በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

መለያየት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

መለያየት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

 ስቲቨን እንዲህ ብሏል፦ “ከሴት ጓደኛዬ ጋር መለያየቴ በከፍተኛ ሐዘን እንድዋጥ አድርጎኝ ነበር። በሕይወቴ ውስጥ እንደዚያ ያለ ቅስም የሚሰብር ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም።”

 አንቺስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞሻል? ከሆነ ይህን ርዕስ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ታገኝዋለሽ።

 የሚሰማሽ ስሜት

 መለያየታችሁ በሁለታችሁም ላይ የስሜት ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም።

  •  ግንኙነታችሁ እንዲቋረጥ ያደረግሽው አንቺ ከሆንሽ እንደ ጃዝሚን ይሰማሽ ይሆናል፤ እንዲህ ብላለች፦ “አስብለት የነበረን ሰው እንደጎዳሁት ማወቄ ሕሊናዬን ይረብሸኝ ነበር፤ እንዲህ ያለው ሁኔታ ዳግም እንዲያጋጥመኝ አልፈልግም።”

  •  ግንኙነታችሁ እንዲቋረጥ ያደረግሽው አንቺ ካልሆንሽ ግን አንዳንዶች ተመሳሳይ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው በቁማቸው እንደሞቱ የሚሰማቸው ለምን እንደሆነ ሳትረጂ አትቀሪም። ጃኔት የተባለች ወጣት እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “የተለያዩ የሃዘን ስሜቶች ተፈራርቀውብኛል። እውነታውን ለመቀበል እቸገር እና እናደድ የነበረ ከመሆኑም በላይ የመንፈስ ጭንቀት ይዞኝ ነበር፤ ወደ አንድ ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ግን እውነታውን አምኜ ተቀበልኩ።”

 ዋናው ነጥብ፦ ከጓደኛሽ ጋር መለያየትሽ ቅስምሽን ሊሰብረውና በሐዘን እንድትዋጪ ሊያደርግሽ ይችላል። ሁኔታው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “የተደቆሰ መንፈስ . . . ኃይል ያሟጥጣል” በማለት ካሰፈረው ሐሳብ ጋር ይመሳሰላል።—ምሳሌ 17:22

 ምን ማድረግ ትችያለሽ?

  •  እምነት ለሚጣልበት ትልቅ ሰው ስሜትሽን ተናገሪ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።” (ምሳሌ 17:17) ለወላጆችሽ አሊያም እምነት ሊጣልበት ለሚችል አንድ ጓደኛሽ ስሜትሽን አውጥተሽ መናገርሽ ሚዛንሽን እንድትጠብቂ ሊረዳሽ ይችላል።

     “ለብዙ ወራት ራሴን ከሰዎች ያገለልኩ ሲሆን ስሜቴንም ለማንም አውጥቼ አልተናገርኩም ነበር። ይሁንና ጓደኞች ከሐዘናችን ቶሎ እንድናገግም ይረዱናል። እፎይታ ማግኘት የቻልኩት ስሜቴን አውጥቼ ከነገርኳቸው በኋላ ነበር።”—ጃኔት

  •  ከተፈጠረው ሁኔታ ትምህርት ውሰጂ። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ደግሞ “ጥበብን አግኝ፤ ማስተዋልንም አዳብር” ይላል። (ምሳሌ 4:5) በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፋችን ስለ ራሳችን ብዙ ነገር እንድናውቅና ችግሮችን እንዴት መወጣት እንደምንችል ያስገነዝቡናል።

     “ከሴት ጓደኛዬ ጋር ከተለያየን በኋላ አንድ ጓደኛዬ ‘ከሁኔታው ምን ተማርክ? ያገኘኸውን ትምህርት ወደፊት ከሌላ ሰው ጋር መጠናናት ስትጀምር ልትጠቀምበት የምትችለውስ እንዴት ነው?’ ብሎ ጠየቀኝ።”—ስቲቨን

  •  ጸልዪ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል” ይላል። (መዝሙር 55:22) ጸሎት ማቅረብሽ ሐዘንሽን ለመቋቋም እና የግንኙነታችሁን መቋረጥ ከሌላ አቅጣጫ ለመመልከት ይረዳሻል።

     “አዘውትራችሁ ጸልዩ። ይሖዋ ያጋጠማችሁን የስሜት ጉዳት ይረዳላችኋል፤ ሁኔታውን ከእናንተ በላይ ጠንቅቆ ያውቃል።”—ማርሲያ

  •  ሌሎች ሰዎችን እርጂ። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ” በማለት ይናገራል። (ፊልጵስዩስ 2:4) ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ባደረግሽ ቁጥር፣ የተቋረጠውን ግንኙነትሽን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማየት ትጀምሪያለሽ።

     “ከጓደኛ ጋር መለያየት ሁሉ ነገር ጭልምልም እንዲል ያደርጋል፤ እያደር ግን ሁኔታው እንደሚሻሻል ተመልክቻለሁ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ከሐዘኔ ማገገም ችያለሁ።—ኤቭሊን