በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ዓይናፋርነትን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

ዓይናፋርነትን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

 የሚያሳዝነው ነገር፦ ዓይናፋርነት ጥሩ ወዳጅነት መመሥረትና አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ የምትችልበትን አጋጣሚ ሊያሳጣህ ይችላል።

 ደስ የሚለው ነገር፦ ዓይናፋርነት ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ከመናገርህ በፊት እንድታስብ እንዲሁም ጥሩ ተመልካችና አድማጭ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል።

 ይበልጥ ደስ የሚለው ነገር፦ ዓይናፋርነት ሊቀየር የማይችል ባሕርይ አይደለም፤ ደግሞም የሚያሳድርብህን አሉታዊ ተጽዕኖ መቆጣጠር ትችላለህ። ይህ ርዕስ እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

 የሚያስፈራህ ነገር ምን እንደሆነ ለይተህ ለማወቅ ሞክር

 ዓይናፋር ከሆንክ ሰዎችን ፊት ለፊት ማነጋገር በጣም ሊጨንቅህ ይችላል። ይህም በጨለማ ክፍል ውስጥ ብቻህን ያለህ ያህል ከሌሎች እንደተገለልክ እንዲሰማህ ያደርግ ይሆናል። ይህ ደግሞ ፍርሃት ሊያሳድርብህ ይችላል። ሆኖም የሚያስፈራህ ነገር ምን እንደሆነ ለይተህ ለማወቅ ጥረት ካደረግክ የሚሰማህ ፍርሃት መሠረተ ቢስ እንደሆነ ማስተዋልህ አይቀርም። እስቲ ሦስት ምሳሌዎችን ተመልከት።

  •   ፍርሃት 1፦ “ምን እንደማወራ ይጠፋብኛል።”

     እውነታው፦ ሰዎች ከምትናገረው ነገር በላይ የሚያስታውሱት ከአንተ ጋር ሲነጋገሩ የተሰማቸውን ስሜት ነው። የማዳመጥ ችሎታህን በማሻሻልና ሌሎች ለሚናገሩት ነገር ትኩረት በመስጠት ፍርሃትህን ማሸነፍ ትችላለህ።

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ አንተ በግልህ ጓደኛህ እንዲሆን የምትፈልገው ምን ዓይነት ሰው ነው? ያለማቋረጥ የሚለፈልፍ ወይስ ጥሩ አድማጭ የሆነ ሰው?

  •   ፍርሃት 2፦ “ካወራሁ ሰዎች ስለ እኔ መጥፎ አመለካከት ይኖራቸዋል።”

     እውነታው፦ ዓይናፋር ሆንክም አልሆንክ ሰዎች ስለ አንተ የሆነ አመለካከት መያዛቸው አይቀርም። ትክክለኛ ማንነትህ እንዲታወቅ ካደረግክ ግን ሰዎች ስለ አንተ የተሻለ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፤ ይህም ፍርሃትህን እንድታሸንፍ ይረዳሃል።

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ሁሉም ሰው ስለ አንተ አሉታዊ አመለካከት እንዳለው የምታስብ ከሆነ ሰዎችን በተሳሳተ መንገድ እየፈረጅክ ያለኸው አንተ ትሆን?

  •   ፍርሃት 3፦ “አጉል ነገር ተናግሬ ከምዋረድ ዝም ብል ይሻላል።”

     እውነታው፦ ሁሉም ሰው የተሳሳተ ነገር መናገሩ አይቀርም። እንዲህ ያሉ ስህተቶችን፣ ራስህን ፍጹም አድርገህ እንደማትመለከት ለማሳየት እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገህ በመቁጠር ፍርሃትህን ማሸነፍ ትችላለህ።

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ራሳቸውን ፍጹም አድርገው ከማይቆጥሩ ሰዎች ጋር መሆን ደስ አይልህም?

 ይህን ታውቅ ነበር? አንዳንድ ሰዎች የጽሑፍ መልእክት በብዛት ስለሚላላኩ ዓይናፋር እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ሆኖም እውነተኛ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችለው የተሻለው ዘዴ ዓይን ለዓይን እየተያዩ ማውራት ነው። የሥነ ልቦናና የቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆኑት ሼሪ ተርክል “ከሰዎች ጋር ልብ ለልብ መገናኘት የምንችለው ፊታቸውን ስናይ እና ድምፃቸውን ስንሰማ ነው” በማለት ጽፈዋል። a

ፍርሃትህን መቆጣጠር ከቻልክ፣ ከሰዎች ጋር ፊት ለፊት መነጋገር ቀደም ሲል የምታስበውን ያህል ከባድ እንዳልሆነ ልትገነዘብ ትችላለህ

 ሊረዱህ የሚችሉ ነገሮች

  •   ራስህን ከሌሎች ጋር አታወዳድር። በጣም ተግባቢ መሆን አይጠበቅብህም። ከዚህ ይልቅ ግብህ ዓይናፋርነትህን በተወሰነ መጠን በመቆጣጠር ጥሩ ወዳጅነት ከመመሥረትና አስደሳች ጊዜ ከማሳለፍ እንዳያግድህ ማድረግ ሊሆን ይገባል።

     “ረጅም ውይይት ማድረግ ወይም ጨዋታ አድማቂ መሆን እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። ከአዲስ ሰው ጋር ለመተዋወቅ ወይም ጥቂት ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ጥረት ማድረግህ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።”—አሊሺያ

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

  •   አስተዋይ ሁን። ተግባቢ የሆኑ ሰዎች ከሌሎች ጋር የሚጨዋወቱት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። ጥሩ ውይይት ለማድረግ የሚረዳቸው ምንድን ነው? ምን ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችስ አስተውለሃል? ካሏቸው ችሎታዎች መካከል አንተ መኮረጅ የምትፈልገው የትኛውን ነው?

     “ከሌሎች ጋር በቀላሉ የሚቀራረቡ ሰዎችን በማየት ከእነሱ ተማር። ከአንድ ሰው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ የሚያደርጉትንና የሚናገሩትን ነገር ተመልከት።”—አሮን

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል።”—ምሳሌ 27:17

  •   ጥያቄዎችን ጠይቅ። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ስለተለያዩ ነገሮች ያላቸውን አመለካከት መናገር ያስደስታቸዋል፤ ስለዚህ ጥያቄ መጠየቅ ውይይት ለመጀመር የሚያስችል ጥሩ ዘዴ ነው። በተጨማሪም ጥያቄ መጠየቅህ በአንተ ላይ ብዙ ትኩረት እንዳያርፍ ይረዳሃል።

     “አስቀድመህ መዘጋጀትህ የሚሰማህን ጭንቀት ለመቀነስ ይረዳሃል። በአንድ ማኅበራዊ ዝግጅት ላይ ከመገኘትህ በፊት ልታነሳቸው የምትችላቸውን ጉዳዮች ወይም ጥያቄዎች አስቀድመህ ማሰብህ አዳዲስ ሰዎችን መተዋወቅ የሚፈጥርብህን ጭንቀት ቀለል ያደርግልሃል።”—አላና

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4

a ሪክሌይሚንግ ኮንቨርሴሽን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።