን ለቅቆ እንዲወጣ ከተገደደ በኋላ በ1533 ወደ ኑሻቴል፣ ስዊዘርላንድ ሄደ። እሱም ከዋልደንሳውያን በተገኘ ገንዘብ ብዛት ያለው “የክህደት” ጽሑፍ ማተም ጀመረ። ለምሳሌ ያህል፣ ቁርባንን የሚያወግዙ ፖስተሮች የታተሙት እሱ ማተሚያ ቤት ውስጥ ነበር፤ ከእነዚህ ፖስተሮች መካከል አንዳንዶቹ የፈረንሳይ ንጉሥ ቀዳማዊ ፍራንስዋ እጅ ሊገቡ ችለዋል።

ደቨንግለ ማተሚያዎቹን በድጋሚ ሥራ ያስጀመረ ሲሆን በዚህ ጊዜ ግን ተልእኮው መጽሐፍ ቅዱስ ማተም ነበር! ኅትመቱን ለማፋጠን ፊደሎቹን የሚለቅሙና ገጾቹን የሚያትሙ እያንዳንዳቸው አራት ወይም አምስት ሠራተኞችን ያቀፉ ሁለት ቡድኖች በሁለቱ የማተሚያ መሣሪያዎች ላይ ተመድበው ይሠሩ ነበር። በመጨረሻም ደቨንግለ፣ በኦሊቬታ መጽሐፍ ቅዱስ የአሳታሚው ገጽ ላይ “ሰኔ 4 ቀን 1535” ፊርማውን አሰፈረ። ተርጓሚው በመቅድሙ ላይ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ “ከንቱ በሆኑ ወጎች . . . ለተደቆሱና ሸክም ለበዛባቸው” ምስኪን አማኞች የተበረከተ መሆኑን ጠቅሷል።

ሥራው በማንኛውም መለኪያ የተፈለገውን ደረጃ ያሟላ ነበር። ሁለት ዓምዶች ያሉት እንዲሁም በምዕራፍና በአንቀጾች ተከፋፍሎ የተቀመጠው የፈረንሳይኛው ጽሑፍ፣ የአጻጻፍ ውበት ያለውና ለመረዳት የማያስቸግር ከመሆኑም ባሻገር ልቅም ባለና በሚያምር የጎቲክ ፊደል የተጻፈ መሆኑ ላቅ ያለ ጥራት እንዲኖረው አድርጓል። የግርጌ ማስታወሻዎቹ ተርጓሚው ሙያዊ ክህሎት እንዳለው ይመሠክራሉ። የመግቢያ ሐሳቦቹ፣ ተጨማሪ ክፍሎቹ፣ ሠንጠረዦቹና ግጥሞቹ ለሥራው ውበት ጨምረውለታል። በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ “ወንጌል ሰባኪዎቹ ዋልደንሳውያን፣ ይህን ውድ ሀብት አደረሱ ለብዙኃን” የሚል አጭር ግጥም ሰፍሮ ይገኛል።

የተዋጣለት ቢሆንም ለኪሳራ የተዳረገ ሥራ

በአንድ ወቅት ሰዎች የኦሊቬታን ሥራ አጣጥለውት የነበረ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የተዋጣለት የትርጉም ሥራ እንደሆነ ብዙዎች በአንድ ድምፅ ይስማማሉ። ከዚህም በላይ የእሱ የትርጉም ሥራ ፕሮቴስታንቶች ላዘጋጇቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለሦስት ምዕተ ዓመታት መሠረት ሆኖ አገልግሏል።

የኦሊቬታ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አንድ ሺህ ገደማ በሚቆጠሩ ቅጂዎች ታትሞ የነበረ ቢሆንም የመጽሐፉ ሽያጭ አመርቂ አልነበረም። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱሱን በተደራጀ መንገድ ለማሰራጨት የሚያስችል መዋቅር አለመኖሩና ወቅቱ ፈረንሳይኛ ፈጣን ለውጥ እያደረገ የነበረበት መሆኑ ነው። ከዚህም ባሻገር 5 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ይህ መጽሐፍ ከቦታ ቦታ ለሚጓዙ ሰባኪዎችና መጽሐፉን በድብቅ ለሚያነቡ ሰዎች ምቹ አልነበረም።

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው በፈረንሳይ በሚኖረው በኮላን ፔላክ ቤት የኦሊቬታ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ቅጂ ከመገኘቱ ውጭ ከሽያጭ አኳያ ሲታይ ለኪሳራ የተዳረገ መጽሐፍ ነው ሊባል ይችላል። ከ150 ዓመት ገደማ በኋላ ይኸውም በ1670 በጄኔቫ የሚገኝ አንድ የመጽሐፍ መሸጫ መደብር ውስጥ የዚህ መጽሐፍ አንድ ቅጂ ይገኝ ነበር።

“ስሙም ሆነ አድራሻው የማይታወቅ”

ኦሊቬታ ተልእኮውን ካጠናቀቀ በኋላ አድራሻውን አጠፋ። ኦሊቬታ ስሙን በመቀየር እሱ በተረጎመው አዲስ ኪዳን እና የብሉይ ኪዳን የተወሰኑ ክፍሎች ላይ ማሻሻያ አደረገ። በሌላ በኩል ደግሞ በጣም ለሚወደው ሌላ ሙያው ይኸውም ለማስተማር ሥራው ያደረ ሰው ነበር። አሳቢ መምህር የነበረው ኦሊቬታ፣ ለልጆች የሚሆን መመሪያ የተባለ መጽሐፉን አሻሽሎ አውጥቷል፤ ይህ መጽሐፍ ለልጆች የሚጠቅሙ የሥነ ምግባር ትምህርቶችን የያዘ ከመሆኑም ሌላ በፈረንሳይኛ ንባብ ለማስተማር የሚረዱ ሙሉ በሙሉ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ ሐሳቦችን የያዘ ነበር። ከኦሊቬታ የብዕር ስሞች መካከል ቤሊሴም ደ ቤሊማኮም የሚለው የሚገኝበት ሲሆን ትርጉሙ “ስሙም ሆነ አድራሻው የማይታወቅ” ማለት ነው።

ኦሊቬታ በ1538 በ30ዎቹ ዕድሜው መጀመሪያ ላይ ሕይወቱ አለፈ፤ የሞተው በሮም እንደሆነ ይገመታል። በዛሬው ጊዜ፣ በፒካርዲ የተወለደው ይህ ወጣት ምሁር ከፈረንሳይ መጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት ጋር በተያያዘ የተጫወተውን ቁልፍ ሚና የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች ናቸው። የእሱ ስም የሚገኝባቸው መዝገበ ቃላት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ይህም “ትሑት የሆነው ትንሹ ተርጓሚ” ተብሎ ለተጠራውና ኦሊቬታ በሚለው ቅጽል ስሙ ከሚታወቀው ሉዊ ሮቤር ባሕርይ ጋር የሚስማማ ነው ማለት ይቻላል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ዋልደንሳውያን፣ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ያደርግ በነበረው ቡድን እንዴት እንደተዋጡ ይበልጥ ለማወቅ የመጋቢት 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 20-23 ተመልከት።

^ አን.7 ሲወለድ ሉዊ ሮቤር ተብሎ ይጠራ የነበረ ቢሆንም እሱ ግን መጠሪያ ስሙ ፒየር እንዲሆን መርጧል። ኦሊቬታ የሚል ቅጽል ስም የወጣለት ኩራዝ በመጠቀም ረዘም ያለ ሰዓት በሥራ ተጠምዶ ስለሚያሳልፍ ብርሃን ለማግኘት የሚጠቀምበትን ብዙ የወይራ ዘይት (ኦሊቭ ኦይል) ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Archives de la Ville de Neuchâtel, Suisse /Photo: Stefano Iori

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Left photo: Alain Leprince - La Piscine-musée, Roubaix / Courtesy of the former Bouchard Museum, Paris

Center and right: Société de l’Histoire du Protestantisme Français, Paris

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Société de l’Histoire du Protestantisme Français, Paris