በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ወጣት ልጃችሁ እምነት ሲያጓድል

ወጣት ልጃችሁ እምነት ሲያጓድል

 አንዳንድ ልጆች ከተፈቀደላቸው ሰዓት በላይ ያመሻሉ። ሌሎች ደግሞ ለወላጆቻቸው በመዋሸት ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት ሲሉ ተደብቀው ከቤት በመውጣት ወላጆቻቸውን ያታልላሉ። ወጣት ልጃችሁ በዚህ መልኩ እምነት ቢያጓድል ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

 ልጃችን ዓመፀኛ ሆኗል ማለት ነው?

 ላይሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በወጣት ልብ ውስጥ ታስሯል” ይላል፤ የአብዛኞቹ ወጣቶች ሁኔታ የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት ያረጋግጣል። (ምሳሌ 22:15 ግርጌ) ዶክተር ሎረንስ ስታይንበርግ እንዲህ ብለዋል፦ “በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች አንዳንድ ጊዜ የችኮላና የሞኝነት ውሳኔ ያደርጋሉ። ስለዚህ ስህተት መሥራታቸው አይቀርም።” a

 ልጃችን ቢያታልለንስ?

 ልጃችሁ ሆን ብሎ ሊያምፅባችሁ እየሞከረ እንዳለ ለመደምደም አትቸኩሉ። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ስለ ወላጆቻቸው ግድ የማይሰጣቸው ቢመስሉም ወላጆቻቸው ለእነሱ ያላቸው አመለካከት በጣም ያሳስባቸዋል። ልጃችሁ ከውጭ ሲታይ ባይመስልም ባደረገው ነገር ተቆጭቶ ሊሆን ይችላል፤ እናንተን በማሳዘኑም በጣም አዝኖ መሆን አለበት። b

የተሰበረ አጥንት ካገገመ በኋላ ጥንካሬውን መልሶ ያገኛል። አንድ ወጣትም ያጣውን እምነት መልሶ ማግኘት ይችላል

 ተጠያቂው ማን ነው?

  •    አዋዋሉ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) በእርግጥም ወጣቶች ከጓደኞቻቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊደርስባቸው ይችላል። እንደ ማኅበራዊ ሚዲያ እና ማስታወቂያ ያሉ ነገሮችም በወጣቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በዚህ ላይ ደግሞ ወጣቶች የሕይወት ተሞክሮ የላቸውም፤ ከዚህ አንጻር ወጣቶች አንዳንድ ጊዜ የሞኝነት ውሳኔ የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። እርግጥ ነው፣ አዋቂ ሲሆኑ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሆኑ ከተፈለገ ውሳኔያቸው ለሚያስከትለው ውጤት ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርባቸዋል።

  •    ችግሩ ከእኛ ይሆን? በጣም ጥብቅ በመሆናችሁ ምክንያት ልጃችሁ እንዲያምፅ እንደገፋፋችሁት ይሰማችሁ ይሆናል። ወይም ደግሞ በጣም ልል እንደሆናችሁና ለልጃችሁ ከመጠን በላይ ነፃነት እንደሰጣችሁት ታስቡ ይሆናል። ለችግሩ መንስኤ የሆናችሁት እንዴት እንደሆነ ከማሰብ ይልቅ ችግሩን መፍታት የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ።

 ልጃችን መልሶ እምነት ማትረፍ እንዲችል ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው?

  •   ስሜታችሁን ተቆጣጠሩ። ልጃችሁ እንደምትቆጡት ሊጠብቅ ይችላል። ለምን የተለየ ምላሽ ለመስጠት አትሞክሩም? የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ ከልጃችሁ ጋር በእርጋታ ተነጋገሩ። የማወቅ ጉጉት አድሮበት ነው? ደብሮት ነው? ብቸኝነት ተሰምቶት ነው? ጓደኞቹን እንዳያጣ ፈርቶ ነው? እርግጥ እነዚህ ነገሮች ልጃችሁ ለሠራው ጥፋት ሰበብ አይሆኑም፤ ሆኖም በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየታችሁ ልጃችሁን ወደዚህ ጥፋት ያመራው ነገር ምን እንደሆነ እንድትገነዘቡ ይረዳችኋል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።”—ያዕቆብ 1:19

  •   ልጃችሁን ከስህተቱ ትምህርት እንዲያገኝ እርዱት። ‘ከዚህ ሁኔታ ምን ትምህርት አገኘህ? ሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቁት። እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች ልጃችሁ የማመዛዘን ችሎታውን እንዲያሳድግ ይረዱታል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በብዙ ትዕግሥትና በማስተማር ጥበብ ውቀስ፣ ገሥጽ እንዲሁም አጥብቀህ ምከር።”—2 ጢሞቴዎስ 4:2

  •   ተገቢውን ቅጣት ጣሉ። ቅጣቱ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው ልጃችሁ ካጠፋው ጥፋት ጋር የሚገናኝ ከሆነ ነው። ለምሳሌ ልጃችሁ መኪናችሁን ሳያስፈቅድ በመውሰድ እምነት ካጓደለ ለተወሰነ ጊዜ ያህል መኪና በመጠቀም መብቱ ላይ ገደብ ልትጥሉበት ትችላላችሁ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።”—ገላትያ 6:7

  •   ዋናው ዓላማችሁ ልጃችሁ መልሶ እምነት እንዲያተርፍ መርዳት መሆኑን አትርሱ። እርግጥ ነው በአንድ ጀምበር መልሶ እምነት ማትረፍ አይቻልም። ይሁንና ልጃችሁ በጊዜ ሂደት መልሶ እምነታችሁን ማትረፍ እንደሚችል ሊያውቅ ይገባል። ልጃችሁ መቼም ቢሆን እምነታችሁን መልሶ ማግኘት እንደማይችል ከተሰማው እምነት ለማትረፍ መሞከሩን ከናካቴው ሊተወው ይችላል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።”—ቆላስይስ 3:21

a ዩ ኤንድ ዩር አዶለሰንት ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

b ይህ ርዕስ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ስላሉ ልጆች ሲናገር ተባዕታይ ፆታ ቢጠቀምም ሐሳቡ ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራል።