በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 15

እውቀት መቅሰምህን መቀጠል ያለብህ ለምንድን ነው?

እውቀት መቅሰምህን መቀጠል ያለብህ ለምንድን ነው?

1. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን መቀጠልህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በዚህ ብሮሹር አማካኝነት ጠቅለል ባለ መልኩ መመልከትህ ለይሖዋ ያለህን ፍቅር እንዳጠናከረልህ ጥርጥር የለውም። ይህ ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። (1 ጴጥሮስ 2:2) የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋህ የተመካው የአምላክን ቃል እያጠናህ ወደ እሱ በመቅረብህ ላይ ነው።​—ዮሐንስ 17:3ን እና ይሁዳ 21ን አንብብ።

ስለ አምላክ ያለህ እውቀት እያደገ ሲሄድ እምነትህ ይበልጥ ይጠናከራል። እምነት ደግሞ አምላክን ለማስደሰት ያስችልሃል። (ዕብራውያን 11:1, 6) እምነት፣ ንስሐ እንድትገባና በሕይወትህ ውስጥ ጠቃሚ የሆኑ ለውጦችን እንድታደርግ ያነሳሳሃል።​—የሐዋርያት ሥራ 3:19ን አንብብ።

2. ስለ አምላክ ያገኘኸው እውቀት ሌሎችን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና መመሥረት ትችላለህ

የተማርከውን ነገር ለሌሎች ለመናገር እንደምትፈልግ ግልጽ ነው፤ ሁላችንም ብንሆን ምሥራች ማብሰር ያስደስተናል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን ስትቀጥል በይሖዋ ላይ ስላለህ እምነትና ስለ ምሥራቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመህ ለሰዎች እንዴት እንደምታስረዳ ትማራለህ።​—ሮም 10:13-15ን አንብብ።

አብዛኞቹ ሰዎች ምሥራቹን መጀመሪያ የሚነግሩት ለጓደኞቻቸው ወይም ለዘመዶቻቸው ነው። አንተም ይህንን ስታደርግ ዘዴኛ ሁን። ሃይማኖታቸው ስህተት እንደሆነ ከመግለጽ ይልቅ አምላክ ስለሰጠን ተስፋዎች ንገራቸው። በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜ ሰዎችን የሚማርካቸው የምትናገረው ነገር ሳይሆን የምታሳያቸው ደግነት እንደሆነ አስታውስ።​—2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25ን አንብብ።

3. ከአምላክ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና መመሥረት ትችላለህ?

የአምላክን ቃል ማጥናትህ በመንፈሳዊ እንድታድግ ይረዳሃል። ውሎ አድሮ ከይሖዋ ጋር በጣም ልዩ ዝምድና መመሥረት ትችላለህ። እንዲያውም የእሱ ቤተሰብ አባል መሆን ትችላለህ።​—2 ቆሮንቶስ 6:18ን አንብብ።

4. እድገት ማድረግህን መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው?

የአምላክን ቃል ማጥናትህን በመቀጠል በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ ትችላለህ። (ዕብራውያን 5:13, 14) የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኑህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ። የአምላክን ቃል ይበልጥ በተማርክ መጠን ሕይወትህ ይበልጥ ስኬታማ ይሆናል።​—መዝሙር 1:1-3ን እና 73:27, 28ን አንብብ።

ምሥራቹ የመጣው ደስተኛ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ነው። እሱን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በመቀራረብ ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ ትችላለህ። (ዕብራውያን 10:24, 25) ይሖዋን ለማስደሰት ጥረት ማድረግህን የምትቀጥል ከሆነ እውነተኛውን ሕይወት ይኸውም የዘላለም ሕይወት ማግኘት ትችላለህ። በእርግጥም በሕይወትህ ልታደርጋቸው ከምትችላቸው ነገሮች በሙሉ የላቀው ወደ አምላክ መቅረብ ነው።​—1 ጢሞቴዎስ 1:11ን እና 6:19ን አንብብ።