በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 8

አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

1. ክፋት የጀመረው እንዴት ነው?

አምላክ፣ ሰዎች ለረጅም ጊዜ እንዲገዙ የፈቀደው ሰብዓዊ አገዛዝ የሰው ልጆችን ችግር ማስወገድ እንደማይችል ለማሳየት ነው

ክፋት በምድር ላይ የጀመረው ሰይጣን የመጀመሪያውን ውሸት ሲናገር ነበር። ሰይጣን መጀመሪያ ላይ ፍጹምና ጥሩ መልአክ ነበር፤ ይሁን እንጂ “በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም።” (ዮሐንስ 8:44) ሰይጣን ለአምላክ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለራሱ የማድረግ ምኞት አደረበት። በመሆኑም ሰይጣን ለመጀመሪያዋ ሴት ለሔዋን ውሸት በመናገር ከአምላክ ይልቅ እሱን እንድትታዘዝ አሳመናት። አዳምም በአምላክ ላይ በማመፅ ከሔዋን ጋር ተባበረ። የአዳም ውሳኔ መከራና ሞት አስከተለ።​—ዘፍጥረት 3:1-6, 19ን አንብብ።

ሰይጣን፣ አምላክን እንዳትታዘዝ ሔዋንን ሲያግባባት በአምላክ ሉዓላዊነት ወይም በመግዛት መብቱ ላይ ዓመፅ እያስነሳ ነበር። አብዛኞቹ የሰው ዘሮች የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን በማለት ከሰይጣን ጋር ተባብረዋል። በዚህም ምክንያት ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዢ” ሆኗል።​—ዮሐንስ 14:30ን እና 1 ዮሐንስ 5:19ን አንብብ።

2. የአምላክ ፍጥረታት ጉድለት ነበረባቸው?

የአምላክ ሥራ ሁሉ ፍጹም ነው። አምላክ የፈጠራቸው ሰዎችም ሆኑ መላእክት ፍጹም በሆነ መንገድ እሱን መታዘዝ ይችሉ ነበር። (ዘዳግም 32:4, 5) አምላክ ሲፈጥረን መልካም ወይም ክፉ የሆነውን ለማድረግ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። ይህ ነፃነት ለአምላክ ያለንን ፍቅር እንድንገልጽ አጋጣሚ ይሰጠናል።​—ያዕቆብ 1:13-15ን እና 1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።

3. አምላክ መከራና ሥቃይ እስከ አሁን እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው?

ይሖዋ በእሱ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ዓመፅ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል ፈቅዷል። ለምን? ያለ እሱ ድጋፍ የሰው ልጆችን ለማስተዳደር የሚደረገው ማንኛውም ጥረት እንደማይጠቅማቸው ለማሳየት ነው። (መክብብ 7:29፤ 8:9) ለ6,000 ዓመት የዘለቀው የሰው ልጅ ታሪክ አንድን እውነታ በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል፦ ሰብዓዊ ገዢዎች ጦርነትን፣ ወንጀልን፣ የፍትሕ መጓደልን ወይም በሽታን ለማስቀረት የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም።​—ኤርምያስ 10:23ን እና ሮም 9:17ን አንብብ።

ከሰብዓዊ አገዛዝ በተቃራኒ የአምላክ አገዛዝ፣ ለተገዢዎቹ ጥቅም ያስገኝላቸዋል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) በቅርቡ ይሖዋ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ያጠፋል። የአምላክን አገዛዝ የመረጡ ሰዎች ብቻ በምድር ላይ ይኖራሉ።—ኢሳይያስ 11:9​—ዳንኤል 2:44ን አንብብ።

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት

4. አምላክ መታገሡ ምን አጋጣሚ ከፍቶልናል?

ሰይጣን፣ ይሖዋን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ተነሳስቶ የሚያገለግል ማንም ሰው የለም የሚል ክስ ሰንዝሯል። ክሱ ውሸት መሆኑን ማሳየት ትፈልጋለህ? ይህን ማድረግ ትችላለህ! አምላክ መታገሡ ከእሱ ወይም ከሰዎች አገዛዝ የትኛውን እንደምንመርጥ ለማሳየት ለእያንዳንዳችን አጋጣሚ ከፍቶልናል። የመረጥነው የትኛውን አገዛዝ እንደሆነ አኗኗራችን ያሳያል።​—ኢዮብ 1:8-12ን እና ምሳሌ 27:11ን አንብብ።

5. አምላክ ገዢያችን እንዲሆን መምረጣችንን የምናሳየው እንዴት ነው?

የምናደርጋቸው ምርጫዎች አምላክ ገዢያችን እንዲሆን እንፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ ያሳያሉ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሰፈረው መሠረት ስለ እውነተኛው አምልኮ የምንማርና የተማርነውን ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ አምላክ ገዢያችን እንዲሆን እንደመረጥን እናሳያለን። (ዮሐንስ 4:23) በተጨማሪም ልክ እንደ ኢየሱስ በፖለቲካና በጦርነት ባለመካፈል የሰይጣንን አገዛዝ እንደማንቀበል ማሳየት እንችላለን።​—ዮሐንስ 17:14ን አንብብ።

ሰይጣን፣ ሥነ ምግባር የጎደላቸውና ጎጂ የሆኑ ልማዶች ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ በሥልጣኑ ይጠቀማል። እንደነዚህ ባሉ ድርጊቶች ካልተካፈልን አንዳንድ ጓደኞቻችንና ዘመዶቻችን ሊያሾፉብን ወይም ሊቃወሙን ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 4:3, 4) በመሆኑም ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል። አምላክን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ነን? ጥበብና ፍቅር የተንጸባረቀባቸውን የአምላክ ሕግጋት እንታዘዛለን? ከሆነ ሰይጣን፣ ማንም ሰው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት አምላክን እንደማይታዘዝ የሰነዘረው ሐሳብ ውሸት መሆኑን እናረጋግጣለን።​—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10ን እና 15:33ን አንብብ።

አምላክ ለሰው ዘር ያለው ፍቅር፣ ክፋትና መከራ እንደሚወገድ ዋስትና ይሆነናል። የአምላክ መንገድ ትክክል እንደሆነ የሚያምኑና አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው እንደሚቀበሉ በተግባር የሚያሳዩ ሁሉ በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።​—ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።