በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን አስመልክቶ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን አስመልክቶ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥር የፆታ ግንኙት እንዲፈጸም ያሰበው በጋብቻ በተሳሰሩ ወንድና ሴት መካከል ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ ዘሌዋውያን 18:22፤ ምሳሌ 5:18, 19) መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸምን ማንኛውንም የፆታ ግንኙነት ያወግዛል፤ በተቃራኒ ፆታም ሆነ በተመሳሳይ ፆታ መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነት ከዚህ የሚመደብ ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ይህም የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸምን፣ የሌላን ሰው የፆታ ብልት ማሻሸትን እንዲሁም በአፍ ወይም በፊንጢጣ ወሲብ መፈጸምን ይጨምራል።

 መጽሐፍ ግብረ ሰዶምን ቢያወግዝም ግብረ ሰዶማውያንን እንድንጠላ ግን አያበረታታም። ከዚህ ይልቅ ለክርስቲያኖች “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ” የሚል ትዕዛዝ ይሰጣል።​—1 ጴጥሮስ 2:17

አንድ ሰው በተፈጥሮው ግብረ ሰዶማዊ ሊሆን ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ የግብረ ሰዶማውያንን ተፈጥሮ አስመልክቶ በቀጥታ የሚናገረው ነገር የለም፤ ያም ቢሆን ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ የአምላክን ትዕዛዛት የመጣስ ዝንባሌ እንዳለን ይገልጻል። (ሮም 7:21-25) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች ግብረ ሰዶም የመፈጸም ፍላጎት እንዲያድርባቸው የሚያደርገውን ምክንያት በተመለከተ የሚናገረው ነገር ባይኖርም ግብረ ሰዶም መፈጸምን ይከለክላል።

የግብረ ሰዶምን ስሜት ተቋቁሞ አምላክን ማስደሰት።

መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋችሁ እንዲቆጣጠራችሁ አትፍቀዱ። ትክክል ያልሆኑ የፆታ ምኞቶችን በሙሉ ግደሉ” ይላል። (ቆላስይስ 3:5 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን) ወደ መጥፎ ድርጊት የሚያመሩ መጥፎ ምኞቶችን ለመግደል አስተሳሰብህን መቆጣጠር ያስፈልግሃል። አእምሮህን ምንጊዜም ጤናማ በሆኑ ሐሳቦች የምትሞላ ከሆነ መጥፎ ምኞቶችን ማስወገድ ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። (ፊልጵስዩስ 4:8፤ ያዕቆብ 1:14, 15) እንዲህ ማድረግ መጀመሪያ አካባቢ ከባድ ቢሆንም ውሎ አድሮ ግን እየቀለለህ መሄዱ አይቀርም። አምላክ ‘አእምሮህን በሚያሠራው ኃይል እየታደስክ እንድትሄድ’ እንደሚረዳህ ቃል ገብቷል።​—ኤፌሶን 4:22-24

 ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር የሚፈልጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግብረ ሰዶማዊ ያልሆኑ ሰዎችም ተመሳሳይ ትግል አለባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የማግባት አጋጣሚያቸው ጠባብ የሆነ ያላገቡ ሰዎች እንዲሁም በአካል ጉዳት የተነሳ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የማይችል የትዳር ጓደኛ ያላቸው ያገቡ ሰዎች ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥማቸውም የፆታ ፍላጎታቸውን ይቆጣጠራሉ። እነዚህ ሰዎች በደስታ መኖር ችለዋል፤ የግብረ ሰዶማዊነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ አምላክን ለማስደሰት ከልባቸው የሚፈልጉ ከሆነ እንዲሁ ማድረግ ይችላሉ።​—ዘዳግም 30:19