በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 09

በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ ቅረብ

በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ ቅረብ

ሕይወትህን እንዴት መምራት እንዳለብህ የሚነግርህ አካል እንደሚያስፈልግህ ተሰምቶህ ያውቃል? መልስ ያላገኘህላቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች አሉህ? ማጽናኛና ማበረታቻ ያስፈልግሃል? ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ ትፈልጋለህ? ጸሎት እነዚህን ሁሉ ፍላጎቶችህን ለማሟላት ሊረዳህ ይችላል። ሆኖም መጸለይ ያለብን እንዴት ነው? አምላክ ለሁሉም ጸሎቶች መልስ ይሰጣል? አንተ የምታቀርበው ጸሎት በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት እንዲያገኝ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን።

1. መጸለይ ያለብን ወደ ማን ነው? ስለ ምን ነገሮችስ ልንጸልይ እንችላለን?

ኢየሱስ መጸለይ ያለብን በሰማይ ወዳለው አባታችን ብቻ እንደሆነ አስተምሯል። እሱ ራሱም ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ . . .’” (ማቴዎስ 6:9) ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት ይጠናከራል።

ስለፈለግነው ነገር ወደ አምላክ ልንጸልይ እንችላለን። እርግጥ ነው፣ አምላክ ለጸሎታችን መልስ እንዲሰጠን ከፈለግን የምንጠይቀው ነገር ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን [ከአምላክ ፈቃድ] ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።” (1 ዮሐንስ 5:14) ኢየሱስ በጸሎታችን ላይ ልናካትታቸው የሚገቡ ነገሮችን የሚያሳይ ናሙና ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 6:9-13⁠ን አንብብ።) በግል ስላሳሰቡን ነገሮች ከመጸለይ በተጨማሪ ላደረገልን ነገሮች አምላክን ማመስገናችንን መርሳት የለብንም፤ አምላክ ሌሎች ሰዎችን እንዲረዳቸውም መጸለይ ይኖርብናል።

2. መጸለይ ያለብን እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ልባችንን በአምላክ ፊት እንድናፈስ’ ያበረታታናል። (መዝሙር 62:8) ስለዚህ ጸሎታችን ከልብ የመነጨ መሆን አለበት። ድምፃችንን አውጥተንም ሆነ በልባችን እንዲሁም በየትኛውም ሰዓትና ቦታ ወደ አምላክ መጸለይ እንችላለን። አምላክ ወደ እሱ ስንጸልይ መቆም፣ መቀመጥ ወይም መንበርከክ እንዳለብን አልተናገረም። ዋናው ነገር ለእሱ አክብሮት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ መጸለያችን ነው።

3. አምላክ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠው እንዴት ነው?

በተለያዩ መንገዶች መልስ ሊሰጠን ይችላል። ይሖዋ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠን ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለበርካታ ጥያቄዎቻችን መልስ እናገኛለን። የአምላክን ቃል ማንበብ “ተሞክሮ የሌለውን ጥበበኛ ያደርጋል።” (መዝሙር 19:7፤ ያዕቆብ 1:5⁠ን አንብብ።) አምላክ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ውስጣዊ ሰላም ይሰጠናል። እንዲሁም እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ አገልጋዮቹን ተጠቅሞ ይደግፈናል።

ጠለቅ ያለ ጥናት

አምላክን የሚያስደስት ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነና መጸለይህ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልህ እንመለከታለን።

4. አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ከፈለግን ልናሟላቸው የሚገቡ መሥፈርቶች አሉ

አምላክ ጸሎታችንን ለመስማት ወይም ላለመስማት የሚወስነው የትኞቹን መሥፈርቶች መሠረት አድርጎ ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ

ይሖዋ ወደ እሱ እንድንጸልይ ይፈልጋል። መዝሙር 65:2ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ‘ጸሎት ሰሚ የሆነው አምላክ’ አንተ ወደ እሱ እንድትጸልይ የሚፈልግ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ከፈለግን እሱ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር አለብን። ሚክያስ 3:4ን እና 1 ጴጥሮስ 3:12ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ከፈለግን ምን ማድረግ አለብን?

በጦርነት ወቅት ሁለቱም ወገኖች ድል ለማግኘት ሊጸልዩ ይችላሉ። አምላክ እንዲህ ያሉ ጸሎቶችን ይሰማል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው?

5. ጸሎታችን ከልብ የመነጨ መሆን አለበት

አንዳንድ ሰዎች በቃል የሸመደዱትን ጸሎት እየደገሙ መጸለይ እንዳለባቸው ተምረዋል። ሆኖም አምላክ ወደ እሱ እንድንጸልይ የሚፈልገው በዚህ መንገድ ነው? ማቴዎስ 6:7ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በምትጸልይበት ጊዜ ‘አንድ ዓይነት ነገር ላለመደጋገም’ ሊረዳህ የሚችለው ምንድን ነው?

በየዕለቱ ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ ያደረገልህን አንድ ነገር ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያም ለዚህ ነገር ይሖዋን አመስግነው። ለአንድ ሳምንት ያህል በየዕለቱ እንዲህ ካደረግክ ስለ ሰባት ጉዳዮች ሳትደጋግም መጸለይ ትችላለህ።

አንድ ጥሩ አባት ልጁ የልቡን አውጥቶ እንዲነግረው ይፈልጋል። ይሖዋም ከልብ በመነጨ ስሜት ወደ እሱ እንድንጸልይ ይፈልጋል

6. ጸሎት የአምላክ ስጦታ ነው

በደጉም ሆነ በክፉው ጊዜ ወደ አምላክ መጸለያችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ።

መጽሐፍ ቅዱስ ጸሎት የአእምሮ ሰላም ለማግኘት እንደሚረዳን ይናገራል። ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ጸሎት ችግራችን እንዲወገድልን ላያደርግ ቢችልም ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

  • ስለ የትኞቹ ጉዳዮች መጸለይ ትፈልጋለህ?

ይህን ታውቅ ነበር?

“አሜን” የሚለው ቃል “ይሁን” ወይም “ተስማምቻለሁ” የሚል ትርጉም አለው። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ሰዎች በጸሎት መጨረሻ ላይ “አሜን” ይላሉ።—1 ዜና መዋዕል 16:36

7. የምትጸልይበት ጊዜ መድብ

አንዳንዴ ጊዜያችን በጣም ከመጣበቡ የተነሳ መጸለይ ልንረሳ እንችላለን። ኢየሱስ ለጸሎት ምን ያህል ቦታ ይሰጥ ነበር? ማቴዎስ 14:23ን እና ማርቆስ 1:35ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ኢየሱስ የሚጸልይበት ጊዜ ለማግኘት ምን ያደርግ ነበር?

  • አንተስ ለመጸለይ የሚሆን ጊዜ የምታገኘው የትኛው ሰዓት ላይ ነው?

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ጸሎት እንዲሁ ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ከማድረግ ያለፈ ጥቅም የለውም።”

  • አንተ ምን ትላለህ?

ማጠቃለያ

ከልብ በመነጨ ስሜት መጸለያችን ወደ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ፣ ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረንና ይሖዋን ለማስደሰት የሚያስፈልገንን ብርታት እንድናገኝ ይረዳናል።

ክለሳ

  • መጸለይ ያለብን ወደ ማን ነው?

  • መጸለይ ያለብን እንዴት ነው?

  • ጸሎት ከሚያስገኝልን ጥቅሞች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

ግብ

ምርምር አድርግ

ስለ ጸሎት ብዙ ጊዜ ለሚነሱ ጥያቄዎች የተሰጠውን መልስ አንብብ።

“ጸሎት—ልታውቃቸው የሚገቡ ሰባት ነገሮች” (መጠበቂያ ግንብ ጥቅምት 1, 2010)

መጸለይ ያለብህ ለምን እንደሆነና የጸሎትህን ይዘት ማሻሻል የምትችለው እንዴት እንደሆነ አንብብ።

“መጸለይ ጥቅም አለው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ወደ ማን እንድንጸልይ ነው?

“ወደ ቅዱሳን መጸለይ ይገባኛል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

የምንጸልይበት ቦታና ጊዜ ለውጥ ያመጣል? መልሱን ከዚህ የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ተመልከት።

ሁልጊዜ ጸልይ (1:22)