በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ሲደብረኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?

ሲደብረኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?

 አንዳንዶች፣ የሚሄዱበት ቦታ ወይም የሚያደርጉት ነገር ሳይኖራቸው ዝናባማ በሆነ ቀን ቤታቸው ዝም ብለው እንደ መቀመጥ የሚደብራቸው ነገር የለም። ሮበርት የተባለ አንድ ወጣት “እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲገጥመኝ ምን ማድረግ እንደምችል ስለማላውቅ ዝም ብዬ ቁጭ እላለሁ” በማለት ተናግሯል።

 አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ሊረዳህ ይችላል!

 ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

  •   ቴክኖሎጂ መጠቀም መፍትሔ ላይሆን ይችላል።

     የኢንተርኔት ገጾችን ማሰስ ጊዜን ለማሳለፍ ቢረዳም አዳዲስ ነገሮችን ከመሞከር ሊያግድህ ይችላል፤ ይህም ይበልጥ እንዲደብርህ ሊያደርግ ይችላል። የ21 ዓመቱ ጄረሚ “ስለ ምንም ነገር ሳላስብ ስክሪኑ ላይ ብቻ አፍጥጬ ቁጭ እላለሁ” ብሏል።

     ኤለና የተባለች ወጣት በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “ቴክኖሎጂ ተጠቅመህ ማከናወን የምትችለው ነገር ገደብ አለው። ከእውነታው ዓለም ተገልለህ እንድትቆይ ስለሚያደርግህ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያህን መጠቀምህን ስታቆም የበለጠ ይደብርሃል።”

  •   አመለካከት ለውጥ ያመጣል

     ልታከናውነው የምትችለው ብዙ ነገር ያለህ መሆኑ ብቻ እንዳይደብርህ ያደርጋል? ይህ ለምታከናውነው ነገር ባለህ ፍቅር ላይ የተመካ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ካረን የተባለች ወጣት እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ትምህርት ቤት ስውል ቀኑን ሙሉ ላከናውነው የምችለው ብዙ ነገር ቢኖረኝም በጣም ይሰለቸኝ ነበር። የምትሠራው ነገር እንዳይደብርህ ሥራውን ልትወደው ይገባል።”

 ይህን ታውቅ ነበር? “ምንም የምትሠራው ነገር የሌለህ” መሆኑ እንቅፋት ሳይሆን ጥሩ አጋጣሚ ነው፤ ይህን አጋጣሚ የፈጠራ ችሎታህን ለማሳደግ እንደሚረዳ ለም አፈር ልትቆጥረው ትችላለህ።

ትርፍ ጊዜ የፈጠራ ችሎታህን ለማሳደግ እንደሚረዳ ለም አፈር ነው

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

 የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን ሞክር። አዳዲስ ጓደኞች ለማፍራት ጣር። አዲስ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ለማግኘት ሞክር። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምርምር አድርግ። የተለያየ ነገር የሚሞክሩ ሰዎች ብቻቸውን ሲሆኑ ቶሎ አይደብራቸውም፤ ሌሎች ሰዎችም ከእነሱ ጋር ሲሆኑ አይደብራቸውም!

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን።”—መክብብ 9:10

 “በቅርቡ ማንዳሪን ቻይንኛ መማር ጀምሬያለሁ፤ በየቀኑ ቋንቋውን መለማመዴ አዲስ ነገር መማር በጣም አስደሳች ነገር እንደሆነ እንዳስታውስ አድርጎኛል። አዲስ ፕሮጀክት ያለኝ መሆኑን በጣም ወድጄዋለሁ። በተጨማሪም አእምሮዬ እንዳይባዝንና ጊዜዬን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድጠቀምበት ረድቶኛል።”—ሜሊንዳ

 ዓላማህ ላይ ትኩረት አድርግ። አንድ ነገር የምታከናውንበትን ዓላማ ከተገነዘብክ ሥራውን ለማከናወን የበለጠ መጓጓትህ አይቀርም። ዓላማህን በአእምሮህ መያዝህ ትምህርት ቤት የተሰጠህን የቤት ሥራ መሥራት እንኳ ቶሎ እንዳይሰለችህ ያደርጋል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰው . . . ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም።”—መክብብ 2:24

 “ትምህርት ልጨርስ አካባቢ ወደ ኋላ የቀረሁበትን ጥናት ለማካካስ በየቀኑ ለስምንት ሰዓታት ማጥናት አስፈልጎኝ ነበር። ዓላማዬን ለማሳካት ቆርጬ ስለነበር ይህ አሰልቺ አልሆነብኝም። ፈተናውን አልፌ ለመመረቅ የነበረኝን ዓላማ በአእምሮዬ መያዜ በትጋት ለማጥናት አነሳስቶኛል።”—ሐና

 መለወጥ የማትችለውን ነገር አምነህ ተቀበል። በጣም የሚያስደስትህ ነገር እንኳ አንዳንድ አሰልቺ ነገሮች እንደሚኖሩት የታወቀ ነው። በጣም የምትወዳቸው ጓደኞችህም ቀጠሯችሁን በመሰረዛቸው የተነሳ ጊዜህን የምታሳልፍበት ነገር ልታጣ ትችላለህ። እንዲህ ያለው ሁኔታ ደስታህን እንዲያሳጣህ ከመፍቀድ ይልቅ ነገሩን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለመመልከት ጣር።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ደስተኛ ልብ ያለው ሰው . . . ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው።”—ምሳሌ 15:15

 “አንዲት ጓደኛዬ ለብቻዬ ሆኜም አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ እንድለምድ መከረችኝ። በተጨማሪም ከሌሎችም ጋርም ሆነ ለብቻችን የምናሳልፈውን ጊዜ ማመጣጠን፣ ሁላችንም ሊኖረን የሚገባ በጣም አስፈላጊ ችሎታ እንደሆነ ነግራኛለች።”—አይቪ