በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ለሚሰነዘርባቸው ለእያንዳንዱ ክስ ምላሽ የማይሰጡት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ለሚሰነዘርባቸው ለእያንዳንዱ ክስ ምላሽ የማይሰጡት ለምንድን ነው?

 የይሖዋ ምሥክሮች፣ ለሚሰነዘርብን ለእያንዳንዱ ክስ ወይም ፌዝ መልስ መስጠት እንደሌለብን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ “ፌዘኛን የሚያርም በራሱ ላይ ውርደት ያመጣል” ይላል። (ምሳሌ 9:7, 8፤ 26:4) ለሚሰነዘሩብን የሐሰት ክሶች ከልክ በላይ ትኩረት በመስጠት ንትርክ ውስጥ ከመግባት ይልቅ አምላክን ለማስደሰት ጥረት እናደርጋለን።—መዝሙር 119:69

 እርግጥ ነው፣ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:7) እውነቱን ለማወቅ ፈልገው በቅንነት ለሚጠይቁን ሰዎች መልስ እንሰጣለን፤ ሆኖም አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ ከመግባት እንቆጠባለን። እንዲህ በማድረግ፣ ኢየሱስና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ እንከተላለን።

  •   ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት ቀርቦ የሐስት ክስ በተሰነዘረበት ወቅት ምንም መልስ አልመለሰም። (ማቴዎስ 27:11-14፤ 1 ጴጥሮስ 2:21-23) ሰካራምና ሆዳም ነው ተብሎ በተወነጀለ ጊዜም ቢሆን መልስ አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ “ጥበብ ትክክል መሆኗ በውጤቷ ተረጋግጧል” ከሚለው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ከቃላት ይልቅ ተግባሩ መልስ እንዲሰጥ አድርጓል። (ማቴዎስ 11:19 የግርጌ ማስታወሻ) አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ግን ነቀፋ ለሰነዘሩበት ሰዎች ድፍረት የተሞላበት ምላሽ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 15:1-3፤ ማርቆስ 3:22-30

     ኢየሱስ ተከታዮቹን በሚሰነዘርባቸው የሐሰት ክስ ምክንያት ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው አስተምሯቸዋል። እንዲህ ብሏል፦ “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁና ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ።” (ማቴዎስ 5:11, 12) ሆኖም ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲህ ባሉ ክሶች የተነሳ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ በሚያገኙበት ጊዜ እንደሚከተለው በማለት የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ተናግሯል፦ “ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ በአንድነት ሆነው ሊቋቋሙት ወይም ሊከራከሩት የማይችሉት አንደበትና ጥበብ እሰጣችኋለሁ።”—ሉቃስ 21:12-15

  •   ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ከተቃዋሚዎች ጋር አላስፈላጊ ጭቅጭቅ ውስጥ ከመግባት እንዲቆጠቡ መክሯቸዋል፤ እንዲህ ያሉት ክርክሮች “ምንም የማይጠቅሙና ከንቱ” እንደሆኑ ተናግሯል።—ቲቶ 3:9፤ ሮም 16:17, 18

  •   ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን ሁኔታቸው በሚፈቅድበት ጊዜ ሁሉ ለእምነታቸው ጥብቅና እንዲቆሙ አበረታቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:15) ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው መንገድ በቃላት መናገር ሳይሆን በተግባር ማሳየት እንደሆነ ጠቁሟል። “መልካም ነገር በማድረግ ከንቱ ንግግር የሚናገሩትን ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎች አፍ ዝም [ማሰኘት]” እንደሚቻል ገልጿል።—1 ጴጥሮስ 2:12-15