በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የወላጆቼን ሕግ ጥሻለሁ—ምን ባደርግ ይሻላል?

የወላጆቼን ሕግ ጥሻለሁ—ምን ባደርግ ይሻላል?

 አብዛኞቹ ቤተሰቦች የራሳቸውን ሕግ ያወጣሉ። ለምሳሌ ቤት መግቢያ ሰዓትን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ወይም ሥነ ምግባርን አስመልክቶ ሕግ ሊያወጡ ይችላሉ።

 የወላጆችህን ሕግ ከጣስክ ምን ማድረግ ትችላለህ? ያለፈውን መቀየር አትችልም፤ ግን ነገሮች እንዳይባባሱ ማድረግ ትችላለህ። ይህ ርዕስ ይህን ማድረግ የምትችልበትን መንገድ ይጠቁምሃል።

 ማድረግ የሌለብህ ነገር

  •   ወላጆችህ ጥፋት ማጥፋትህን ካላወቁ ጥፋቱን ለመደበቅ ትፈተን ይሆናል።

  •   ጥፋት ማጥፋትህን ወላጆችህ ካላወቁ ሰበብ ለመደርደር ወይም ጥፋቱን በሌላ ሰው ላይ ለማላከክ ትፈተን ይሆናል።

 ሁለቱም አማራጮች ጥሩ አይደሉም። ለምን? ምክንያቱም ጥፋቱን መሸፋፈንህም ሆነ ሰበብ አስባብ መደርደርህ እንዳልበሰልክ ያሳያል። እንዲያውም እንዲህ ማድረግህ ወላጆችህ እንደ ሕፃን እንዲቆጥሩህ ሊያደርግ ይችላል።

 “መዋሸት መቼም ቢሆን መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ውሎ አድሮ እውነቱ መውጣቱ አይቀርም። መዋሸትህ ሲታወቅ የሚደርስብህ ቅጣት መጀመሪያውኑ እውነቱን ተናግረህ ቢሆን ኖሮ ከሚደርስብህ ቅጣት መባሱ አይቀርም።”—ዲያና

 የተሻለ ዘዴ

  •   ስህተትህን አምነህ ተቀበል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሠራውን በደል የሚሸፋፍን አይሳካለትም” ይላል። (ምሳሌ 28:13) ወላጆችህ ፍጹም መሆን እንደማትችል ያውቃሉ። ሐቀኛ እንድትሆን ግን ይጠብቁብሃል።

     “ጥፋትህን ከተናገርክ ወላጆችህ አንተን ይቅር ማለት ይቀላቸዋል። እውነቱን ከተናገርክ ሐቀኛ እንደሆንክ ይገነዘባሉ፤ እንዲሁም በአንተ ላይ ያላቸው እምነት ይጨምራል።”—ኦሊቪያ

  •   ይቅርታ ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስ “ትሕትናን ልበሱ” ይላል። (1 ጴጥሮስ 5:5) ሰበብ አስባብ ከመደርደር ይልቅ “ይቅርታ” ማለት ትሕትና ይጠይቃል።

     “ሁልጊዜ ሰበብ አስባብ የሚደረድሩ ሰዎች ሕሊናቸው እየደነዘዘ ሊሄድ ይችላል። ውሎ አድሮም ስህተት መሥራታቸው ጨርሶ የማይረብሻቸው ደረጃ ላይ ይደርሳሉ።”—ሄዘር

  •   ውጤቱን ተቀበል። መጽሐፍ ቅዱስ “ተግሣጽን ስሙ” ይላል። (ምሳሌ 8:33) ሳታጉረመርም ወላጆችህ የሚሰጡህን ቅጣት ተቀበል።

     “ቅጣት ስትቀበል ማጉረምረምህ ሁኔታውን ያባብሰዋል። ቅጣቱን እመንበት፤ እንዲሁም ባጣኸው ነገር ላይ አታተኩር።”—ጄሰን

  •   የወላጆችህን አመኔታ መልሰህ ለማትረፍ ጥረት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውን አሮጌውን ስብዕናችሁን አውልቃችሁ ጣሉ’ ይላል። (ኤፌሶን 4:22) ወላጆችህ እምነት እንዲጥሉብህ የሚያደርጉ ነገሮችን አድርግ።

     “በቀጣይነት ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎችን በማድረግ ስህተቱን እንደማትደግመው ለወላጆችህ የምታሳያቸው ከሆነ ውሎ አድሮ መልሰው እምነት ይጥሉብሃል።”—ኬረን

 ጠቃሚ ምክር፦ እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ለማሳየት ከሚጠበቅብህ ነገር አልፈህ ሂድ። ለምሳሌ በቀጣዩ ጊዜ ከቤት ስትወጣ፣ ባታመሽም እንኳ መንገድ ስትጀምር ቤት እየመጣህ እንደሆነ ለወላጆችህ ደውለህ ንገራቸው። እንዲህ ማድረግህ የእነሱን አመኔታ መልሰህ ማትረፍ እንደምትፈልግ ያሳያቸዋል።